Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሊቀለበስ የማይችልበት ደረጃ የደረሰው ዴሞክራሲ

0 311

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሊቀለበስ የማይችልበት ደረጃ የደረሰው ዴሞክራሲ

ኢብሳ ነመራ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሣለኝ ሰሞኑን ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መንግሥታቸው እያካሄደ በሚገኘው በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ዙሪያ ጥያቄ ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በሰጡት ምላሽ፣ በጥልቀት የመታደሱ እንቅስቃሴ በሦስት ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር ጠቅሰዋል። እነዚህም የመንግሥትን የሥራ አፈጻጸም በብቃት ላይ በማደራጀት ውጤታማ ማድረግ፣ አስፈጻሚውን አካል የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት እንዲሁም በህዝብ ተሳትፎ ማጠናከር እና የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ትኩረት በማድረግ የሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ማሳደግ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእነዚህ ሦስት ዘርፎች ውጤታማ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል። በዚሀ ጽሁፍ የዴሞክራሲ ተቋማትን በተመለከተ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ በማሳደግ ዴሞክራሲን በማጥለቅ የተከናወኑ ተግባራት ላይ አተኩራለሁ።

ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ የመድብለ ፓርቲ የመንግሥት ሥርዓት መገንባት ከጀመረች ሁለት አሥርት ዓመታት ተቆጥረዋል። የአገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ገና ለጋ ነው። ዴሞክራሲ በአዋጅ የሚሰፍን ሥርዓት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በህዝብ ውስጥ ሰርጾ የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ባህል በመሆን የሚሰፍን ነው። እናም የዳበረ ምሉዕ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የማስፈን ጉዳይ የትውልዶችን እድሜ ይጠይቃል። አሁን የዳበረ ዴሞክራሲ አለን የሚሉት ምዕራባውያን እዚህ ለመድረስ በመቶ የሚቆጠሩ ዓመታትን ተጉዘዋል።

አሁንም ቢሆን ግን ዴሞክራሲያቸው ምሉዕ ነው ማለት አይቻልም። አሁን ባለንበት ዘመን በአሜሪካ ህዝቡ ስለአገሪቱ ፖለቲካ ያለው ግንዛቤና የፖለቲካ ተሳትፎው ሲታይ የአሜሪካ ዴሞክራሲ የሦስት መቶ ዓመታት እድሜ ያለው መሆኑ ጥያቄ ላይ ይወድቃል።

እርግጥ ህዝቡን ከአገሪቱ ፖለቲካ የመነጠል (depoliticize) ሥራ ሆን ተብሎ የተከናወነ ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክቱ ጥናቶች አሉ። ያም ሆነ ይህ ምሉዕ ዴሞክራሲን የማስፈን ጉዳይ የአመለካካት ለውጥ የማምጣትና ባህል የመገንባት ጉዳይ ስለሆነ ጊዜ ይወስዳል።

የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ በእድሜ ገና ለጋ በመሆኑ ብዙ የሚቀረው ቢሆንም፣ ሊቀለበስ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ፀድቆ ሥራ ላይ በዋለባቸው ያለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አምስት የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫዎች እንዲሁም አራት አካባቢያዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል። በሚቀጥለው ዓመት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትን ጨምሮ አምስተኛው ዙር አካባቢያዊ ምርጫ ይካሄዳል።

ምርጫ የዴሞክራሲ ምሰሶ ነው። ይህ የሆነው ምርጫ የህዝብ ብቸኛ የሥልጣን ምንጭነትና ባለቤትነት የሚገለጽበት ሥርዓት በመሆኑ ነው። ምርጫ ህዝብ በእጁ ያለውን ሥልጣን በውክልና የሚሰጥበት ሥርዓት ነው። የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ከዚህ አኳያ ስንመለከተው ቀደም ሲል እንደተገለፀው ዘጠኝ ምርጫዎች ተካሂደው ህዝብ በአብላጫ ድምጽ ሥልጣን በውክልና ሰጥቷል።

ምርጫን ከማካሄድ ባሻገር በምርጫው ላይ የሚሳተፈው ለአካለ መጠን የደረሱ ዜጎች መጠንም የአንድን አገር የዴሞክራሲውን የጥልቀት መጠን ይገልጻል። በኢትዮጵያ የተካሄዱት ምርጫዎች ላይ የሚሳተፈው ህዝብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቶ ለአካለ መጠን ከደረሱ ዜጎች ከ90 በመቶ በላይ ለመራጭነት የሚመዘገቡበት፣ ከተመዘገቡት መካከልም በተመሳሳይ ከ90 በመቶ በላይ ድምጽ የሰጡበት ሁኔታ ነው የነበረው። ይህ የህዝብ ተሳትፎ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እየጎለበተ መሄዱን ያመለክታል። ለምሳሌ በ2007 ዓ.ም በተካሄደው 5ኛ ዙር ምርጫ 36,851,461 ህዝብ ለመራጭነት ተመዝግቧል። ከዚህ ውስጥ 33,201,969 ያህሉ ድምጹን ሰጥቷል።

ይህ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ በውክልና ሥልጣን የሰጠውን መንግሥት የመጠየቅ መብት እንዳለው ጠንቅቆ ያወቀበት ደረጃ ደርሷል። ከገጠር እስከ ከተማ ህዝብ በሚሳተፍባቸው መድረኮች ላይ ህዝቡ ያለምንም ፍርሃት የመንግሥትን ችግር በይፋ ይናገራል። ይህ በተለይ ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ በተግባር የታየ እውነት ነው።

እርግጥ በድፍረት ያቀረባቸው ቅሬታዎቹ ይደመጣሉ ወይ? በወቅቱ ምላሽ ይሰጣቸዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ ሊነሳበት የሚችል ጉዳይ መሆኑ አይካድም። ሌላው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ አማራጭ ይዘው የሚቀርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች መኖር ነው። አማራጭ ከሌለ ምርጫ ትርጉም አይኖረውምና። ከዚህ አኳያ በህገ መንግሥት በተረጋገጠው የፈቀዱትን አመለካከት የመያዝ፣ የመግለጽ፣ በይፋ የማራመድ፣ ከሌሎች ጋር የመደራጀት፣ አቋምንና አመለካከትን አቅርቦ በምርጫ የመሳተፍ በህዝብ ድምጽ በሚገኝ ውክልና ልክ ሥልጣን የመረከብ መብትና ነጻነት መሠረት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደራጅተው በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። አሁንም አዳዲስ ፓርቲዎች እየተደራጁ ነው። በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ ህጋዊ እውቅና ኖራቸው የሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ60 በላይ ናቸው። እነዚህ ፓርቲዎች በፌዴራልና በክልል እንዲሁም አካባቢያዊ ምርጫዎች ላይ ሲሳተፉ ቆይተዋል።

የአገሪቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ እስከ ሦስተኛው ዙር ምርጫ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በመረጣቸው ህዝብ ልክ መቀመጫዎችን ሲጋሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ከአራተኛው ዙር ምርጫ በኋላ ግን የህዝቡ የምርጫ ተሳትፎ እያደገ ቢመጣም፣ ተቃዋሚዎች የምክር ቤቶች መቀመጫ የሚያገኙበት እድል ግን እጅግ አሽቆልቁሎ ምንም ወደሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የፌዴራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢሕአዴግና ተመሳሳይ የፖለቲካል ኢኮኖሚ አቋም ባላቸው አጋር ፓርቲዎች የተያዘ ነው። ኢሕአዴግ በሚወዳደርባቸው ኦሮሚያ፣ አማራ፣ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሲያሸንፍ ከሐረሪ ክልል ሁለት መቀመጫዎች አንዱን አሸንፏል። አንደኛው በሐረሪ ብሄራዊ ሊግ ነው የሚያዘው። በድሬዳዋም በተመሳሳይ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ) ጋር ይጋራል።

ከዚህ ውጭ በአፋር፤ የአፋር ብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (የአብዴፓ) እና የአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (አህዴድ)፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ፤ የኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ)፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ)፣ በጋምቤላ፤ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋህዴን)፤ በሐረሪ፤ የሐራሪ ብሄራዊ ሊግ (ሃብሊ) ናቸው ያሸነፉት። ከጋምቤላ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች በርካታ ፓርቲዎች ለምርጫ ቀርበዋል። ለምሣሌ በአምስተኛው ዙር ምርጫ በትግራይ 6፣ በአፋር 9፣ በአማራ 13፣ በኦሮሚያ 16፣ በኢትዮጵያ ሶማሌ 6፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ 5፣ በደቡብ 21 ፓርቲዎች ነበር የተወዳደሩት። በጋምቤላ 1 ፓርቲ ብቻ ነው የተወዳደረው። ይህ እንደ ጉድለት ሊታይ የሚችል ነው።

በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ዋነኛ መገለጫ የሆነው የምርጫ ሥርዓት ሂደት በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ከህዝብ ተሳትፎም፣ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎም አኳያ ችግር የለበትም። የምርጫውን ፍትሃዊነትና ተአማኒነት በተመለከተ፣ ቅሬታዎች የሚነሱ ቢሆንም በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፉ ችግሮች የቀረበቡበት ሁኔታ ግን የለም። ከአገሪቱ ዴሞክራሲ ለጋ መሆን አንጻር የተፈጠሩ ችግሮች እንኳን ቢኖሩ በ50 + 1 ቀላል አብላጫ የተገኘውን ውጤት ሊቀይሩ የሚችሉ አይደሉም። በአጠቃላይ ከላይ የተገለጹት እውነታዎች የአገሪቱ ዴሞክራሲ ሊቀለበስ የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ያመለክታሉ።

ያም ሆኖ ለምሣሌ በ5ኛው ዙር ምርጫ 58 ፓርቲዎች ተወዳድረው፣ በየክልሉ አንድ አንድ ፓርቲ ብቻ አሸንፎ ምክር ቤቱ ተመሳሳይ አቋም ባላቸው ኢሕአዴግና አጋር ፓርቲዎቹ ብቻ መያዙ ግን ጤናማ ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም። በምርጫው ላይ የተሳተፉት ሁሉም ፓርቲዎች ድምጽ አግኝተዋል። ለምሣሌ ኢሕአዴግ በተወዳደረባቸው ክልሎች ያገኘው ድምጽ 84 ነጥብ 2 በመቶ ነው። ይህ ድምጽ በቀላል የአብላጫ ድምጽ ሥልጣን መረከብ ቢያስችለውም የተቀረውን 16 በመቶ ድምጽ ያገኙ ፓርቲዎች አንድም መቀመጫ ሳያገኙ ነው የቀሩት። ኢሕአዴግ በተወዳደረባቸው ክልሎች ኢሕአዴግን ያልመረጠ ህዝብ በቁጥር ከ5 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ነው። ይህን ያህል ህዝብ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድምጹን የሚያሰማለት ወኪል አላገኘም ማለት ነው። ይህ ውክልና የሌላቸው በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ያሉበት ሁኔታ የፖለቲካ ምህዳሩ ስፋት በሚፈለገው ልክ እንዳይሆን አድርጎታል። ይህ ደግሞ ቅሬታ ፈጥሯል።

እናም የፖለቲካ ምህዳሩን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ማስፋት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታ ነው። ባለፈው ዓመት ተቀስቅሶ የነበረውን ሁከት ከለኮሱ የህዝብ ቅሬታዎች አንዱ ይህ የፖለቲካው ምህዳር በሚፈለገው ልክ አለመስፋት መሆኑን የሚያመለክቱ እውነታዎች አሉ። ኢሕአዴግና መንግሥት አገሪቱን ከገጠማት ፈተና ለማውጣት በጥልቀት የመታደስ እርምጃ ለመውሰድ ሲነሱ፣ ይህ መታደስ ከሚመለከታቸው ጉዳዮች አንዱ የአገሪቱን ዴሞክራሲ ማጥለቅ ነው። በሌላ አነጋገር የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ነው። በጽሁፌ መግቢያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ሰሞኑን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በጥልቀት የመታደሱን እንቅስቃሴ አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ ትኩረት በማድረግ የሲቪክ ማህበራትና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ማሳደግ በሚል የጠቀሱት ይህንን ነው።

የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ ለማስፋትና ሁሉም ድምጾች የሚወከሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ከተወሰዱት ርምጃዎች መካከል ተጠቃሹ በኢሕአዴግና በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተጀመረው የድርድር ሂደት ነው። ይህ ድርድር የመጀመሪያውን ምዕራፍ ጨርሶ ወደዋናው ድርድር ለመሸጋጋር ቀናት ቀርተውታል። በዚህ ኢሕአዴግን ጨምሮ በ22 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተጀመረው ድርድር ሦስት ፓርቲዎች (የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ  (መድረክ)፣ የመላው አማራ ህዝብ ድርጅት (መአህድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ በራሳቸው ውሣኔ ከድርድሩ ራሳቸውን ሲያገሉ፣ የተቀሩት 19ኙ በ12 አጀንዳዎች ላይ ተስማምተው በ9ኛ ስብሰባቸው “የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር አሠራር ደንብ” የተሰኘ ሰነድ አጽድቀዋል። የድርድሩ እያንዳንዱ ሂደት ለህዝብ ሲገለጽ ስለቆየ ወደኋላ ተመልሼ ማስታወስ አልፈልግም።

ድርድር ለማድረግ የተስማሙት ፓርቲዎች በ9ኛ ስብሰባቸው ከመካከላቸው ድርድሩን የሚመሩ አባላት መርጠዋል። ፓርቲዎቹ በዘጠነኛ ዙር ስብሰባቸው አቶ አሰፋ ኃብተወልድ ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) የአደራዳሪው ሰብሳቢ፣ አቶ ዋስይሁን ተስፋዬ ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የአደራዳሪው ተቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ፣ አቶ አለማየሁ ደነቀ ከአዲሱ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) የአደራዳሪው ምክትል ሰብሳቢ አድርገው መርጠዋል። ፓርቲዎቹ ሦስት አባላት ያሉት የአጀንዳ አደራጅና የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ኮሚቴም አዋቅረዋል። ፓርቲዎቹ ኢሕአዴግ ድርድሩን የጠራ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ በአጀንዳ አደራጅና የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ኮሚቴ ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፍ ተስማምተዋል። አቶ ገብሩ ብርሃኑ ከኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴሃግ) የኮሚቴው ሰብሳቢ ሆነው ሲመረጡ፣ አቶ አስመላሽ ገብረሥላሴ ከኢሕአዴግ እንዲሁም አቶ መላኩ መሰለ ከኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) የኮሚቴው አባላት ሆነው ተመርጠዋል።

ፓርቲዎቹ በድርድር ደንቡ መሠረት ከሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ በ15 ቀናት ውስጥ የመደራደሪያ አጀንዳዎቻቸውን ለአጀንዳ አደራጅና የሚዲያና የኮሙዩኒኬሽን ኮሚቴ ያስገባሉ። አጀንዳቸውን አስገብተው ካበቁ በኋላ አደራዳሪ ኮሚቴዎቹ ቀን በመወሰንና ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጥሪ በማድረግ ሥራቸውን ይጀመራሉ።

ይህ ከላይ የተገለጹት አጠቃላይ እውነታዎች ገና ሁለት አሥርት ዓመታትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ መጎልበት ቢቀረውም የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ መድረሱን ያመለክታሉ። ካሁን ወዲያ በኢትዮጵያ ፍጹም አምባገነን ሥርዓት ሊመሠረት አይችልም። ባለፉት ሃያ ዓመታት ዴሞክራሲን ያጣጣመው ህዝብ ካሁን በኋላ አምባገነናዊ ሥርዓትን ሊቀበል አይችልም። እናም ዴሞክራሲውን ይጠብቀዋል፤ ያጎለብተዋልም።

በተለይ በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እያካሄዱት ያለው ድርድር በራሱ የዴሞክራሲው መጎልበት ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው በሠላማዊ ሂደት ብቻ መሆኑን፣ ከዚህ ያፈነገጡ ፓርቲዎች አካሄድ ተገቢ አለመሆኑን ሊገነዘብ ይገባል። በፖለቲካ ፓርቲዎች በመከናወን ላይ የሚገኘው የፖለቲካ ምህዳሩን ወቅቱ በሚጠይቀው ልክ በማስፋት ዴሞክራሲውን የማጎልበት ተግባር ስኬታማ እንዲሆን ህዝብ ሠላማዊ ድርድሩን የመረጡ ፓርቲዎችንና አጠቃላይ ሂደቱን ሊያበረታታ ይገባል። ይህን ሠላማዊ ሂደት ለማሰናከል የሚነዙ ውዥንበሮችንም በጥንቃቄ አጢኖ ራሱን ከመደናገር ሊጠብቅ ይገባል። ዴሞክራሲ የሚጎለብተው በሠላማዊ ሂደት ብቻ ነውና።

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy