NEWS

ምርቶቻቸው በጤና ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ስድስት የውሃና የከረሜላ አምራቾች ንግድ ፈቃድ ተሰረዘ

By Admin

April 30, 2017

በህብረተሰብ ጤና ላይ ጉዳት ያደርሳሉ ባላቸው ስድስት የከረሜላና የውሃ አምራች ኩባንያዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለሥልጣኑ በክትትልና ቁጥጥር ስራው ለህብረተሰቡ ጤና አስጊ ናቸው ያላቸውን አራት የከረሜላና ሁለት የታሸገ ውሃ አምራችና አስመጪዎች የንግድ ፈቃድ መሰረዙን ገልጿል።

የባለስልጣኑ የምግብ አምራቾች ቁጥጥር አስተባባሪ አቶ ገረመው ጣሰው እንደገለጹት፥ በድርጅቶቹ ላይ እርምጃ የተወሰደው በ190 ሀገር በቀል የምግብ አምራችና ላኪዎች ላይ ባካሄደው የቁጥጥርና የክትትል ስራ ነው።

“የስድስቱም ድርጅቶች ምርቶች ለህብረተሰቡ ጤና አስጊ ሆኖ በመገኘቱ ከገበያ እንዲወገዱ ተደርጓል” ብለዋል።

የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን አብርሃ እርምጃ ከተወሰደባቸው ድርጅቶች መካለከል የከረሜላ አምራችና አስመጪዎቹ ግሪን ሼር፣

ስዊት ወርልድ እና ኢት ፊትስ ሲሆኑ፥ ሪል ወተር እና ገንድሮብ ወተር ደግሞ ሁለቱ ፈቃዳቸውን የተነጠቁ ውሃ አምራቾች ከስድስቱ አምስቱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአንዱን ከረሜላ አምራች ስም እንዲናገሩ፥ ኢዜአ ለሁለቱም የተቋሙ ሃላፊዎች ቢያቀርብም መረጃውን እንዳላገኘ ጠቅሷል።

ድርጅቶቹ ከመታገዳቸው በፊት ማስጠንቀቂያ እንደደረሳቸው የተናገሩት አቶ ገረመው ማስጠንቀቂያውን ተቀብለው ለማሻሻል ባለመፈለጋቸው እርምጃው መወሰዱን አስረድተዋል።

በተመሳሳይም ለ16 ምግብ አምራችና አስመጪዎች ባለስልጣኑ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መስጠቱንም ነው የተናገሩት።

የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ከተሰጣቸው ድርጅቶች ስምንቱ የምግብ አስመጪና ላኪ ሲሆኑ ስምንቱ ደግሞ አምራቾች መሆናቸው ጠቅሰዋል።

ከነዚህ በተጨማሪም 28 የተለያዩ አምራች ድርጅቶች ላይም ምርቶቻቸው ጥራትና ደረጃቸውን ያልጠበቁ በመሆኑ ከተሰራጩበት ገበያ እንዲሰበስቡ በማድረግ እገዳ እንደተጣለባቸው ተናግረዋል።