Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሰብዓዊ መብት ጥሰት ጥያቄ የታጀበው የግብፅ ፕሬዚዳንት የአሜሪካ ጉብኝት

0 412

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ለግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በግብፅ የሚታየው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እስራት አግባብ እንዳልሆነና አሜሪካን ሥጋት ላይ እንደጣላት የተናገሩት እ.ኤ.አ. በ2014 ነበር፡፡

በግብፅ ለመጀመርያ ጊዜ በምርጫ ፕሬዚዳንት የሆኑትን መሐመድ ሙርሲ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን አስለቅቀውና እስር ቤት ከትተው መንበረ ሥልጣኑን የተቆናጠጡት አልሲሲ፣ ከሥልጣናቸው ጊዜ ጀምሮ የግብፅ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና ጋዜጠኞችን በማሰርም ይተቻሉ፡፡ ለግብፅ ኢኮኖሚ ማሽቆልቆልም እንደ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡ በግብፅ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመራከቱ ሳቢያ የኦባማ አስተዳደር የመከላከያ በጀት ድጎማ ከማድረግ አንስቶ የተለያዩ ትብብሮችን ነስቷቸው ቆይቷል፡፡

ግብፅ የአሜሪካ አጋር ብትሆንም አልሲሲ ሥልጣን ከያዙበት እ.ኤ.አ. ከ2014 ወዲህም ኦባማ ሥልጣን እስካስረከቡበት ጊዜ ድረስ ምድረ አሜሪካን ረግጠው አያውቁም፡፡

ግብፅና እስራኤል የፈረሙትን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ለግብፅ የምታደርገውን ወታደራዊ ዕርዳታ ያጠናከረችው አሜሪካ እ.ኤ.አ. 1979 እስከ 2003 ባለው ጊዜ ብቻ 19 ቢሊዮን ዶላር ሰጥታለች፡፡ ይህም አሜሪካ የኔቶ አባል ላልሆኑ አገሮች ከምታደርገው ወታደራዊ ድጋፍ ከእስራኤል ቀጥሎ ትልቁ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም ግብፅ ከአሜሪካ የ30 ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚያዊ ዕርዳታ አግኝታለች፡፡

ዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በገባበት እ.ኤ.አ. በ2009 ደግሞ የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊና የ250 ቢሊዮን ዶላር ኢኮኖሚያዊ ዕርዳታ ተደርጎላታል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2011 በግብፅ ተቀስቅሶ የነበረው አብዮት ግን በአሜሪካና በግብፅ መካከል የነበረውን ወታደራዊ ግንኙነት አሻክሮ ነበር፡፡ ግብፅን ከ30 ዓመታት በላይ የገዙት ሆስኒ ሙባረክ ከሥልጣን ወርደው መሐመድ ሙርሲ በምርጫ ሥልጣን እስከተቆናጠጡ ድረስ የነበረው ወታደራዊ ዕገዛም የጎላ አልነበረም፡፡ ሙርሲ እ.ኤ.አ. በ2012 የግብፅ ፕሬዚዳንትነትን ሥልጣን ቢይዙም፣ ዓመት እንዳገለገሉ ነበር በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን የተባረሩት፡፡ ይህን ያወገዘው የኦባማ አስተዳደርም አሜሪካ ለግብፅ የምትሰጠውን ወታደራዊ ዕርዳታ ከመሰረዝ ጀምሮ፣ ኤፍ 16 ተዋጊ ጄቶችንና ኤኤች – 64 አፓቼ ሔሌኮፕተሮችን ለግብፅ መከላከያ ሠራዊት ከመስጠት ተቆጥቦ ነበር፡፡

በግብፅ መንግሥት እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲኮንኑ የነበሩት ኦባማም፣ አሁን ግብፅን እየመሯት የሚገኙትን አልሲሲን ወደ አሜሪካ ጋብዘው አያውቁም፡፡

ግብፅን በቀጥታም ባይነካም በሙስሊም አገሮች ላይ ሁለት ጊዜ የጉዞ ማዕቀብ የጣሉት የአሜሪካ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ፣ ሥልጣን በያዙ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ውስጥ ከጋበዙዋቸው የአገር መሪዎች የግብፅ ፕሬዚዳንት ከቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡

በተያዘው ሳምንት መግቢያ ላይ ከግብፅ አቻቸው አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የተወያዩት ትራምፕ፣ ግብፅ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት የምታደርገውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፉና አብረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ትራምፕ፣ ‹‹ምናልባት ግልጽ ያልሆነ ነገር ካለ ሁሉም እንደሚያውቀው የምንፈልገው እኛ ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር መሆናችንን ነው፤›› ማለታቸውን  ኤቢሲ ዘግቧል፡፡

የግብፅ ፕሬዚዳንት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አመርቂ ሥራ መሥራታቸውን ለማውሳትም፣ ‹‹አሜሪካ ከግብፅና ከግብፅ ሕዝብ ጋር ናት፤›› ብለዋል፡፡

በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት መሐመድ ሙርሲን ገልብጠው ሥልጣን የተቆናጠጡት አልሲሲ የኦባማ አመራር የጉብኝት ግብዣ ያላደረገላቸው፣ በግብፅ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መበራከታቸውን ምክንያት አድርጎ ነበር፡፡ የሰብዓዊ መብት ቡድኖች የፕሬዚዳንት አልሲሲ መንግሥት 40 ሺሕ ያህል የፖለቲካ እስረኞች በቁጥጥር ሥር አውሎ እንደነበር፣ በአልሲሲ ላይ ተቃውሞ ከነበራቸው ውስጥ አንድ ሺሕ ያህሉ መገደላቸውን በመጥቀስ፣ የትራምፕ አልሲሲን መጋበዝ ትክልል አይለደለም ብለዋል፡፡

የሒውማን ራይትስ ዎች ዋና ዳይሬክተር ኬኔት ሮዝ፣ ትራምፕ በስብዓዊ መብት ጥሰት የሰላ ትችት የሚሰነዘርባቸውን አልሲሲ ‹‹እንኳን ደህና መጣህ›› ብለው መቀባቸውን አውግዘዋል፡፡

‹‹አልሲሲ ከ817 በላይ ዜጎችን ገድሏል፣ ብዙዎችን አሰቃይቷል፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ አስሯል፡፡ ትራምፕ ግን በትዊተሩ ‹አልሲሲ ታላቅ ጓደኛና የአሜሪካ ወዳጅ› ብሎ አስፍሯል፤› ሲሉም ሮዝ በምሬት ተናግረዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ተማጋቾችን አልሲሲ ይደፈጥጣሉ ተብለው ቢወገዙም፣ በትራምፕና በአልሲሲ መካከል በነበረው የአንድ ለአንድ ውይይት ይህ ስለመነሳቱ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ትራምፕ ግብፅና አሜሪካ ያልተስማሙባቸው ጥቂት ጉዳዮች አሉ ከማለት ባለፈ ስለጉዳዮቹ በግልጽ አላብራሩም፣ ትዊትም አላደረጉም፡፡

አሜሪካ ሁሌም ስለምታነሳውና በግብፅ ይካሄዳል ስለሚባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተነገረ ነገር የለም፡፡ ሆኖም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ ኒኪ ሐሌይ፣ ‹‹የትራምፕ አስተዳደር አሜሪካ በግብፅ ላይ ያላትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጀንዳ ወደ ጎን አይለውም፡፡ ምክንያቱም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በግብፅ ስላለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስናገር ሙሉ ለሙሉ ድጋፍ አግኝቼ ነበር፤››  ብለዋል፡፡

በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ አገሮች የአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ ግብፅ ከአሜሪካ በዓመት የ1.3 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ዕርዳታ ታገኛለች፡፡ በመሆኑም አሜሪካ ግብፅ የምትተችበትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንድታለዝብና ሽብርተኝነትን በመዋጋቱ ላይ እንድታተኩር ጥረዋል፡፡ ኤቢሲ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ የአሜሪካ ባለሥልጣን አናግሮ ነበር፡፡ ባለሥልጣኑ አሜሪካ ለግብፅ ተጨማሪ ዕርዳታ ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆነች መናገራቸውን አስፍሯል፡፡

አልሲሲ አሜሪካ ለግብፅ ተጨማሪ የገንዘብ ዕርዳታ እንድታደርግ የጠየቁ ሲሆን፣ ዕርዳታ የማያገኙ በመሆናቸው መበሳጨታቸው እንደማይቀርም ተገልጿል፡፡ እኚሁ ባለሥልጣን፣ ‹‹አሜሪካ ለግብፅ ተጨማሪ የገንዘብ ዕርዳታ አታደርግም፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የትራምፕ አስተዳደር የአሜሪካ አስተዳደር ካለው አጠቃላይ በጀት 28.7 በመቶውን ለመቀነስ አቅዷል፡፡ ይህም አሜሪካ ለአገሮች የምታደርገውን ዕርዳታ የሚጎዳው ሲሆን፣ ግብፅ በበጀት ቅነሳ ትገዳ አትጎዳ የታወቀ ነገር የለም፡፡  reporter

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy