NEWS

በራስ አቅም የሚካሄደው የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሊመጣ የሚችለውን የዲፕሎማሲ ጫና ማቃለል አስችሏል —ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

By Admin

April 01, 2017

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፊል የግንባታ ስራ በራስ አቅም እየተካሄደ መሆኑ ሊመጣ የሚችለውን የውጭ ጫና እንዳቃለለ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል አስታወቁ።

የትግራይ ብዙሀን መገናኛ ተቋም የህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በመቀሌ ከተማ ያዘጋጁት የፓናል ውይይት ዛሬ ተካሂዷል፡፡

ሚኒስትሩ በፓናል ውይይቱ ወቅት እንዳሉት፣ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ግንባታ ሲታሰብ አብሮት ሊመጣ የሚችል የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲና ሌሎችንም ተፅኖዎች አስቀድሞ መለየት ተችሏል፡፡

በግልገል ጊቤ ሶስት ግድብ የግንባታ ፕሮጀክት ላይ ካጋጠሙት ፈተናዎች ትምህርት በመውሰድ ሥራውን ሙሉ በሙሉ ለውጭ ተቋራጮች ከመስጠት ይልቅ ከፊል ስራዎች በራስ አቅም እየተካሄደ በመሆኑ የተለያዩ ጫናዎችን መቀነስ አስችሏል፡፡

ሚኒስትሩ እንዳመለከቱት ሳሊኒ የሲቪል ስራዎች እንዲያከነውን ሲደረግ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎች ደግሞ በሃገር መከላከያ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ይህም ያጋጥም የነበረው የግንባታ መስተጓጎልና የውጭ ምንዛሪን ከመቀነስ ባለፈ ሌሎች ሜጋ ግድቦችን ለመገንባት የቴክኖሎጂና የእውቀት አቅም መገኘቱንም ጠቁመዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ አሁን 57 በመቶ የደረሰ መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ደብረጽዮን ፣ ” የፕሮጀክቱ አካል የሆኑ የሳድል ግድብ፣የኤሌክትሮ ሜከኒካል ስራዎችና ሌሎችን ጨምሮ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ከተጠናቀቁትም መካከል የሳብስቴሽንና ባለ 500 የሀይል ማስተላለፊያ ግንባታ ይገኝበታል፡፡

የግድቡ ግንባታ በጥሩ ፍጥነትና ምቹ በሆነ ሁኔታ መቀጠሉን ጠቅሰው እስከ አሁንም 50 ቢሊዮን ብር ወጪ መሆኑን ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡