CURRENT

ማህበራዊ ድረ ገጽ እና ወጣቱ

By Admin

April 28, 2017

ኢንተርኔት ማለት ፌስቡክና ሌሎች ማህበራዊ ድረ ገጾች ብቻ እስከሚመስሉ አብዛኛው ወጣቶች በእነዚህ ተጠቃሚ መሆናቸው ይስተዋላል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አብዛኛው የእዚህ ማህበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚ ከ25 እስከ 34 ዓመት የዕድሜ ክልል ይገኛሉ፡፡ በፈረንጆቹ ጥር 2017 በተሰራ ጥናት በዓለም በየዕለቱ 1 ነጥብ 15 ቢሊዮን ያህል ሰዎች በሞባይላቸው ይህንን ማህበራዊ ድረ ገጽ ይጎበኛሉ። እንደ ጥናቱ ይህን ማህበራዊ ድረ ገጽ ለንባብ ከማዋል አንጻር በአሜሪካን አገር በየዕለቱ አምስት ገጽና ከዚያ በላይ የሚሆን ጽሁፍ ይነበብበታል፡፡

በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የንባብ ባህል እየቀዘቀዘ ነው የሚል መከራከሪያ ቢነሳም፤ ማህበራዊ ድረ ገጾችን የሚጎበኙ ብዙ ወጣቶች በእዚያ የሚነበቡ ነገሮች ስለሚገኙ እያካካሱት ነው ብለው የሚሞግቱም አይጠፉም። ብዙ ጠቃሚ መረጃዎችም አሉ በማለት ይገልጻሉ። አንዳንዶች ደግሞ ማህበራዊ ድረ ገጾች ከመጽሐፍና ከሌሎችም የህትመት ውጤቶች ከሚገኙ ንባቦች ጋር አይመጣጠኑም በማለት ይከራከራሉ። የሚገኙትም መረጃዎች ቢሆኑ ተጨባጭነታቸው አጠራጣሪ ነው ይላሉ።

ማህራዊ ድረ ገጾች ትክክለኛ መረጃዎችን፣ ታሪክን፣ ባህልን በማስተዋወቅ ለብዙ ተከታዮች እንዲሰራጩ ያደርጋሉ። የሚነበቡ ነገሮችም በብዛት ይገኝባቸዋል ከሚሉት ወጣቶች መካከል የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋዜጠኛ የሆነው የሺሀሳብ አበራ ይገኝበታል፡፡

ጋዜጠኛ የሺሀሳብ አበራ ሀሳቡን ሲያብራራ፤ ወደ ማህበራዊ ድር ገጽ የሚልካቸውን መረጃዎች ከመጻህፍት ወይም ከሌላ ትክክለኛ ምንጭ ሳያረጋግጥ አይጠቀማቸውም፡፡ ምክንያቱም መረጃዎቹ በአንድ ጊዜ ለብዙ ሰዎች ይደርሳሉ፡፡ በገጹ ላይ ያላነበበው ሰው እንኳን ካነበቡት ሰዎች ሊሰማ ይችላል፡፡በመሆኑም በኢንተርኔት የሚሰራጩ ጽሁፎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸው ይገልጻል፡፡

ከዜናዎች በተጨማሪ ሌሎች መጣጥፎችን በማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ለማስቀመጥ መጻህፍትን፣ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን ያነባል፡፡ እንደ የሺሀሳብ እምነት መጻሕፍት፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች በጥንቃቄ የተሰሩና ተጠያቂነት ያለባቸው በመሆኑ እነሱን በምንጭነት መጠቀም የነገሩን እውነትንት ያረጋግጣል፡፡

‹‹ኢንተርኔት አንድን ነገር በቀላሉ ፈልጎ ለማግኘት ምቹ ነው። አንድ ስም እንኳን ባስገባ በዚያ ስም የሚጠሩና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮችንም ያመጣልኛል፤ ለመጻፍም ሆነ ለማንበብ ምቹ ነው›› የሚለው የሺሀሳብ ኢንተርኔት ግን ራሱን ችሎ የንባብ ምንጭ መሆን እንደማይችል ይነገራል፡፡ የብዙ ነገሮች መነሻዎች ቀድም ሲል በ «ሃርድ ኮፒ» የተጻፉት ናቸው፡፡ እነርሱን እንደማጣቀሻ ሳይጠቀሙ በኢንተርኔት ብቻ ሙሉ ነገር ማግኘት እንደማይቻል ያምናል፡፡

የሺሀሳብ በራሱ ገጽ ላይ ለሚለቃቸው ነገሮች ህጋዊ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ተጠያቂነት እንዳለበት ያምናል፡፡ ‹‹በኔ ገጽ ላይ የተለቀቀው መረጃ ሀሰት ሆኖ ቢገኝ ብዙ ሰው ውሸታም ያደርገኛል፤ በሰዎች ዘንድ ያለኝን ክብር ይቀንስበኛል›› ይላል፡፡ ማህበራዊ ድረ ገጽ በባህሪው ህጋዊ ተጠያቂነት ባይኖረውም ማህበራዊ ተጠያቂነት ግን እንዳለበት ያምናል፡፡

‹‹ማህበራዊ ድረ ገጾች በባህሪያቸው ለአዝናኝና ለአጫጭር ነገሮች የሚመቹ ናቸው›› በሚለው ሀሳብ አይስማማም፡፡ እንደ እርሱ አገላለጽ ይህ የሰዎች ባህሪ እንጂ የማህበራዊ ድረ ገጾቹ አይደለም፡፡ ብዙ ተለፍቶባቸው የተጻፉ የጥናትና ምርምር ሥራዎችንም መጠቀም ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ገጾች ላይ የሚገኙ ሀሳቦች በራሳቸው ለጥናትና ምርምር መነሻ እንደሚሆኑም ያምናል፡፡

ሌላኛው የፌስቡክ ተጠቃሚ ወጣት ጌጥዬ ያለው ይባላል፡፡ ማህበራዊ ድረ ገጽን የሚጠቀመው እንደ የስነ ጽሑፍ መረጃ የሚገኝበት ምንጭ በማድረግ ነው፡፡ ብዙ የአጻጻፍ ስልቶችንና አዳዲስ ሀሳቦችን ያገኝበታል፡፡ ለዚህም የሚከታተላቸው ማህበረዊ ድረ ገጾች የተመረጡና ጠቃሚ ነገር የሚያገኝባቸውን ነው፡፡

በሌላ በኩል ማህራዊ ድረ ገጽ የሚጠቀመው አዳዲስ መረጃዎችን ለማግኘት ነው፡፡ እንደ ጌጥዬ እምነት ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ያየውን ነገር ሀሰት ነው ብሎ አያልፍም፤ እውነት ነው ብሎ አይደመድምም፡፡ በተለይም እንደ ጉዳዩ አጠራጣሪነት እውነት ነው ወይስ ሀሰት የሚለውን ለማጣራት መደበኛ መገናኛ ብዙኃንን ይከታተላል፡፡ ‹‹ማህበራዊ ሚዲያ በመደበኛው ሚዲያ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል›› በሚለው ሀሳብ ጌጥዬ አይስማማም፡፡ እንዲያውም ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የራሱን ተሞክሮ ምሳሌ በማድረግ ይናገራል፡፡ አንድ ነገር ማህበራዊ ድር ገጽ ላይ ካነበበ ያንን ነገር ለማጣራት መደበኛ መገናኛ ብዙኃንን ይከታተላል፡፡ ‹‹መደበኛ ሚዲያዎች በኤዲቶሪያል ፖሊሲ የሚተዳደሩ ናቸው፤ ተጠያቂነት አለባቸው፡፡ ማህበረዊ ሚድያ ላይ ግን በሰሚ ስሚ ሊለቅ ይችላል›› የሚለወቅ ጌጥዬ ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ መነጋገሪያ የሆነ ነገር ጋዜጣ፣ ሬዲዮና ቴሌቭዥን እንዲከታተል ያደርገዋል እንጂ ከእነዚያ መገናኛ ብዙሃን አያርቀውም፡፡

‹‹መደበኛ ሚዲያዎች የሚመለከተውን ሰው አነጋግረው፣ በባለሙያ የተብራራና ታማኝነት ያለው መረጃ ይዘው ስለሚመጡ ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ያየሁትን ነገር ያረጋግጡልኛል›› የሚለው ጌጥዬ ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ የሚታይ ነገር የአንድ ግለሰብ ሀሳብ ሊሆንም ስለሚችል ሀሰት ወይም እውነት ብሎ እንደማይቀበል ይናገራል፡፡

ማህበራዊ ድረ ገጽን አንዳንዶች ለዜናና ወቅታዊ፣ አንዳንዶች ለአዝናኛ ነገሮች፣ ለስነ ጽሁፋዊ ሀሳቦች ይጠቀሙበታል፡፡ አጠቃቀም እንደየ ተጠቃሚው ይለያያል፡፡ ወጣት ተመስገን አሰፋ እንደሚለው ደግሞ ማህበራዊ ድረ ገጽን ለወቅታዊ ነገሮች ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ከጓደኛ ለመገናኘትም ይጠቀምበታል፡፡ ስልክ ተደዋውሎ ብዙ ወጪ ከማውጣት በቀላሉ በእነርሱ ማወራት እንደሚችል ይናገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከማያውቃቸው ሰዎች ጋር ይተዋወቃል። የተለያዩ የስራና ማስታዎቂዎችንም ማግኘት እንደሚችል ይገልጻል፡፡

አብዛኛው የማህበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚ ወጣቱ ቢሆንም ከነዚህ ውስጥ የትኞቹ ወጣቶች በብዛት ይጠቀሙ ይሆን? የዓለም የዕርቅና ሰላም ግብረሰናይ ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ጸጋዘአብ ለምለም ወጣቶችንና ኢንተርኔትን በተመለከተ በተለያዩ መድረኮች የዳሰሳ ጥናቶችን አቅርበዋል፡፡ አቶ ጸጋዘአብ እንደሚሉት፤ አብዛኞቹ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በትምህርት ላይ ያሉ፣ ትምህርት ጨርሰው በሥራ ፍለጋ ላይ ያሉና በመንግሥት ተቋማት ላይ የተቀጠሩ ሲሆኑ በግል ተቋማት ውስጥ የሚሰሩና በንግድ ሥራ የተሰማሩት እምብዛም የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ይገልጻሉ፡፡

በተደረገው የዳሰሳ ጥናት በተለይም በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡

አቶ ጸጋአዘብ በኢንተርኔት አጠቃቀም ላይ የተዛባ አረዳድ እንዳለም ይገልጻሉ፡፡ ኢንተርኔት ማለት ማህበራዊ ድረ ገጽ ብቻ የሚመስላቸው እንዳሉ በመግለጽ ‹‹አብዛኛው ወጣት የእነርሱ ተጠቃሚ ነው›› ይላሉ፡፡ ኢንተርኔት በወጣቶች ላይ አሉታዊ ጎን ቢኖረውም ለንባብ እንደሚያነሳሳም ይገልጻሉ፡፡ ብዙ ማንበብ የማይወዱ ወጣቶች እንዲያነቡ አድርጓል፤ ኢንተርኔት በራሱ ጊዜ የሚነበቡ ነገሮችን ስለሚያመጣ ለማንበብ እንደሚያነሳሳም ያብራራሉ፡፡ የኢንተርኔትን ጠቃሚነትና ጎጂነት ከእሳት ጋር ያነጻጽሩታል፡፡ ‹‹እሳት እንደ አያያዛችን የሚጠቅምም የሚጎዳም እንደሆነ ሁሉ ኢንተርኔትም እንዳያያዛችን ነው›› ይላሉ፡፡

በዚህ በቴክኖሎጂ ዘመን የመገናኛ ብዙሃን ራሳቸው እንኳን የማህበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ዜናዎቻቸውን በማህበራዊ ድረ ገጽ ያሰራጫሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮምኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት አቶ ተሻገር ሽፈራው እንደሚሉት መገናኛ ብዙሃን ቀደም ብሎም አንዱ በአንዱ ላይ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ መጀመሪያ ጋዜጦች ነበሩ፡፡ ሬዲዮ ሲመጣ ጋዜጦች የተወሰነ ጊዜ አንባቢ ያጣሉ፡፡ ቴሌቭዥን ሲመጣም ሬዲዮ ለተወሰነ ጊዜ አድማጭ ያጣል፡፡ እየቆየ ሲሄድ ግን የየራሳቸው የሆነ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

‹‹ይህ ሁኔታ ብዙም አይቀጥልም፤ እንዲያውም ጋዜጦች በኋላ የበለጠ ተወዳጅ እየሆኑ መጥተዋል›› ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ድረ ገጽ ላይ ጋዜጣ የሚያወጣውን ነገር በሙሉ ማግኘት አይቻልም፡፡ በስክሪን ላይ ማንበብም በጣም አድካሚ መሆኑ ታወቀ፡፡ በዚህም ምቹነቱ እንደ ወረቀት ሊሆን አልቻለም፡፡ በኢንተርኔት ምክንያት ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ይጠፋሉ ማለት እንደማይቻል መምህር ተሻገር ይገልጻሉ፡፡

ወጣቶች የማህበራዊ ድረ ገጽን አጠቃቀም በአግባቡ በመመራት ለሚፈልጉት አላማ መዋል ይገባቸዋል። እየቀዘቀዘ መጥቷል የሚባለውን የንባብ ባህል የሚያካክሱ መረጃዎች በኢንተርኔት እንደሚገኙ እሙን ቢሆንም ጥቅምና ጉዳቱን በማመዛዘን መጠቀም አለባቸው።

ዋለልኝ አየለ