CURRENT

ለአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግንባታ ከኮንትራት ውጭ 82 ሚሊየን ብር ተጨማሪ ክፍያ ተፈፅሟል

By Admin

April 03, 2017

የፌዴራሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት በአዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ የተገነባው የአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከኮንትራት ውል በላይ የ82 ሚሊየን ብር ተጨማሪ ክፍያ መፈጸሙ ከመመሪያ ውጭ ነው በሚል ያቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ አቋቁሚያለሁ ብሏል።

ኮሚቴው በማጣራቱ ሂደት ለችግሩ ምክንያት የሆኑ አካላትን ተጠያቂ የሚያደርግ መሆኑም ነው የተገለጸው።

ከፈዴራሉ ዋና ኦዲት መስሪያ ቤት ያገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው በ2002 ዓ.ም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ የአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የግንባታ ስራ ለማከናወን ከሳንታ ኮንስትራክሽን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጋር ውል ፈጽሟል።

በውሉ መሰረት የተጨማሪ ዕሴት ታክስን ጨምሮ 12 ሚሊየን 541 ሺህ 417 ብር ክፍያ ተፈጽሟል።

ይሁንና ሪፖርቱ በግዥ መመሪያው መሰረት ለሆስፒታሉ ተጨማሪ ግንባታ የሚደረግ ከሆነ ከመጀመሪያው ውል ላይ ከሰፈረው መጠን ከ30 በመቶ መብለጥ የሌለበት ቢሆንም ዳግም በተደረገው ውል ላይ ይህን መመሪያ በሚጥስ መልኩ 120 በመቶ ጭማሪ የታየበት ውል በድጋሚ ተፈጽሟል።

ከዚህ በተጨማሪ ግንባታው ከተያዘለት ጊዜ በእጅጉ የተጓተተ መሆኑን በመግለጽ ኦዲት ተደርጎ ችግሩ ከተረጋገጠ በኋላ ክዋኔው ክትትል ተደርጎበት በድጋሚ ለተቋሙ ተልኳል ነው ያሉት የዋናው ኦዲተር የውጭ እና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ጤናው።

በድጋሚ መላክ ያስፈለገውም በመጀመሪያው ዙር ለቀረበው ሪፖርት የተሰጠው ምላሽ አጥጋቢ ባለመሆኑ ነው ብለዋል።

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የአማኑኤል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ፕሮጀክትን የሚያስተዳድረው የመሰረተ ልማት ዳይሬክተር አቶ ታደሰ የማነ፥ የሆስፒታሉ ግንባታ መዘግየትም ሆነ ተጨማሪ 82 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገው ግንባታው ከመጀመሩ በፊት የቅድመ ዝግጅት፣ የመሬት እና የዲዛይን ጥናት ባለማደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመጀመሪያው ውል ላይ ከሰፈረው ከ30 በመቶ የበለጠ ውል መፈፀሙ እና ፕሮጀክቱ የወሰደው ጊዜም የአሰራር ክፍተት እና መመሪያ የመጣስ አሰራር የታየበት ነው ብለዋል ሀላፊው።

ችግሩ በወቅቱ በነበሩ ሃላፊዎች ትዕዛዝ የተፈጠረ መሆኑንም ነው ያነሱት።

በዚህም ተጠያቂ አካላትን የማጣራት ስራ መጀመሩን የተናገሩት አቶ ታደሰ፥ ከሶስት ዳይሬክቶሬት የተዋቀረ አጣሪ ኮሚቴ ተቋቁሟል ብለዋል።

ሆስፒታሉ ዘግይቶ ቢጠናቀቅም የተለያዩ ተጨማሪ የኦፕሬሽን እና የህጻናት ህክምና መስጫ ማስፋፊያዎች ተደርጎለት ከሁለት ሳምንት በፊት የሙከራ ስራ መጀመሩንም ገልፀዋል።

ከእቅድ ውጪ አራት አመት የዘገየው ሆስፒታሉ ለግንባታ ወጪ በአጠቃላይ 156 ሚሊየን ብር ፈጅቷል።

ሆስፒታሉ የተለያዩ ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ስራ ማከናወን የሚያስችል ከውጪ ተገዘተው የገቡ ማሽኖች ተተክለውለት ነው የሙከራ ስራውን የጀመረው።

የአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በቀጣይ ሁለት ወራት በይፋ ስራውን ይጀምራል ተብሏል።