Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ሜትር ታክሲዎች ከነቅሬታቸው ናቸው

0 1,147

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በአዲስ አበባ ከተማ የሚትር ታክሲ አገልግሎት ሲጀመር በተሳፋሪውና በተሸከርካሪው ስምምነት ላይ ተመስርቶ የአገልግሎት ክፍያ ይፈጸም እንደነበረ የታክሲዎቹ አሽከርካዎችና ባለንብረቶች ያስታውሳሉ። ይህ ብዙም ሳይቆይ መንግሥት በኪሎ ሜትር 10 ብር ታሪፍ በማውጣት ስራ ላይ እንዲውል ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ይህን ተከትሎም የታክሲ ባለንብረቶች ታሪፉ የሚያሰራ አይደለም፣ ወጪያችንን ጭምር ለመሸፈን እንቸገራለን እያሉ ቅሬታቻውን ማሰማ ታቸውን ቀጥለዋል፡፡

የፒኮክ የከተማ ሚትር ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር አባልና አሽከርካሪ አቶ ሁነኛው ዳኜ እንደሚለው፤ ቀደም ሲል የአገልግሎት ክፍያው በእነሱና በተሳፋሪው ስምምነት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ በቅርቡ የአገልግልት ታሪፍ ከወጣ ወዲህ በኪሎ ሜትር 10 ብር በማስከፈል አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ አንድ ወር ሞልቶታል፡፡

ይህ ታሪፍ የሚያዋጣ እንዳልሆና የመኪናዎቹ መለዋወጫዎች እንደልብ የማይገኝ መሆኑን በመጥቀስ ታሪፉ ከወጪው ጋር ፈፅሞ እንደማይጣጣም ይናገራል፡፡ ‹‹በኪሎ ሜትር 10 ብር እያስከፈልን ተልጋዮችን የፈለጉት ቦታ ብናደርስም ተመላሽ ሰው ስለማናገኝ ባዷችንን እየተመለስን ነው›› ይላል፡፡ በዚህም ምክንያት እንደልብ ተንቀሳቅሶ መስራት እንዳልተቻለም ያመለክታል፡፡ ወጪያቸውና በየወሩ ለመንግሥት የሚከፍሉት ሊመጣጠን እንዳልቻለም ጠቅሶ፣ ታሪፉ አዋጭ አለመሆኑን ይገልፃል፡፡

አገልግሎቱን በብዛት የሚጠቀሙት የህብረተሰብ ክፍሎች መክፈል የሚችሉ ናቸው የሚለው አቶ ሁነኛው፣ ‹‹የአገልግሎት ታሪፉ እንደማያዋጣን ተገልጋዮችም ተረድተውናል›› ይላል። አገሪቷ ይበልጥ እያደገች ስትሄድ ስራውም እየተለመደ የሚመጣ ከሆነ፣ እንደልብ ተንቀሳቅሶ መስራት ይቻላል፤ ይህን ተከትሎም ታሪፉም ያዋጣ ይሆናል ይላል፡፡

በታሪፉ ላይ መንግሥት በሩን ዝግ እንዳላደረገና ከማህበራቱ ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከሰሞኑ በታሪፉ ላይ ማስተካከያ ያደርጋል ብለው እንደሚያስቡም ይናገራሉ፡፡

የአርመኒያ የከተማ ሜትር ታክሲ ማህበር አሽከርካሪ አቶ በለጠ የትተገኘህ በኪሎ ሜትር 10 ብር የሚለው ታሪፍ አዋጪ አይደለም ሲሉ የአቶ ሁነኛው የሰጡትን አስተያየት ይጋራሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ታክሲዎቹ የተገዙት 70 በመቶ ከባንክ በተገኘ ብደር 30 በመቶ ደግሞ ባለታክሲዎቹ ወጪ እንደመሆኑ ባለታክሲዎቹ በወር ለመንግሥት 7ሺ 500 ብር መክፍል ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ላይ የቤተሰብ፣ የቤት ኪራይና የመኪና ሰርቪስ ወጪዎች ይጠብቋቸዋል ፡፡ ይህ ደግሞ በ10 ብር ታሪፍ ብቻ የሚሸፈን አይሆንም፡፡

አቶ በለጠ የፈለጉት ቦታ ቆመው መስራት እንዳልቻሉና ይህም በስራቸው ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ያስረዳሉ፡፡ ለሚኒባስ ታክሲዎች በነዳጅ ላይ የተደረገው የታሪፍ ማስተካከያ ሜትር ታክሲዎችን አላካተቱም አግባብ እንዳልሆነ ይገልፃሉ፡፡ ‹‹መንግሥት ችግራችንን በማየት ተገቢውን ምላሽ ሊሰጠን ይገባል›› ይላሉ፡፡

‹‹የህብረተሰቡን የትራንስፖርት ፍላጎት እየፈታን አይደለም›› የሚሉት አቶ በለጠ፤ የተወሰኑ ተገልጋዮች ብቻ አገልግሎቱን እንደሚጠቀሙ ተናግረው፣ ተጠቃሚዎቹም የላዳ ታክሲ ተጠቃሚዎች የነበሩ ብቻ እንደሆኑም ይገልፃሉ ፡፡

የአርመንያ የከተማ ሜትር ታክሲ ባለንብረቶች ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውዴ ሙሉጌታ እንደሚገልፁት፤ ከትራንስፖርት ባለሥልጣን ጋር በተወሰነ መልኩ ውይይት ቢደረግም ታሪፉን በተመለከተ ግልፅ የሆነ ውይይት አልተደረገም፤ ባለሥልጣኑ ከየካቲት 1ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ታሪፉ በሥራ ላይ እንዲውል በመገናኛ ብዙሃን ይፋ ካደረገ ወዲህ ለመወያያት እድል አልተሰጣቸውም፡፡

አቶ ዘውዴ ‹‹ባለሥልጣኑ በታሪፉ ላይ ጥናት አድርጎ ወደ ስራ የገባው የእኛንና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ አይደለም›› ይላሉ፡፡ ‹‹ይህን ቅሬታችንን ለፌዴራል መንግሥት ትራንስፖርት ባለስልጣን አቅርበናል›› የሚሉት አቶ ዘውዴ፣ በወቅቱም ከስድስት ወራት በኋላ ተመኑ እንደሚስተካከል ተገልጾላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ስራቸውን እየሰሩ መብታቸውን ለማስከበር ጥረት ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉም ይናገራሉ ፡፡

አቶ ይታገሱ አምባዬ ጊዜያቸውን በአግባቡ ለመጠቀም ሲሉ የሜትር ታክሲዎችን አልፎ አልፎ ይገለገላሉ ፡፡ መንግሥት በኪሎ ሜትር እንዲከፈል ያደረገው አስር ብር ለእኛ ፍትሃዊ ነው የሚሉት አቶ ይታገሱ፣ አገልግሎት ሰጪዎቹን ግን ይጎዳል ይላሉ፡፡

‹‹ታክሲዎች በዚህ ታሪፍ ሃያ አራት ሰዓት ተንቀሳቅሰው መስራት ቢችሉ ያዋጣቸዋል›› የሚሉት አቶ ይታገሱ፣ ተመላሽ የሚያገኙ ከሆነም ታሪፉ ሊያዋጣቸው እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ግን ሲሆን አይስተዋልም መኪናዎቹ ተገልጋዩን አድርሰው ወደቦታቸው የሚመለሱት ባዷቸውን ነው ይላሉ፡፡ መንግሥት በታሪፉ ላይ ጥናት በማድረግ ተጠቃሚውንም ሆነ አገልግሎት ሰጪዎቹን በማይጎዳ መልኩ መስራት እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡

በአዲስ አባባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ጀርመን እንደሚሉት፤ የከተማ ሜትር ታክሲ አገልግሎት የተጀመረው የከተማዋን ኢኮኖሚዊ እድገት፣ የህብረተሰቡን የትራንስፖርት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ነው ፡፡

የህብረተሰቡ ፍላጎት መፈጠሩንና የውጪ እንግዶችም ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የተፈጠረውን የትራንስፖርት አገለግሎት ችግር እየፈታ መሆኑን ጠቅሰው፣ አዲስ አሰራር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በክፍያ ታሪፍ በኩል የግንዛቤ ክፍተት መከሰቱን አቶ ሰለሞን ይገልፃሉ፡፡ በችግሩም ላይ ከታክሲ ባለንብ ረቶችና አመራሮች ጋር ውይይት መደረጉንና የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ያመለክታሉ፡፡

አቶ ሰለሞን እንደተናገሩት፤ ታሪፉ ከየካቲት 1ቀን 2009 ዓ.ም ጀምሮ ስራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ ታክሲዎቹም በታሪፉ መሰረት አገልግሎት መስጠት እንደሚኖርባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷል፡፡

ከታክሲ ባለንብረቶቹ በኩል ታሪፉ አዋጭ አይደለም የሚል ቅሬታ መቅረቡን አቶ ሰለሞን ያምናሉ፡፡ ታሪፉ በጥናት ላይ ተመስርቶ የወጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ የነዳጅ ፍጆታን፣ የአሽከርካሪ ደመወዝን፣ የማሳደሪያ ቦታ ክፍያን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

‹‹የታክሲ ባለንብረቶቹ አያዋጣንም ከማለት ይልቅ አገልግሎቱን ሲሰጡ ጠቀሜታውንም መረዳት ይችላሉ፡፡ እኛም ከመጀመሪያውኑ በጥናቱ ላይ አዋጭነቱን ተረድተን ነው አገልግሎቱ ተግባረዊ እንዲሆን ያደረግነው›› ይላሉ፡፡ መነሻቸውን አንድ ቦታ ላይ አርገው አየተዘዋወሩ አገልግሎት መስጠታቸው ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው አቶ ሰለሞን ይጠቁማሉ፡፡ ወደፊት እየታየ በታሪፉ ላይ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችልም ይገልፃሉ፡፡

ቀደም ሲል በተገልጋዩ ዘንድ የተሟላ ግንዛቤ እንዳልነበር የሚያስታውሱት አቶ ሰለሞን፣ የአገልግሎት ደረሰኝ ያለማግኘትና ያለታሪፍ ክፍያ መጠየቅ አልፎ አልፎ እንደሚስተዋሉም ይናገራሉ። ተገልጋዮች የሚሰጧቸውን አስተያየቶች ለመቀበል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ አሠራር መዘርጋቱን ይጠቁማሉ፡፡

አስናቀ ፀጋዬ

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy