Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለቀጠሮ ማረፊያ ቤቱ ቃጠሎ መንስኤ የሽብርና የከባድ ወንጀል የህግ እስረኞች የቀሰቀሱት ዓመፅ ነው – የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን

0 592

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዲስ አበባ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በቀጠሮ ማረፊያ ቤት ላይ የደረሰው ቃጠሎ መንስኤ የሽብርና የከባድ ወንጀል የህግ እስረኞች በቀሰቀሱት ዓመፅ የተከሰተ መሆኑን ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።

ቅሊንጦ በሚገኘው በአስተዳደሩ የቀጠሮ ማረፊያ ቤት ላይ ነሓሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም በተከሰተው ቃጠሎ 23 የህግ እስረኞች ለህልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ የቃጠሎውን መንስኤ በተመለከተ ምርመራ ሲያካሄድ ቆይቷል።

ኮሚሽኑ ያካሄደውን ምርመራ ውጤት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለህግ ፍትህና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ዛሬ አቅርቧል።

ኮሚሽነር ዶክተር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር ሪፖርቱን ሲያቀርቡ እንደገለፁት፤ በማረፊያ ቤቱ ቃጠሎ ተከስቶ የነበረው በቅፅበት ሳይሆን በሽብርና በከባድ ወንጀል ተጠርጥረው የህግ እስረኞች በቀሰቀሱት ዓመፅ ነው።

በሽብርና በከባድ ወንጀል የህግ እስረኞች የሆኑ ቃጠሎው ከመነሳቱ አስቀድመው ባደረጉት ቅስቀሳ አማካኝነት የታራሚዎች ተቃውሞና ዓመጽ ሳምንት ሙሉ እንደነበር በምርመራው መረጋገጡን ገልፀዋል።

በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ እና የወንጀል ሪከርድ ያለባቸውን ሰዎች በአንድ ላይ መታሰርና ወደ ግቢው ተቀጣጣይ ነገሮች መግባት መቻላቸው ለዓመጹ ቀስቃሾች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ነው ያረጋገጡት።

ዓመፅ ለመቀስቀስና ለማምለጥ የሚሞክሩ በከባድ ወንጀል የተጠረጠሩ እስረኞች መኖራቸውን አስመልክቶ የእስረኞች አስተባባሪዎች በተደጋጋሚ ለኃላፊዎች እንደተናገሩ ጠቁመው፤ መረጃውን ተቀብሎ ጥንቃቄ ያለመደረጉንና ቃጠሎውን ለማስቀረት ያለመቻሉን ገልጸዋል።

እንደኮሚሽነሩ ገለጻ፤ በጥቂት ሰዎች ላይ ለተከሰተው አተት መንስኤ ከውጪ የሚገባ ምግብ መሆኑ በሀኪሞች በመገለጹ ለተወሰነ ጊዜ እንዳይገባ ተደርጓል። ይህን እንደምክንያት በመጠቀም ነሓሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ቃጠሎ መድረሱን በምርመራው ተረጋግጧል።

በእስረኞች የቀጠሮ ማረፊያ ቤት ዓመጽ በመቀስቀስ በአሰቃቂ ሁኔታ የሰው ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም ያደረጉ የህግ እስረኞች የአገሪቷ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ተጠያቂ እንዲሆኑም ዶክተር አዲሱ ጠይቀዋል።

በተደረገው ምርመራ “አልባሳትና ዕቃዎች የተቃጠሉት በላይተር መሆኑ ተረጋግጧል” ነው ያሉት።

ምርመራ በተከናወነበት ወቅት በእስረኞቹ ማረፊያ ቤት ውስጥ ላይተር፣ ክብሪት፣ ጫት፣ ሀሽሽ እና የኤሌትሪክ ምድጃዎች መገኘታቸውንም ገልፀዋል።

በማረሚያ ቤቶች ተቀጣጣይ ነገሮች እንዳይገቡ ማድረግ ያልቻሉት ጥበቃዎችና የማረፊያ ቤቱ አስተዳደር ሓላፊዎች ሊጠየቁ እንደሚገባ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል።

በኮሚሽኑ የምርመራ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት ሓላፊ አቶ ብርሃኑ አባዲ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ማረሚያ ቤት አቃጥሎ ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ የሚደረገው ሙከራ በሌሎች ቦታዎችም ታይቷል።

ችግሩን ለማቃለል በአጠቃላይ የአገሪቷ የማረሚያ ቤቶችና ጥበቃ ስርዓቱ በሚገባ መጠናከር እንደለበት አመልክተዋል።

ኮሚሽኑ ቃጠሎው ከመከሰቱ በፊት ባካሄደው ክትትል ተቀጣጣይ ነገሮች እንደሚገቡ ማረጋገጡን ጠቁመው፤ ችግሩ እንዲፈታ ምክረ ሃሳብ አቅርቦ እንደነበርም ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ማረሚያ ቤቱ ችግሩን ባለ ማቃለሉ “የቃጠሎው መንስኤ የሆኑ እስረኞች እድሉን ተጠቅመውበታል” ነው ያሉት።

ማረሚያ ቤቱ እስረኞቹን በዕድሜና በወንጀላቸው ክብደት ለይቶ ባለመያዙ ዓመጽ ለመፍጠር ለሚፈልጉት ዕድል እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

ሪፖርቱን ያዳመጠው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለህግ ፍትህና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ኮሚሽኑ የተሰጡትን አስተያየቶች በማስተካከል በሚያዝያ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲቀርብ ቀጠሮ ይዟል።

በቃጠሎው መንስኤ የ23 ሰዎች ህይወት ማለፉንና 15 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙ ታውቋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy