Artcles

በህዝባዊ ወገንተኝነት የሚመራው መንግስታዊ ጥረት

By Admin

April 23, 2017

 

በህዝባዊ ወገንተኝነት የሚመራው መንግስታዊ ጥረት ዘአማን በላይ የኢፌዴሪ መንግስት በባህሪው ለህዝብ የወገነ ነው። በሚያከናውናቸው ማናቸውም ተግባራት የህዝብን ጥቅም ያማከለ ነው። ይህ ህዝባዊ መንግስት በተለያዩ ወቅቶች ህገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ የህዝቡን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከመጠበቅ ባሻገር፤ ባለፉት ጊዜያት ባህር ማዶ ተሻግሮም ባለማወቅ በህገ ወጥ ደላላዎች ተታልለው ለስደት የተዳረጉ ወገኖቻችን ለመርዳት ብዙ ርቀት በመጓዝ ኃላፊነቱን ተወጥቷል፤ እየተወጣም ይገኛል። በተለይም የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በህገ ወጥ መንገድ ተጉዘው የሀገሪቱ መንግስት የውጭ ዜጎች እንዲወጡ ያስቀመጠውን የጊዜ ገደብ ያልተቀበሉ ዜጎች ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያደረገው ጥረት ተጠቃሽ ነው። በወቅቱ የኢፌዴሪ መንግስት በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ የገቡትን ዜጎች ከዚያች ሀገር ለማስወጣት ብርቱ ጥረት አድርጓል። በዚህም በህገ ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የገቡ ዜጎችን ለመመለስ መንግስት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ መድቦ ዜጎቹን በማጓጓዝ ከጀመረ መንግስታዊ ሃላፊነቱን መወጣን እስታውሳለሁ። ዋነኛ ትኩረቱን በዚህ ጉዳይ ላይ በማድረግና ያለ አንዳች ዕረፍት በመስራቱም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቹን ለሀገራቸው አብቅቷል። ጥረቱ በዚህ ብቻ ሳይገደብም፤ እነዚህ ወገኖች የሚያገግሙበትን ሁኔታ አመቻችቶ በተዘጋጀላቸው ስፍራም እንዲያርፉ ብሎም ዘላቂ ህይወታቸው የተመቻቸ እንዲሆን የሚያደርጉ አቅጣጫዎችን በመቅረፅ የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥሯል። ይህም ከስደት ተመላሾቹ በሀገር ቤት ሰርተው መለወጥና ማደግ እንዲችሉ ያስቻለ ተግባር ነበር። መንግስትም ምን ያህል ለህዝቡ ተቆርቋሪና አሳቢ መሆኑን ያንፀባረቀ ተግባር እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። ከሶስት ዓመት በኋላም ዛሬ ላይ ተመሳሳይ ችግር ተፈጥሯል። ይኸውም የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ሀገሩ ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ የገቡ የውጭ ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ የምህረት አዋጅ ማውጣቱ ነው። አሁንም ቢሆን ሳዑዲ ውስጥ ቁጥራቸው እጅግ የበዛ ኢትዮጵያዊያን እንዳሉ ይታወቃል። ታዲያ ይህን ዕውነታ በሚገባ የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት ካለው ህዝባዊ ወገንተኝነት በመነሳት ዜጎቹ በተሰጠው ምህረት ተጠቅመው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ሰፊ ጥረት እያደረገ ነው። በዚህም ከሳዑዲ መንግስት ጋር ፊት ለፊት በመነጋገር ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ዜጎቻችን በሳዑዲ ውስጥ በሚገኙባቸው የተለያዩ ከተማዎች በመገኘት የጉዞ ሰነድ እንዲወስዱ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመክፈት ከምህረቱ ቀነ ገደብ በፊት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ጥረት እያደረገ ነው። ምን ይህ ብቻ። በሪያድ መንግስት በህገ ወጥነት የተፈረጁት ስደተኞች በዚያች ሀገር ቆይታቸው ያፈሩትን ንብረት ይዘው በህጋዊ መንገድ እንዲገቡ እንዲሁም አሻራ መስጠት ሳያስፈልጋቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ ጥረት ተጠናክሯል። ስደተኞቹ ወደ ሀገራቸው ሲገቡም 21 የሚሆኑ የመገልገያ ዕቃዎቻቸውን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ፈቅዷል። እነዚህ ከታክስ ነፃ እንዲገቡ የተፈቀዱ ቁሳቁሶች ዝርዝር፣ ስደተኞች ጅዳና ሪያድ በሚገኙ የኤምባሲው ቢሮዎች ማግኘት እንደሚችሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። ከሁለቱ ቢሮዎች ውጪም ተመሳሳይ የጉዞ ሰነድ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት መቋቋማቸው ተገልጿል። እነርሱም በሪያድ ሚሲዮን፣ ቡረይዳና ዋዲ ደዋስር (ሪያድ አካባቢ)፣ እንዲሁም በጅዳ ሚሲዮን በመካ፣ ከሚስሸጥ፣ ጄዛንና መዲና የሚገኙት ማዕከላት ተጠቃሽ ናቸው። ይህ ተግባር የኢፌዴሪ መንግስት ምን ያህል ለህዝቡ የሚያስብና ዜጎቹ እንዳይጎዱ ያለውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው። ያም ሆኖ ግን መንግስት ዜጎች ሰነዶቻቸውን እንዲያገኙ በሳዑዲ የተለያዩ ጽህፈት ቤቶችን ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ እስካሁን በቂ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች የምህረት አዋጁን እየተጠቀሙበት አለመሆኑ ይታወቃል። የዚህ ችግር ምክንያቱ ህገ ወጥ ደላላዎች ‘የሳዑዲ መንግስት እንዲህ አያደርግም’ በማለት በሚነዙት አሉባልታ ንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ይመስለኛል።

ምክንያቱም ስደተኞቹ ወትሮም ከሀገር የወጡት በህገ ወጥ መንገድ በእነዚሁ ህገ ወጥ ደላላዎችም አማካኝነት የሚካሄድ በመሆኑ ከህግ ያፈነገጠው ስራቸው እንደሚበላሽባቸው በሚገባ ስለሚያውቁ ነው። እርግጥ የሳዑዲ መንግስት በአዋጁ ላይ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አማካኝነት እንደገለፁት ስደተኞቹ በሌላ ጊዜ በህጋዊ መንገድ እንደሚመለሱ እነዚህ ደላላዎች ስለሚያውቁ በህገ ወጥ ስራቸው ላይ የሚያመጣባቸውን ውድቀት በመገንዘብ አስቀድመው በ“ይሆናል” መላ ምቶች የታገዙ አሉባልታዎችን ማስወራታቸው የሚገርም አይደለም። ምክንያቱም የሳዑዲ መንግስት ፍላጎት የየትኛውም ሀገር ዜጋ በህጋዊ መንገድ በሀገሩ ውስጥ እንዲኖር እንደሚፈልግና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወሰ ውጭ ሀገር እንዲሄዱ የማድረግ ስራ በቅርቡ ይጀመራል ማለታቸው የህገ ወጥነት መንገድ እንደሚገባ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው። ዳሩ ግን የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ በህገ ወጥ መንገድ በሳዑዲ ይኖሩ በነበሩ ዜጎች ላይ የደረሰው ሞት፣ እንግልትና በባዶ እጅ መመለስ የሚያሳየው ነገር ቢኖር፤ ዛሬም በምህረት አዋጁ ያልተጠቀሙ ስደተኞች የዚያን ጊዜው አደጋ ሊያጋጥማቸው እንደማይችል ምንም ዓይነት ዋስትና የለም። እናም ስደተኞቹ ይህንን የለየት የህገ ወጥ ደላላዎችን ቅጥፈት ባለመስማት አንድም የሳዑዲ መንግስት ያስቀመጠውን የጊዜ ገደብ መጠቀም፣ ሁለትም የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን ደህንነት አስቀድሞ ለመጠበቅ ከወዲሁ የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ስደተኞቹ የተሰጣቸውን ዕድል በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል። በመሆኑም ስደተኞቹ ዕውነታውን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ተገንዝበው ለራሳቸው ዘላቂ ህይወትም ይሁን ለመንግስት ህዝባዊ ወገንተኝነት ጥረት ዋጋ መስጠት ይኖርባቸዋል እላለሁ። የኢፌዴሪ መንግስት እንኳንስ የራሱን ዜጋ ቀርቶ የሌሎች ሀገራትን ስደተኞች ተቀብሎ የሚያስተናግድ የህዝብ ወገንተኝነትን የተላበሰ ነው። ይህ ምስጉን ተግባሩም በተለያዩ ሀገራት እየተደገፈ ነው። መንግስት በዜጎቹ ላይ ወደፊት ሊደርስ የሚችለውን ችግር ከወዲሁ በመገንዘብ የስጋት ትንተና (treat analysis) በማካሄድ ከወዲሁ ችግሩን ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት መደገፍ እንዳለበት አንዳንድ ሀገራት እየገለፁ ነው። ከእነዚህ ሀገራት ውስጥ ዴንማርክ አንዷ ናት። ሁሌም ጥሩነት መልሶ ይከፍላልና ኢትዮጵያ ለሌሎች ሀገራት ስደተኞች የምታደርገውን ጥረት በአንክሮ ሲከታተል የነበረው የዴንማርክ መንግስት ሰሞኑን በስደተኞች ኢንተግሬሽንና ቤቶች ሚኒስትሯ ሚስ ኢንገር ስቶይበርግ አማካኝነት የኢትዮጵያ መንግስት በሳዑዲ ዓረቢያ የሚኖሩ ዜጎቹን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እያከናወነ ላለው ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ይህ የዴንማርክ መንግስት ፍላጎት የኢፌዴሪ መንግስት ዜጎቹ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለሚያደርገው ከፍተኛ ጥረት አጋዥ ነው። ማንኛውም በሀገራችን ስራዎች ላይ የተወሰነ እሴት የሚጨምር ጉዳይ ቅቡል በመሆኑ እኔ በበኩሌ ይህን የዴንማርክ መንግስትን የድጋፍ ፍላጎት ሳላደንቅ አላልፍም። ያም ሆኖ የኢፌዴሪ መንግስት ህዝባዊ በመሆኑ ከሁሉም በላይ ለዜጎቹ ችግር ፈጥኖ ደራሽ መሆኑ ሊታወቅ የሚገባ ይመስለኛል። ይህ ሁኔታም በዜጎች ላይ ችግር በተፈጠረ ቁጥር በሀገር ውሰጥም ይሁን በባህር ማዶ እየተገኘ ፈጣን ምላሽ በመስጠትና ተገቢውን ርምጃ መውሰዱ ለህዝቡ የሚሰጠው ከፍተኛ ክብር ምን ያህል እንደሆነ ያሳያል። መንግስት ሁሌም እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚያከናውነው መነሻውም ይሁን መድረሻው ከሚከተለው ህዝባዊ ወገንተኝነት የመነጨ ነው። ዜጎቹ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ በህገ ወጥነት በመገኘታቸው ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ስር ሳይወድቁ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረት የዚሁ ለህዝብ የወገነ መርሁ ነፀብራቅ ነው። ታዲያ በመንግስት በኩል ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው ጥረቶች ተጠናክረው የቀጠሉ ቢሆንም፤ ስደተኞቹም ይህን ጥረት ሊደግፉት ይገባል። እርግጥ አንድ ስደተኛ በስደት የሚኖርበትን ሀገር ህጋዊ አሰራሮችን ተከትሎ ህይወቱን መግፋት ካልቻለና በሀገሬው ህጋዊ አሰራር መሰረት “ህገ ወጥ” ተብሎ ከተፈረጀ፤ የሚኖረው የተሻለ አማራጭ ለሌሎች አደጋዎች ሳይጋለጥ በሰላም ወደ ሀገር ቤት መመለስ ይመስለኛል። ታዲያ ይህን ነባራዊ ዕውነታ በሳዑዲ የሚገኙት ዜጎቻችንም ሊረዱት ይገባል። በመንግስት ጥረት የተመቻቸላቸውን ሁኔታ ጊዜ ሳይሰጡ መጠቀምን ሁሌም ሊዘነጉት አይገባም። እናም በየአቅራቢያዎቻቸው በተዘጋጁላቸው ቦታዎች የጉዞ ሰነዶችን በመውሰድ ከህጋዊነት የሚገኘውን ጥቅም ሊያገኙ ይገባል እላለሁ።