ቀጣይ ጉዞዎትን ለምን ወደ አስደናቂዋ ኢትዮጵያ ማድረግ ይገባዎታል ብሎ ዘገባውን የሚጀምረው መቀመጫውን ፊሊፒንስ ያደረገው ኢንኩዊሪየር ድረ-ገፅ ፊሊፒናዊያን ተጓዦች ከጉብኝታቸው መዳረሻዎች አንዷ ሊያደርጓት እንደሚገባ ይጠቁማል ፡፡
ድረ-ገፁ ሎንሊ ፐላኔት እኤአ በ2017 ከአለማችን ምርጥ 10 የቱሪዝም መዳረሻዎች ኢትዮጵያን ብቸኛ የአፍሪካ ተወካይ አድርጎ መምረጡንም አስታውሶ “ማራኪ የመሬት አቀማመጥና ውብ የተፈጥሮ ጸጋዎች አላት” ብሏል፡፡
ኢትዮጵያን ለየት የሚያደርጋት ምንድን ነው?ብሎ የሚጠይቀው ድረ-ገፁ ሀገሪቱ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መቀመጫ መሆኗን ያወሳል፡፡
ባለፉት አመታትም በአፍሪካ ውስጥ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉ ሃገራትና በአለምም ኢኮኖሚያቸው እያደጉ ካሉ አምስት ሃገራት አንዷ መሆኗን ጠቁሞ ልማቷ በተጨባጭ በሚታይ መሰረተ ልማትና እያደገ በሚገኝ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደሚገለፅ ጠቁሟል፡፡
ለአብነትም እ.ኤ.አ በ2014 ስምንት መቶ ሺህ ያህል የውጪ ሃገር ዜጎች እንደጎበኟትና ከዚህም 2.8 ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ አስደናቂና ሚስጥራዊ ውበት የሚገለፀውና በተጓዦች በተደጋጋሚ የሚያስነሳት የታሪክ ሃብታምነቷ፣ጥንታዊ ልማዶቿና ደጋግ ህዝቦቿ መሆናቸውን ድረ- ገፁ ይገልፃል፡፡
ካሏት የቱሪዝም መዳረሻዎች የኦሞ ብሄራዊ ፓርክን፣የእንጦጦ ኮረብታዎች ፣ጣና ሀይቅ፣የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ፣የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ፣የአክሱም ሃውልቶችንም ጠቅሷል፡፡
የፊሊፒንስ ተጓዦች ወደ ኢትዮጵያ ከመግባታቸው በፊት ቪዛ ማግኘት ይገባቸዋል የሚለው ዘገባው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከማኔላ ወደ አዲስ አበባ በሳምንት አራት ጊዜ በረራ እንደሚያደርግም ጠቁሟል፡፡ እናም ፊሊፒናዊያንም ሆናችሁ የዓለም ዜጎች ኢትዮጵያን በመጎብኘት ደጋግ ዜጎቿንና ውብና ማራኪ የተፈጥሮ ጸጋዋን ያድንቁ ሲል ዘገባው ይመክራል፡፡
ምንጭ፡- http://lifestyle.inquirer.net