Artcles

በሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግና መለወጥ ይቻላል!

By Admin

April 25, 2017

በሀገር ውስጥ ሰርቶ ማደግና መለወጥ ይቻላል!

ዳዊት ምትኩ

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እዚህ ሀገር ውስጥ መነጋገሪያ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሁንና የችግሩ አሳሳቢነትና ትኩሳት ዛሬም ድረስ አለ። የችግሩ ምንጭ በመንግስት በኩል በሚገባ የተለየ ቢሆንም፤ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ መቅረፍ አልተቻለም። ይህ የሆነበት ምክንያትም ሀገራችን ውስጥ ዛሬ የ“አይቻልም” መንፈስ እየተሰበረ መሆኑን የማይገነዘቡና በግ ወጥ አዘዋዋሪዎች የተሳሳተ ገለፃ ምክንያት የሚታለሉ ዜጎች በመኖራቸው ይመስለኛል።

እናም በእነዚህ ህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ምክንያት በተይም ወጣቱ ክፍል በአቋራጭ ሃብት ለማግኘት የሚያደርገው የተሳሳተ ስሌት ለከፋ አደጋ ሲጋለጡ ይሰተዋላል። በየጊዜው “በእዚህ ሀገር ውስጥ ኢትዮጵያዊያን በኮንቴይነር ሱጓዙ ተያዙ፣ በባህር ላይ ሲያቋርጡ እንዲህ ሆኑ…” የሚሉ ዘገባዎች ይህን አባባሌን የሚያጠናክሩ ናቸው።

በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰው አደጋ በመጠንም ሆነ በአይነቱ የተለያየ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው። ከመብት ጥሰት እስከ ህይወት ማጣትን በሚያስከትለው በዚህ ወንጀል ሰለባ የሚሆኑት ዜጎቻችን ቁጥር ከፍተኛነትም እንዲሁ። የሀገራችን ገጽታ መበላሸትም ሳይዘነጋ።

ከገንዘቡ በስተጀርባ በዜጎች ላይ የሚደርሰው የመብት ጥሰት፣ የአካል መጉደል፣ የጤና መታወክ አደጋም በነርሱ ዘንድ ግምት የሚሰጠው ጉዳይ አይሆንም፡፡ የሀገራችን ገጽታ መበላሸትም አያስጨንቃቸውም፡፡ በርግጥም ጭንቅላታቸው በገንዘብ ተደፍኗልና በየወቅቱ በዜጎች ላይ የሚደርሱ አደጋዎች መንስዔዎቹ እነርሱ መሆናቸውን እያወቁ ለፀፀት ሲገባቸው “የሌባ አይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ” እንደሚባለው በተቃራኒው ጉዳዩን ለማስተባበል ሲረባረቡ መታየታቸው ግለሰቦቹ ምን ያህል በአፍቅሮተ-ነዋይ እንደታወሩ የሚያመላክት ነው፡፡

ታዲያ የችግሩን መስፋትና አደገኝነት የተገነዘበው መንግስት የዜጎችን ከአደጋ ለመታደግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ቢጀምርም ጥረቱ የተፈለገውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ አልቻለም። የችግሩን አደገኛነት እንደ ፊልም ካልቆጠርነው በስተቀር በአንድ ወቅት በዕቃ ታንከር ውስጥ ታሽገው ህይወታቸውን ካጡት ዜጎቻችን በተጨማሪ በባህር ላይ ተጥለው የአሳ ነባሪ ሲሳይ ለመሆን የሚገደዱ ወገኖቻችንን ስቃይና እንግልት ከራሳቸው የስደት ሰለባ ከሆኑት ወገኖች አንደበት አርምጠናል።

እርግጥ ችግሩ የእያንዳንዳችንን በር እስኪያንኳኳ ድረስ መጠበቅ የለብንም። እናም ለችግሩ መንስዔ የሆኑ ጉዳዩችን ማወቅ ይገባል። እነዚህ የችግሩ ተዋናዮች ግብ አንድና አንድ ነው። ገንዘብን በማንኛውም መንገድ አግኝቶ የተደላደለ ኑሮን መምራት፡፡ በቃ! ለእነርሱ የዜጎች ስቃይና ሞት ምናቸውም አይደለም፡፡ የመብታቸው፣ የደህንነታቸውና የክብራቸው ጉዳይም አያሳስባቸውም፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ አንድ ዕውነታን ማንሳት ይገባል—የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ስለመሆኑ፡፡ ምክንያቱም ለስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድልን በመፍጠር መንግስትነት ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል፤ የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር አደጋን ለመከላከልም ከግንዛቤ ማስጨበጥ እስከ ተጨባጭ ርምጃዎችን መውሰድ ደረጃም ደርሷል። እንደሚታወቀው በመላ ሀገሪቱ በተዋረድ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል፡፡ በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሔው አካል እንዲሆን በየክልሉ በርካታ ተግባራት ዕውን ሆነዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደራጀው ግብረ ሃይልም በሀገራቸውም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር በህጋዊ ተንቀሳቅሰው መስራት የሚፈልጉ ዜጎችን በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በማስገባት በተለያዩ የስራ መስኮች የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠት እንዲሁም ከሥልጠናው በኋላ በሰለጠኑበት ሙያ በሀገር ውስጥ በመደራጀት ወደ ሥራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ከስራ ጋር ለማስተሳሰር ተችሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት ለሚፈልጉ ዜጎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ፣ ለስልጠና እና መሰል ስራዎች ድጋፍ የሚውል ሐብት ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ማዘጋጀትና ሃብት የማፈላለግ ተግባራት ገቢራዊ ሆነዋል። ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተከናወኑትን ተግባራት እንደ ምሳሌ ብንወስድ እንኳን፣ ከአረብ አገር ተመላሾችን በጊዜያዊነት በመንከባከብ እንዲረጋጉ ከማድረግም አልፎ  ለ2 ሺህ 797 ከስደት ተመላሾች የስነ ልቦና፣ የአመለካከትና የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙና ወደ ተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ተደርጓል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በዚህ ትውልድን ለአደጋ በሚዳርግ ተግባር የተሰማሩ ደላሎች ላይ የህግ ማስከበር ስራዎችም ተከናውነዋል። በዚህም የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ቦታዎችን መለየት ችግራቸውን መሰረት አድርጎ በተመረጡ እንዲሁም ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች የመቆጣጠር ስራ ገቢራዊ ሆኗል።

በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሀገር የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግም ህግን መሰረት አድርጎ ነው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ ተችሏል። የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎችን የሚመለምሉና የሚያዘዋውሩ ደላላዎችን፣ ተባባሪና ቤት አከራዮችን እንዲሁም አጓጓዦችን መረጃ ማሰባሰብና በመለየት በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር የመፍጠር ርምጃዎችም ሲወሰድ ቆይቷል።

ይሁንና በመንግስት በኩል ችግሩን ለመቅረፍ ይህ ሁሉ ጥረት ቢደረግም፣ ችግሩ ግን አሁንም በበቂ ሁኔታ ተፈትቷል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የህገ ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎቹ ብዛትና ዓይነት፣ የመረቡ ውስብስብነት፣ የቤተሰብ ገፋፊነትን ጨምሮ ሁሉም ለችግሩ መስፋፋት የራሱን አስተዋጽኦ የሚያበረክት በመሆኑ ነው።

እነዚህ ሀገር ውስጥ በአሁኑ ወቅት በመንግስትና በህዝብ አማካኝነት ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ሁኔታዎቹን አሟጦ መጠቀም ከወጣቶች ይጠበቃል። በተለይም መንግግስትና ህዝቡ ለወጣቱ ከ10 ቢሊዩን ብር በላይ ተዘዋዋሪ ፈንድ በመመደብ የወጣቱን ስር አጥነት ለመፍታት ጥረት እያደረጉ ነው። ወጣቱ ይህን የተመቻቸ ሁኔታ አዋጪ በሆኑ ስራዎች ዙሪያ በመደራጀት ሊጠቀምበት ይገባል።

ለዚህም ሁሉንም ነገር ከመንግስት መጠበቅ የለበትም። መንግስት በጀቱን ሲያቀርብ ወጣቱ ደግሞ ስራን በመፍጠር ገቢውን ማዳበር ይኖርበታል። ይህም በራሱ ሀገርና ህዝብ መካከል ሰርቶ እንዲለወጥ ያስችለዋል። በመሆኑም እዚህ ሀገር ውስጥ በፌዴራል መንግስትና በክልሎች የተመቻቸውን ዕድል በመጠቀም ራሱን በመጥቀም ለሀገሩ ኢኮኖሚም የበኩሉን እገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል። በመሆኑም ወጣቱ የህግ ወጥ ደላላዎችን የተሳሳተ ምክር እየሰማ ሁሌም ውጭ ውጭውን ከመመልከት በሀገር ውስጥ ማደግና መለወጥ እንደሚቻል ግንዛቤ መያዝ አለበት።