Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ለጥልቅ ተሃድሶው ስኬት

0 1,183

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ለጥልቅ ተሃድሶው ስኬት  /ታዬ ከበደ/

በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለው የጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተካሂዷል። በሁሉም ባለድርሻ አካላት ውስጥ በአስተሳሰብ ደረጃ መግባባት ላይ ተደርሷል። ይህ ውጤትንም የመጀመሪያው ደረጃ የተሃድሶው ውጤት መሆኑን ኢህአዴግና መንግስት ገልፀዋል። ታዲያ ይህን የአስተሳሰብ ግብብነት ወደ ተግባር መቀየር የገዥው ፓርቲ፣ የመንግስትና የህዝብ ሃላፊነት ነው።

በሁሉም በጥልቀት የመታደስ መድረኮች ሀገራችን ውስጥ መልካም አስተዳደርን ያሰፍናሉ የተባሉ ጉዳዩች ሁሉ እውን ሆነዋል። በተለይም ለመልካም አስተዳደር መጓደል ምክንያት የሆኑ የፌዴራልና የክልል መንግስታት አመራሮች፣ የስራ ፈፃሚዎችና የድርጅት አባላት ላይ ተገቢው የማስተካከያ እርምጃ ተወስዷል።

ይህን  ግለት ሳይረጥ ለመቀጠል ታዲያ ሁሉም የሚመለከተው አካል በጥልቅ ተሃድሶው አተገባበር ላይ እጁን ማስገባት ይኖርበታል። ይህ በሂደት እውን የሚሆነው የመታደስ ጉዞ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ሁሉም የጉዳዩ ተዋንያን በንቃት ተሳትፈው የተጀመረው ሂደት እንዳየስተጓጎል ሲያደርጉ ነው። አሊያ ግን የአንድ ሰሞን ስራ ከመሆን የሚዘል አይመስለኝም።

እንደሚታወቀው የዛሬ 16 ዓመት ገደማ ኢህአዴግ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሊያመሩ የሚችሉ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የትምክህትና የጠባብነት የዝቅጠት አደጋዎችን በተካሄደው ተሃድሶ ችግሩን መቅረፍ ችሏል። የህዝቡን ሁለንተናዊ ዕድገት ሊያሳልጡ የሚችሉ ዙሪያ መለስ ስትራቴጂዎችም በመንደፍም ዛሬ ለምንገኝበት አስተማማኝ ሰላም፣ ዘላቂ ልማትና ስር የሚሰድ ዴሞክራሲ ዕውን እንዲሆን ተደርጓል።

በእኔ እምነት ይህ የድርጅቱ ተሃድሶ ሀገራችንን አሁን ላለችበት የዕድገት ጎዳና ያበቃት ነው። በወቅቱ በአንድ በኩል ስልጣንን የኢኮኖሚያዊ ሃብትና የብልፅግና መሳሪያ በማድረግ ፀረ-ዴክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት በሚሹ ወገኖች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን የሃብት ምንጭ እንዳይሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ እንዲያብብና እንዲዳብር ብሎም የጥገኝነት አስተሳሰብ የበላይነት እንዳያገኝ በሚተጉ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ግምገማና የመድረክ ትግል መካሄዱን እናስታውሳለን።

ታዲያ በድርጅቱ ውስጥ ተፈጥረው በነበሩት በእነዚህ ሁለት ፅንፍ አመለካከቶች ዙሪያ በተካሄዱ ግምገማዊ የሃሳብ ፍጭት፤ ስልጣን የጥቂቶች የሃብት ማካበቻ እንዳይሆን እንዲሁም ዴሞክራሲና ዴክራሲያዊ አንድነት እንዲጎለብት ብሎም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ የበላይነት እንዳያገኝ የታገለው ወገን ነጥሮ በመውጣት ተሃድሶው ግቡን መትቷል፤ ውጤትም አምጥቷል።

እንደ እውነቱ ከሆነ በወቅቱ እንዲህ ዓይነቱ የተሃድሶ ርምጃ በድርጅቱ ውስጥ ባይካሄድ ኖሮ፤ ሀገራችን የምትመራባቸው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እንዲሁም ስልቶች ባልተነደፉ ነበር። በድርጅቱ ውስጥ አቆጥቁጦ የነበረው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብም በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ ጋር አብሮ ባልከደሰመ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም በአንደኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕድገት የተገኘው ሁለንተናዊ እመርታ አይታሰብም ነበር። ሁለተኛ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕድገት ዕቅድም ሊታለም አይችልም። ከሁሉም በላይ ለህዳሴያችን ጉዞ የመረባረብ ሃሳቡም አይኖረንም ነበር። እናም በወቅቱ የተካሄደው ተሃድሶ ውጤታማ ብቻ ሳይሆን፣ ዛሬ ላለንበት ሀገራዊ ቁመና ፈር የቀደደ ነው ማለት ይቻላል። ይህም ራሱን በራሱ እያረመ ለሚሄደው ኢህአዴግ ጠንካራ ትምህርት የሰጠው ይመስለኛል።

ኢህአዴግ በዚህ የተሃድሶ ዘመን የቀመረው ትምህርት ለወቅቱ ብቻ አልነበረም። ከትናንት ዛሬ የሚማርበት መድረክ እንጂ። ኢህአዴግ ተሃድሶን ለታይታ የሚያደርግ ድርጅት አይደለም። የዛሬ 16 ዓመት ገደማ የተካሄደው የተሃድሶ መስመር የዚህ አባባሌ ሁነኛ አስረጅ ነው። በወቅቱ ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የተካሄደው ግምገማ ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ዋነኛ እንቅፋት የነበሩትን አስተሳሰቦች ማስወገድና አዲስ እሳቤን  ማረጋገጥ ተችሏል።

ይህ ሁኔታም ድርጅቱ በውስጡም ይሁን እንደ ገዥ ፓርቲነቱ በሀገር ላይ ተጋርጦ የነበረውን አደጋ በአስተማማኝ ሁኔታ በማስወገድ ፊቱን ወደ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲያዞር ያደረገው ነው። በተሃድሶው ውጤትም መላው የሀገራችን ህዝቦች ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት በበጎ ገፅታ ይበልጥ ጎልታ እንድትታይ ያደረጋት ይመስለኛል። የምትከተለው በሳል የዲፕሎማሲ መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነቷን ከማረጋገጥ ባሻገር፤ ለጎረቤቶቿ ህዝቦች የሰላም ጠባቂ፣ መጠጊያና መጠለያ ሆናለች። ከራሷ አልፋ ለሌላው ተርፋለች።

እርግጥ በ1993 ዓ.ም ከተካሄደው ተሃድሶ ኢህአዴግ ውጤታማነትን አትርፏል። ይህ ውጤት ግን አሁንም በሂደት ሊጎለብቱ በሚችሉ ጉዳዩች ሳቢያ በብዙ ጥረቶች መታጀብ ይኖርበታል። ዛሬም እንደ ትናንቱ የመንግስት ስልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ዝንባሌና አስተሳሰብ ብሎም የህብረተሰቡን እርካታ ያለመፍጠር ችግር ብርቱ ችግር ሆነዋል። እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም ገዥው ፓርቲ በጥልቅ ተሃድሶ መስመር የመጓዙ ትክክለኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይመስለኝም። እናም ከ16 ዓመት በኋላ ጥልቀት ባለው ሁኔታ እታደሳለሁ ማለቱ ከሂደት እንደሚማርና ውጤቱም ምን ሊሆን እንደሚችል ስለሚያውቅ ይመስለኛል።

ኢህአዴግ ዳግም በመታደስ ሂደት ውስጥ ራሱንና የመንግስት አሰራሮችን ሲፈትሽ መነሻውም ሆነ መድረሻው ስር ነቀል ለውጥን ማዕከል ያደረገ መሆኑን በግልፅ ገልጿል። አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት “አለባብሰው ቢያርሱ፤ በአረም ይመለሱ” ዓይነት አይደለም። በእኔ እምነት መንግስት ከህዝቡ ጋር የተጀመራቸው የውይይት መድረኮች ለዚህ ትግበራ ዓይነተኛ ሚና ተጫውተዋል።

እነዚህ መድረኮች መንግስትንና ህዝቡን በቀጥታ ፊት ለፊት የሚያገናኙ እንዲሁም ያሉትን ችግሮች ከዋነኛ ተዋናዩ ማግኘት የሚያስችሉ በመሆናቸው ለስር ነቀል አፈታቱ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ በመሆናቸው መቀሜታቸው የጎላ ነው። የችግሮቹን ትክክለኛ መንስኤዎች በተገቢው መንገድ ለማወቅ፣ አውቆም ለመረዳትና የህዝቡን ፍላጎት ለማርካት መንግስት ወደ ታች ወደ ህብተሰቡ ውስጥ የሚያወርዳቸው መድረኮችም ይጠናከራሉ። የውይይቶች መጠናከር ደግሞ የታሰበውን የተሃድሶ ንቅናቄ ከግቡ የሚያደርሰው መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ይመስለኛል።

እርግጥ ውይይቶች ሁከትንና ብጥብጥን ለራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ መጠቀሚያ ለማድረግ ለሚሹ ኃይሎች የራስ ምታት ይሆናሉ። እናም ውይይቶቹንና ለውይይቶቹ መነሻ የሆነውን ጥልቅ ተሃድሶ በሁከት ሃይሎቹ አማካኝነት “አይሳካም” በማለት የሚነዛው አሉባልታ ብዙም የሚደንቅ አይሆንም። ያም ሆኖ የሁከት ኃይሎቹ በህዝቡ ውስጥ ውዥንብርና አሉባልታ በመንዛት ውይይቶቹን ለማደናቀፍ ለመጣር ቢሞክሩም ህዝቡ ራሱ የሰላሙ ባለቤት በመሆኑ ለቅጥፈታቸው ቦታ አልሰጣቸውም።

ምናልባት ‘ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል’ የሚባለው እውነት የሚመስላቸው ወገኖች ካሉ ነገር ገዥው ፓርቲ ዛሬም እንደ ትናንቱ ቃሉን የማያጥፍና ሁሌም የሚያካሂደው ተሃድሶ በውጤት የሚታጀብ መሆኑን ማስረዳት የሚገባ ይመስለኛል።

ለህዝቡ ሁሉም ጉዳዩች በጥልቅ ተሃድሶው ውይይትች ላይ በግልፅ የነስተዋል። የሁከትና የትርምስ ኃይሎች የሀገራችንን ዕድገትና ብልፅግና የማይሹ አንዳንድ የውጭና የውስጥ ሃይሎች እንጂ ከየትኛውም ብሔርና ህዝብ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው መሆኑንም ህዝቡ አሁን ካለው ግንዛቤ በላይ ይበልጥ ማስረፅ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይህም ጥልቅ ተሃድሶውን የማስቀጠል ስራ ነው።

በመሆኑም ይህ የጥልቀት እንቅስቃሴ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ቢጠናቀቅም፣ በሂደት ለሚደረገው ተግባራዊ ስራ ሁሉም ባለ ድርሻ አካል የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል። እናም በመሰረታዊ የጥልቅ ተሃድሶው ሂደት ላይ የተደረሰባቸው መሰረታዊ መግባቢያዎች ጊዜን በሂደት እንዲቀጥሉና የስራ መመሪያ እንዲሆኑ ኢህአዴግ፣ ገዥው ፓርቲና መንግስት የበኩላቸውን ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሰላም!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy