Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሕገ መንግስትና የሕግ የበላይነት

0 635

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሕገ መንግስትና የሕግ የበላይነት /ታዬ ከበደ/

በህግ ካለተደነገገ በስተቀር በየትኛውም ሀገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ የህግ የበላይነትን በመፃረር እንዳሻው ሊኖር አይችልም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በህግና ስርዓት የሚመራ ካልሆነ የትኛውም ወገን የመኖር ዋስትና ሊኖረው አይችልም። በመሆኑም ማንኛውም ዜጋ የሚንቀሳቀሰው ህግ ባለበት ሀገር ውስጥ ነውና ህገ-ወጥ ተግባርን ከከወነ የህግ የበላይነት ተፈፃሚ እንደሚሆንበት ማወቁ ተገቢ ይመስለኛል።

ህገ መንግስቱ የህግ የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲል ከህግ አግባብ ውጪ ስልጣን መያዝ የተከለከለ ነው። ይህም የህገ መንግስቱን አንቀፅ 56 የሚመለከት ነው። በዚህ አንቀፅ መሰረት በምክር ቤተ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅት የፌዴራሉን መንግስት የህግ አስፈፃሚ አካል እንደሚያደራጁና እንደሚመሩ ተገልጿል።

ይህም የትኛውም አካል ህገ መንግስቱ ላይ ከተደነገገው ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ውጪ ነፍጥ አንግቦ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመጣል የሚያደርጋቸው ማናቸውም ተግባራት ህገ ወጥ መሆኑን ያሳያል። በመሆኑም ከህገ መንግስቱ አኳያ በዚህ ተግባር ላይ የተሰለፉ ማናቸውም የፖለቲካ አሊያም የሽብር ድርጅቶች ህገ ወጥ ናቸው። ከእነርሱም ጋር የሚደረግ ማናቸውም ግንኙነት ወይም የእነርሱን አጀንዳ በማራመድ ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመናድ የሚደረጉ ጥረቶች የህግ የበላይነትን መፃረር እንደሆነ ግንዛቤ ሊያዝ የሚገባ ይመስለኛል።

ለአብነት አንድ ሰው በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ውስጥ በአሸባሪነት የተሰየሙትን ኦነግንና ግንቦት ሰባት የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖችን ከደገፈ ወይም የእነርሱን ዓላማ ለማሳካት በተለያዩ መንገዶች ከተንቀሳቀሰ ከህግ የበላይነት ጋር እየተጋጨ መሆኑን ግንዛቤ ሊይዝ ይገባል። ምክንያቱም እነዚህ የሽብር ቡድኖች ህገ መንግስቱን ተፃርረው ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ እየተንቀሳቀሱ በመሆናቸው ነው። እናም እነርሱን አለመደገፍ የህግ የበላይነትን ማክበር ሲሆን፣ የእነርሱን ህገ ወጥ ዓላማ በማናቸውም መንገድ መደገፍ ደግሞ የህግ የበላይነትን መፃረር መሆኑን መረዳት ይገባል።

የህግ የበላይነት ልዕልና ሊጠበቅ ይገባል። የህግ የበላይነት ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆኑ የዜጎች መብቶች ሊሸራረፉ ይችላሉ።

የመብት መሸራረፎች ደግሞ አንዱ እንዳሻው እንዲፈነጭ የሚያደርገው ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ህግና ስርዓትን አክብሮ እንዲንቀሳቀስ ያደርገዋል። ይህም ህግና ስርዓትን የሚያከብረው ዜጋ ሌላውን በመመልከት ወደ ተሳሳተ መንገድ ሊያመራ ይችላል። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍም የህግ የበላይነት ልዕልና ገቢራዊ መሆን አለበት። በመሆኑም ህግና ስርዓትን የማስከበር ተግባር በሀግ አስፈፃሚው አካል በሚፈፀምበት ወቅት የተለየ ትርጓሜ ሊሰጠው አይገባም።

እንደሚታወቀው የኢፌዴሪ ህገ መንግስት በ106 አንቀፆች የተዋቀሩ መብቶችንና ግዴታዎችን የያዘ ሰነድ ነው። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ስለ የህግ የበላይነት የሚያወሳው የህገ መንግስቱ ክፍል ነው፤ በአንቀዕ ዘጠኝ ላይ። በዚህ አንቀፅ ስር ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ መሆኑ፤ ማንኛውም ህግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት እንደሆነ፤ ማንኛውም ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌሎች ማህበራት እንዲሁም ባለስልጣኖቻቸው ህገ መንግስቱን የማክበርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ የመሆን ኃላፊነት እንዳለባቸው ይደነግጋል። እንዲሁም በዚህ ህገ መንግስት ከተደነገገው ውጭ በማናቸውም አኳኋን የመንግስት ስልጣንን መያዝ የተከለከለ መሆኑን ያስረዳል።

በአንቀፁ ስር የተደነገጉት ጉዳዩች የህግ የበላይነትን የሚገልፁ ናቸው። ይህ የህግ የበላይነት ሁኔታ በሁሉም ሀገር ውስጥ የግድ መኖር ይኖርበታል። ምክንያቱም የህግ የበላይነት በሌለበት ሀገር ውስጥ ማንኛውም ሰው በሰላም ወጥቶ ሊገባ አይችልም። መብት ሰጪዎችና ነሺዎች ጉልበተኞች ይሆኑና ስርዓት አልበኝነት ይነግሳል። ጉልበተኞቹም ሌሎች ዜጎችን እንዳሻቸው በማድረግ የባሪያና ሎሌ ስርዓት ይፈጥራሉ።

ስርዓት አልበኝነት ሲገነግንም ህግን አክብሮ የሚንቀሳቀስ ዜጋ አይኖርም። ሁሉም በየፊናው እየሮጠ የራሱን የበላይነት ለማስጠበቅ ለማረጋገጥ ይጥራል። ይህ ሁኔታም አንድን ሀገር የነበረበትን ሰላማዊ ምህዳር በማወክ በሁከት እንዲታመስ ያደርገዋል። በሰላም ውስጥ ኖሮ ሀገርን ማበልፀግና ወደ ተሻለ ህይወት መረማመድ ያበቃለታል። እናም ይህን ሁኔታ ለመከላከልና ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የህግ የበላይነት መኖር የግድ ይላል።

ይህም የህግ የበላይነትን አለማረጋገጥ ህገ መንግስቱን መፃረር መሆኑን የሚያመላክት ነው። ምክንያቱም ህገ መንግሰቱ የህጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ መጠን፤ እርሱን ተከትለው የሚወጡ አዋጆችን ተፈፃሚ አለማድረግ መልሶ ህገ መንግስቱን መቃወም ነው። ይህ እንዲሆን ደግሞ አስፈፃሚውም አካል ሆነ ማንኛውም ዜጋ መፍቀድ ያለበት አይመስለኝም። የህግ የበላይነት ዕውን እንዳይሆን መፍቀድ ነውና። የህግ የበላይነትን መፃረር ስርዓት አልበኝነትን የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር፤ ህጎች ለሁሉም ዜጎች እኩል እንዳይሰሩ ያደርጋል። እናም ‘ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው’ የሚለውን ህገ መንግስታዊ መርህ ገቢራዊ ለማድረግ የህግ የበላይነት በማያሻማ ሁኔታ መረጋገጥ ይኖርበታል።

የህግ የበላይነት መከበር ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ብሎም ልማትን ለማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የህግ የበላይነት ከሌለ ሰላም የሚባልን ነገር ማሰብ አይቻልም። ሰላም ከጠፋ ደግሞ ስለ ልማትና ዴሞክራሲ ማሰብ አይቻልም። ፀረ-ልማትዊነትና ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት ቦታውን ይረከባሉ። ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ ሰላምን፣ ልማትንና ዴሞክራሲን የህልውናው ጉዳይ ላደረገ ሀገር አሜኬላ እሾህ መሆኑ አያጠያይቅም።

እርግጥ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ባህል ግንባታ ሂደት ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል፤ አስተማማኝ ሠላም የሰፈነበት ምህዳርን መፍጠር የግድ ነው። ምክንያቱም ሀገራችን ፈጣን ልማትን ማምጣትና ከተመፅዋችነት መላቀቅ ብሎም ዴሞክራሲን መገንባት የሞት ሽረት ያህል የህልውና ጉዳይ አድርጋ ስለያዘችው ነው። ታዲያ ሰላምን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ለብሔራዊ ደህንነቷ ስጋት የሆኑ እንቅስቃሴዎችን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላት ዘንድ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ የሚኖርባት ይመስለኛል።

የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ሰላምን እንጎናፀፋለን። ሰላምን ስንጎናፀፍ ደግሞ የምናውዳቸውን የልማትና የዴሞፐክራሲ ስራዎችን ዕውን እናደርጋለን። ህጎች ለአንዱ የሚሰሩ ለሌላው ደግሞ የማይሰሩ ለሆኑ አይችሉም። ሁላችንም በህግ ፊት እኩል እንስተናገዳለን። የህግ የበላይነት ሲኖር ሁላችንም ከሚገኘው ሀገራዊ ጥቅም ተካፋዩች እንሆናለን። እናም እንደ ማንኛውም ዴሞክራሲን የሚከተል አገር በሕገ መንግስቱ መሰረት የሕግ የበላይነትን ማክበበር ህግና ስርዓትን ማክበር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ሰላም!

  

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy