Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ማዕቀብና ሻዕቢያ

0 356

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ማዕቀብና ሻዕቢያ /ዳዊት ምትኩ/

ሰሞኑን የኤርትራ መንግስት በመንግስታቱ ድርጅት አዲስ ማዕቀብ እንደተጣለበት እየተሰማ ነው። የማዕቀቡ ምክንያትም ከሰሜን ኮሪያ የመሳሪያና የወታደራዊ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎቹን በመግዛቱ ነው። ይህ ሁኔታም የአቶ ኢሳይያስን መንግስት ለሶስተኛ ጊዜ በማዕቀብ ውስጥ እንዲዘፈቅ ያደረገው ነው።

በእኔ እምነት የትኛውም ዓይነት ማዕቀብ ሻዕቢያን አይመልሰዋል ብዬ ባላስብም፤ የአስመራው መንግስት ግን ከዓለማቀፉ ማህበረሰብ ክልከላዎች ጋር ዘወትር መጋጨቱ የለመደው ተግባሩ ነው። እናም የመንግስታቱ ድርጅት በተለያዩ ወቅቶች ያወጣቸውን ማብራሪያዎች ተመርኩዤ ቀደምት ማንነቱን አመለከታለሁ። የመረጃዬ ምንጭ የመንግስታቱ ድርጅት የሶማሊያንና የኤትራን ጉዳይ የሚቃኘው አጣሪ ቡድን በተለያዩ ወቅቶች የለቀቃቸው ሪፖርቶች ናቸው።

እንደሚታወቀው ኤርትራ በይፋ ከኢትዮጵያ ተነጥላ ነጻነቷን ያወጀችው የወታደራዊው መንግሥቱ ኃይለማርያም አገዛዝ እ.ኤ.አ በ1991 ያስወገደውን የ30 ዓመታት የነጻነት ትግል ተከትሎ በ1993 በተደረገው ህዝበ ውሳኔ ነው፡፡ በዓለም ባንክ ግምት 5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ህዝብ እንዳላት የሚነገርላት ኤርትራ፤ ከዓለማች በኋላ ቀር ሀገሮች ተርታ ትፈረጃለች፡፡ ኤርትራ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላት ግንኙነት በፀብ አጫሪነት የተሞላ ነው፡፡

ድንበሯን በማካለሉ ሂደት ከኢትዮጵያ፣ ከየመንና ከጅቡቲ ጋር ጦርነት ከፍታለች፡፡ ከሱዳን ጋር ያላት ግንኙነትም ቢሆን ውስብስብና ሚናውን ያልለየ ነው፡፡ በጥር 2009 የሶማሊያ ታጣቂ ተቃዋሚ ኃይሎችን በመርዳትና ከጅቡቲ ጋር በፈጠረችው የድንበር ግጭት በቀረበባት ክስ ምክንያት የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራን አስመልክቶ በቁጥር 1907 (2009) የማዕቀብ ውሳኔ አስተላልፋል። ሁለተኛውንም ማዕቀብ ከአራት ዓመታት በፊት ጥሎባታል።

እነዚህ ማዕቀቦች በኤርትራ ላይ አጠቃላይ የጦር መሣሪያ እገዳን (መሸጥ፣ መለወጥ፣ መጠቀም) አለመቻልን ያወጀ ሲሆን፤ በቀጣናው ያሉ ታጣቂ ኃይሎችን እንዳትረዳም የሚከለክል ነው፡፡ ህጉን የሚጥሱ አካላት የጉዞና በባንክ ያለ ገንዘባቸውን ያለማንቀሳቀስ እገዳ ይጥልባቸዋል፡፡ በተጨማሪም በሁለተኛው ማዕቀብ የፀጥታው ምክር ቤት የአስመራው አስተዳደር ውጪ ከሚገኙ ዜጎቹ የሚሰበስበውን የሁለት ከመቶ የቀረጥ ታክስ እንዳይወስድ የሚያግድ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡

ኤርትራ በቀጣናው ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ያላትን ንክኪ ጨምሮ የውጭና የደህንነት ፖሊሲዋ ከ1998 እስከ 2000 ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር ካደረገችው ጦርነት አንጻር ብቻ ሊጤን የሚገባው ይመስላል፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አካላይ ኮሚሽን ውሳኔን ኢትዮጵያ አለማክበሯ፣ የሲቪልና ወታደራዊ ሃይሎች ዛሬም ድረስ በአካባቢው እንደሰፈሩ መቅረታቸው፣ ኤርትራ ኦብነግንና ኦነግን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ታጣቂ ሃይሎችን ለመርዳቷ ምክንያት አድርጋ ታቀርባለች፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ማድረጋቸው የኤርትራን ፖለቲካዊና የልማት መዘውር አቅጣጫውን እንዲቀይር አስገድዶታል፡፡ ኤርትራ በ1997 ያረቀቀችው ህገ – መንግስት እንዲቆም አድርጎታል፡፡ ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል፡፡

የኤርትራ ገዥው ፓርቲ ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ (ህግደፍ) ራሱን ወደ ወታደራዊ ግንባር ቀይሮ፤ የመንግስት አስተዳደርንና ተግባራቱን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል፡፡ እናም የመንግስትና የፓርቲ ተቋማት ተደበላልቀዋል፡፡ ስልጣንና ሀብት በጥቂቶች እጅ ወድቋል። የመንግስት ተቋማት የሚመሩት በዘፈቀደ ነው፡፡

በዚህ ዘገባ የተገለጹትን የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 1844 (2008) እና 1907 (2009) ጥሰት ተጠያቂዎችና ግለሰቦች ለማጣራት፤ አጣሪ ቡድኑ ከሀገሪቱ አስተዳዳሪዎች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች የደህንነትና የፓርቲ ባለስልጣናት ጋር ለመገናኘት ችሏል፡፡ ፍጹም ግለሰባዊነት የሰፈነበት የውሳኔ አሰጣጥ፣ ዘፈቀዳዊ የሆነ የሀብት አጠቃቀምና ብክነት እንዲሁም ልማዳዊ አሰራሮችና ማን አለብኝነት መንሰራፋታቸውን አጣሪ ቡድኑ ተገንዝቧል፡፡ አጣሪ ቡድኑ በዚህኛው የሥራ ዘመኑ በጅቡቲ፣ በኢትዮጵያ፣ በሶማሊያና በሱዳን የሚንቀሳቀሱትን ጨምሮ በቀጣናው ያሉ ታጣቂ ተቃዋሚ ኃይሎችን ኤርትራ እንደምትደግፍ አሳማኝ መረጃ አሰባስቧል፡፡

በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስና በሌሎችም አካባቢዎች የሚኖሩ የኤርትራ የዲፕሎማሲ ፣ የደህንነትና የህግደፍ ደጋፊዎች ለተጠቀሱት ታጣቂ ተቃዋሚ ኃይሎች ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ አል-ሸባብን ጨምሮ ከሌሎች ታጣቂ ተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ግንኙነት መመስረቱን የኤርትራ መንግስት አልካደም፡፡ ኤርትራ የኢትዮጵንና የጅቡቲን ታጣቂ ቡድኖች ስለመርዳቷ ለቀረበላት ጥያቄ የሁለት ሀገሮች ውዝግብ ከድንበር ጋር የተገናኘ መሆኑን ካስታወሰች በኋላ ከጅቡቲ ጋር የተፈጠረውን የድንበር ውዝግብ ለመፍታት ግን በኳታር አደራዳሪነት ጉዳዩ ለእርቅ መቅረቡን በመጥቀስ ለአጣሪ ቡድኑ መረጃ ለመስጠት አልፈቀደችም፡፡

የአስመራው መንግስት ለታጣቂ ተቃዋሚ ሃይሎች የምታደርገው ድጋፍ የሚመራው ከብሔራዊ የደህንነት ጽሕፈት ቤት፣ ከኤርትራ ወታደራዊና ከህግደፍ (ህዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲና ለፍትህ) አመራሮች በተውጣጡ አነስተኛ መኮንኖች በተመሰረተ ቡድንና በቀጥታ በፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት አዛዥነት ነው፡፡

እነዚህ ተቋማት በባህሪያቸው ምስጢራዊነት አልፎ አልፎ ደግሞ የኃላፊነት መደራረብ ይስተዋልባቸዋል፡፡የሥልጣን መባለግና ግለ-ታማኝነትም ሌላኛው መገለጫቸው ነው፡፡ ይህም የዕዝ ሰንሰለቱን ለማወሳሰብ ሆነ ተብሎ የሚሸረብ ሴራ ነው፡፡ መኮንኖቹ በርካታ ተግባራትን እንዲከውኑ ይጠበቃል፡፡ ከአንድ በላይ ለሆኑ የዕዝ ሰንሰለቶችም ሪፖርት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

የኤርትራ ደህንነት አገልግሎት መዋቅሩን ይበልጥ ለማወሳሰብ ደግሞ የማደራጀት ሥራ በመስራት ላይ መሆኑን በቅርቡ ለአጣሪ ቡድኑ የደረሱ መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ የሆነ ሆኖ ግን፤ ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የመታካሂደውን የውጭ ዘመቻዎችን የሚመሩና አቅጣጫ በመስጠት ተግባር የተሰማሩ ዋና ዋና መኮንኖችን ቁልፍ ተልዕኮቻቸውን አጣሪ ቡድኑ ለማወቅ ችሏል፡፡

በእነዚህና ሌሎች ምክንያቶች የኤርትራ መንግስት ሁሌ ማዕቀቦች ተጥለውበታል። እነዚህን ማዕቀቦች በመተላለፍ በተለያዩ ወቅቶች እንደ አል-ሸባብ ላሉ ድርጅቶች መሳሪያ የማቀበል፣ የጎረቤቶቹን ሰላም የማደፍረስ ተግባራትን እየተጫተ ነው። ይህ ተግባሩ ሊለቀው ባለመቻሉ ዛሬም ከሰሜን ኮሪያ የጦር ቁሳቁሶችን በመግዛት ማዕቀብ ተጥሎበታል። ይህም ሻዕቢያና ማዕቀብ ሁለት የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ገፅታዎች የሆኑ አስመስሏቸዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy