Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በምድረ ቀደምቷ አገር እየተካሄደ ያለው የተመድ ቱሪዝም ጉባዔ

0 488

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 59ኛው የአፍሪካ ቱሪዝም ከፍተኛ ጉባዔ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በአፍሪካ የዘላቂ ቱሪዝም ልማት ላይ ያተኮረው ጉባዔ ከሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ቅርሶችን በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ አገር በሆነችው ኢትዮጵያ በሚካሄው ጉባዔ የአለም ቱሪዝም ድርጅት ፕሬዝዳንት ታሊብ ራፋይን ጨምሮ ከ300 ያላነሱ የውጭና የአገር ውስጥ ተሳታፊዎች ታድመዋል፡፡

በሪፖርት ይቀርባሉ ተብለው ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል በጥቅምት ወር መግቢያ በሞሮኮ የተፈረመው ቻርተር ይገኝበታል፡፡

ዘላቂ የአፍሪካ ቱሪዝም ልማት

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ በየጊዜው መካሄድ ከጀመረ ረጅም ጊዜ እንደሆነ ይታወቀል፡፡ ከዚሁ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ጎን ለጎን በሞሮኮ ማራካሽ ተካሂዶ በነበረው የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ስብሰባ በርካታ የአፍሪካ አገራት የቱሪዝም ቻርተር አጽድቀዋል፡፡

ቻርተሩ በአመዛኙ ዘላቂነትና ኃላፊነትን መርህ ያደረገ የዘርፉን ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት ያለመ መሆኑን የአለም ቱሪዝም መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ 24 በላይ አገራት የጸደቀው የቱሪዝም ቻርተር ስምምነት ዘላቂነት ያለው የቱሪዝም ዘርፍን፣ ተጠያቂነት ያለባቸውን አሠራሮች ለመተግበር የጋራ ማዕቀፍ ተደርጎ እንደሚወሰድ የአለም ቱሪዝም ድርጅት ሪፖርት ይጠቁማል፡፡

ሞሮኮ፣ የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አንጎላ፣ ቤኒን፣ ካሜሩን፣ ጊኒ ቢሳው፣ ኬብ ቬርዴ፣ ቡሩንዲ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ኮትዲቯር፣ ጋምቢያ፣ ጋቦን፣ ኬንያ፣ ማሊ፣ ሞውሪታንያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ናይጄሪያ፣ ኒጀር፣ ሴኔጋል፣ ሲሼልስ፣ ሱዳን፣ ዚምባብዌ፣ ቱኒዝያ እንዲሁም ቻድ የቱሪዝም ቻርተሩ ፈራሚዎች ናቸው፡፡

አገራቱ በቱሪዝም ሚኒስትሮቻቸው አማካይነት ቻርተሩን በማጽደቅ ወደ ተግባር ለመወለጥ መስማማታቸው ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ከቱሪዝም ልማት ጋር ተሰናስሎ መልካም የሚባሉ የቱሪዝም ዘርፉ ልምምዶች ከአካባቢ ጥበቃ እንዲሁም በእያንዳንዱ አገር ውስጥ ከሚገኘው የባህል ብዝሃነት አኳያ ተጣጥሞ የሚተገበርበት፣ ወጥ የሆኑ የቱሪዝም ሥራዎች መተግበሪያ መሣሪያ ሆኖ ቀርቧል፡፡

የቱሪዝም አለም አቀፋዊና አህጉራዊ ሁኔታ

የቱሪዝም ዘርፍ በአለም ደረጃ ለአገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለው ሚና እያደገ መምጣቱን የአለም ቱሪዝም ድርጅት ጥናት ያመለክታል፡፡ በተለይ ደግሞ ለአገራት የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆንና የስራ ዕድል የመፍጠር ሚናው እየጎላ መጥቷል፡፡

እኤአ በ2015 አለምን የጎበኙ የቱሪስቶች ቁጥር 1 ነጥብ 186 ቢልዮን መሆናቸውና ከዚህም 1 ነጥብ 26 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የአለም አቀፉ ቱሪዝም ድርጅት ያደረገው ጥናት ያመለክታል፡፡ እኤአ እስከ 2030 ድረስ የአለም አቀፍ ቱርስቶች ቁጥር ወደ 1 ነጥብ 8 ቢልዮን እንደሚያድግ ተመሳሳይ ጥናት ያመለክታል፡፡

ቱሪዝም በአለም ኢኮኖሚ ያለውን ፋይዳ ያጠናው ሌላው ድርጅ ኢርጎ ቱሪዝም (Ergo tourism) ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ በአማካይ ከአገራት 10 በመቶ ጠቅላላ አገራዊ ምርት ጋር እንደሚስተካከልና በአለም ደረጃ ከሚገኘው አስራ አንድ የስራ ዕድል አንዱ ከቱሪዝም ዘርፍ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

አፍሪካ የአለም አቀፍ ቱሪዝም ድርሻዋ እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም ካላት እምቅ የቱሪዝም አማራጮች አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን በአለም አቀፉ ቱሪዝም ድርጅት የተደረገ ጥናት ያመለክታል፡፡

እአአ በ2000 26 ሚሊዮን ገደማ የነበረው የአፍሪካ ጎብኚ ቱሪስቶች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ወደ 53 ሚሊዮን ቢያድግም ያለው አለም አቀፍ ድርሻ ከ5 በመቶ ያልበለጠ ነው፡፡ የዕድገት መጠኑ ፈጣን የተባለለት የአፍሪካ ቱሪዝም እኤአ እስከ 2030 የቱሪስቶች ቁጥር ከዕጥፍ በላይ በማደግ ከ134 ሚሊዮን እንደሚደርስ የአለም አቀፍ ቱሪዝም ድርጅት ትንበያ ይጠቁማል፡፡

ዘላቂ የቱሪዝም ልማት በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በተመሳሳይ ከፍተኛ የቱሪዝም ዕምቅ አቅም ያላት አገር ብትሆንም ከቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ መሆን ባለባት ልክ መጠቀም ሳትችል ቆይታለች፡፡

ኢትዮጵያ በአውሮፓ የቱሪዝምና የንግድ ምክር ቤት የ2015 ምርጥ የቱሪስት መዳረሻና የባህል ተመራጭ አገር በሚል መሸለሟ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ባደረጋቸው ተከታታይ የኢኮኖሚ ሪፎርሞች የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ እያደገ መምጣቱን የመንግስታቱ ድርጅት የአፍሪካ አኮኖሚክ ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል፡፡

በኢትዮጵያ እኤአ በ1990ዎቹ 64 ሺህ ገደማ የነበረው የቱሪስቶች ቁጥር በ2013 ከአስር ዕጥፍ በላይ በማደግ 680 ሺህ በላይ መድረሱን የኮሚሽኑ ጥናት ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ በመጪዎቹ አሥር ዓመታት የሚተገበር የቱሪዝም ማስተር ፕላን ይፋ ማድረጓን የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኮሚሽን ገልጿል፡፡

ማስተር ፕላኑ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ከጉብኝት ሥራዎች ጋር በተዛማጅነት ወደፊት ያስመዘግባቸዋል የተባሉ ዝርዝር ዕቅዶች የተካቱበት ነው፡፡ በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. በ2024 በየዓመቱ የ4.8 በመቶ ዕድገት በማስመገዝብ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስገኝና የአገሪቱን 3 ነጥብ 6 በመቶ ኢኮኖሚ ድርሻ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡

ከዚህ ባሻገር የተቀረጸው ማስተር ፕላን አምስት ሚሊዮን የሚጠጋ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችልበት አቅም እንዳለው ተገልጿል፡፡

በአሥር ዓመት ውስጥ አሥር ዋና ዋና የተግባር መስኮች የተለዩለት የኢትዮጵያ ዘላቂ የቱሪዝም ማስተር ፕላን፣ የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ቁጥር ወደ አምስት ሚሊዮን እንዲሆን፣ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢም 180 ቢሊዮን ብር የማድረግ ትልም አስቀምጧል፡፡

በአሥር ዋና ዋና ሥራዎች የተለየው ማስተር ፕላኑ ዘላቂና ተወዳዳሪ የቱሪዝም ዘርፍ በአገሪቱ እንዲፈጠር ለማስቻል መንግሥት የ5.3 ቢሊዮን ብር ወጪ መመደብ እንዳለበትም በማስተር ፕላኑ ተጠቅሷል ፡፡

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የባህል እና የሳይንስ ድርጅት ዩኒስኮ ዘጠኝ የሚዳሰሱና ሶስት የማይዳሰሱ ቅርሶችን በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀደሚ ሀገር ናት፡፡

አክሱም፣ ላሊበላ፣ ጎንደር፣ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፣ የታችኛው አዋሽ ስምጥ ሸለቆ፣ የታችኛው ኦሞ ስምጥ ሸለቆ፣ ኮንሶ፣ ጢያ እና ሀረር የሚዳሰሱ ቅርሶች ሲሆኑ፣ የመስቀል፣ የጨምበላላ በዓልና የገዳ ስርዓት የማይዳሰሱ የሀገሪቱ ቅርሶች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሌሎች ተጨማሪ ቅርሶችን ለማስመዝገብም ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የምትታወቅበትን “ኢትዮጵያ የአስራ ሶስት ወር ጸጋ” ልዩ የቱሪዝም ምልክት ወይም ብራንድ ወደ “ኢትዩጵያ ምድረ ቀደምት” መቀየሯ ይታወሳል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy