Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በሳዑዲ ያለመኖሪያ ፍቃድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ እየተሰራ ነው

0 482

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት በሀገሪቱ ያለመኖሪያ እና የስራ ፍቃድ የሚኖሩ የውጭ ሀገራት ዜጎች በ90 ቀናት ውስጥ ያለቅጣት እንዲወጡ ባወጣው አዋጅ ኢትዮጵያውያን እንግልት ሳይደርስባቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ኮማንድ ፖስት አቋቁሜ እየተንቀሳቀስኩ ነው አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ አለም ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ሳዑዲ ዓረቢያ በሃገሪቱ ያለመኖሪያና ስራ ፍቃድ የሚኖሩ የውጭ ሃገራት ዜጎች በ90 ቀናት እንዲወጡ መደንገጓን አስታውሰዋል።

ቃል አቀባዩ መንግስት ኢትዮጵያውያን እንግልት ሳይደርስባቸው ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በቅርቡም በሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር አክሊሉ ገብረሚካኤል የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ ሳዑዲ አምርቶ በጉዳዩ ዙሪያ ከሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መወያየቱንም አንስተዋል።

ከውይይቱ በኋላ ዜጎች በቀላሉ መውጫ ቪዛ እንዲያገኙ በሳዑዲ መንግስት በኩል ተንቀሳቃሽ ጽህፈት ቤቶች እንዲከፈቱ መደረጉንም ገልጸዋል።

በሪያድና በጂዳ የሚገኙ ሚሲዮኖች የጉዞ ሰነድ አሰጣጥ ሁኔታ የተቀላጠፈ እንዲሆንና በጉዳዩ ዙሪያ ሊያጋጥሙ በሚችሉ መሰናክሎች ላይ ውይይት ተደርጓልም ነው ያሉት።

ውይይቱ በሳዑዲ ከሚኖሩ የኮሚዩኒቲ ማህበራትና የተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር የተደረገ ሲሆን፥ እስካሁን 4 ሺህ ህገ ወጥ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድ ወስደው 2 መቶዎች ወደ ሃገራቸው መግባታቸውንም አስረድተዋል።

ቃል አቀባዩ ቁጥሩ መግባት ከሚገባው አሃዝ አንጻር ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው፥ የመገናኛ ብዙሃንም የአዋጁን ምንነት በማሳየት በዜጎች ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር ለመቅረፍ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

በህገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው የገቡ ስደተኞች፣ ቋሚ ቦታ ሳይኖራቸው በመዘዋወር በህገ ወጥ መንገድ የሚሰሩ ስደተኞች፣ የስራ እና የመኖሪያ ፍቃድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የውጭ ሃገራት ነዋሪዎች፣ የስራ ፍቃድ ኖሯቸው ነገር ግን የመኖሪያ ፍቃድ መታወቂያ ካርድ የሌላቸው፣ ለዑምራና ሃጂ ሄደው በዚያው የቀሩ ወይም የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ነዋሪዎች እና ያለ ሃጂ ፍቃድ የተጓዙ አማኞች በሳዑዲ መንግስት ህገ ወጥ የሚባሉ ናቸው።

በአዋጁ የተሰጠውን የጊዜ ገደብ አክብረው የሚወጡ የውጭ ሃገራት ዜጎች፥ በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኙ የኢሚግሬሽን ጽህፈት ቤቶች የመውጫ ቪዛ እንዲያገኙ ይደረጋል።

ያለምንም ቅጣት በራሳቸው ትራንስፖርት ወጭ በፈቃደኝነት ከሃገሪቱ እንዲወጡ የሚደረግ ሲሆን፥ የጉዞ ሰነዶችን ከሚመለከታቸው አካላት ይወስዳሉ።

በጊዜ ገደቡ ውስጥ የሚወጡ በህጋዊ መንገድ ወደ ሳዑዲ መመለስ ይችላሉ፤ በመሆኑም ከሃገሪቱ በሚወጡበት ጊዜ የጣት አሻራ አይሰጡም።

ይሁን እንጅ የምህረት አዋጁ በወንጀል ተከሰው በቁጥጥር ስር የሚገኙትን አይመለከትም ነው የተባለው።

በአዋጁ የተሰጠውን ገደብ በማያከብሩት ላይ ደግሞ፥ የምህረት ጊዜው ሲጠናቀቅ በጸጥታ ሃይሎች የቤተ ለቤት አሰሳ ተካሂዶ፥ ህገ ወጥ ነዋሪዎች በህግ እንዲጠየቁ ይደረጋል።

ከዚህ ባለፈም ከሶስት ወር በፊት የወጣው የእስራትና የገንዘብ ቅጣት በህገ ወጥ ነዋሪዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።

ከምህረት ጊዜው መጠናቀቅ በኋላ ለህገ ወጦች ከለላ የሰጠ ወይም የቀጠረ ግለሰብ ወይም ተቋም በሃገሪቱ ወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት እንዲጠየቅ ይደረጋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy