Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በቀን አስር!!

0 783

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ሰሞኑን በመገናኛ ቡዙሃን እየተዘከረ ወይም እየተከበረ ያለ አንድ አንኩዋር ጉዳይ አለ፡፡ የትራፊክ አደጋን በጋራ ለመከላከል ያስችል ዘንድ ታስቦ የተሰናዳ ነው፡፡

ከጥር 22 ቀን 2009 ጀምሮ እስከ ግንቦት 7/2009 ድረስ  “ከትራፊክ አደጋ የፀዳ የትራንስፖርት አገልግሎት ለሀገራዊ ህዳሴ” በሚል መሪ ቃል ነው እየተዘከረ ያለው፡፡

እኛም ይህን አሳሳቢ ጉዳይ መሰረት አድርገን በፍትህና ህግ ዘገባችን ልንዳስሰው ሞከርን! እነሆ!!

የትራፊክ አደጋ በተለይ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት አሳሳቢ መሆኑን የአለም ባንክና የዓለም ጤና ድርጅት በጋራ ባወጡት መግለጫ መግለጻቸው የሚታወስ ነው፡፡

ተቋማቱ በ2015 ባወጡት ሪፖርት መሰረት በአካባቢው ሀገራት በየቀኑ ከአምስት እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚሆኑ ህፃናት ህይወታቸውን በጎዳና ላይ በዚሁ አደጋ እንደሚያጡና ከዚህ ቀደም በአካባቢዎቹ ገዳይ ከሚባሉት ወባና ሌሎች በሽታዎች በላይ ገዳይ እየሆነ መምጣቱን ይጠቁማሉ፡፡

ወደ ሀገራችን ኢትዮጵያም ስንመጣ ለዓብነት ብንጠቅስ ባለፈው 2008 ዓ.ም ብቻ በትራፊክ አደጋ ከሶስት ሺሀ ስምንት መቶ በላይ ዜጎች ህይወታቸውን ማጣታቸውን የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን የወጣው ሪፖርት ያሳያል፡፡

ሪፖርቶቹን እዚህ ጋር ገታ አደርገን ወደ ፍትህ ስርዓቱ ጎራ ስንል ከሚገኙ በርካታ ፋይሎች አንድ ሁለቱን እንይ፡፡

ፋይሎቹን ያገኘነው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሲሆን ከሳሽ የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ነው፡፡

ተከሳሽ ወርቁ አሰፋ ይባላል፡፡ የተከሰሰበት ወንጀል ደግሞ ሾፌር በመሆኑ የሌላ ሰው የህይወት ደህንነት የመጠበቅ የሙያ ግዴታ እያለበት በቸልተኝነት ነሀሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም በግምት ከምሽቱ 2፡00 /ሁለት ሰዓት/  ሲሆን የሚያሽከረከረውን የአንበሳ አውቶቡስ ደህንነት ሳያረጋግጥና የቴከኒክ ችግር ያለበት መኪና በመንዳት በነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን የክሱ መዝገብ ያስረዳል፡፡

በዚህም ሳቢያ በእለቱ ከሽሮ ሜዳ ወደ ኪዳነምህረት በሚወስደው መንገድ ኪዳነምህረት ጠበል ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ግራ መስመራቸውን ይዘው ይጉዋዙ የነበሩ ዳንዔል ገበየሁ፤ ዘሪሁን ጉዱ፤ አስራት ማሞ ፤ ሮማን ማሞ ፤ ድርብነሽ ተክሌ ፤ ምስራቅ ምስጋናው እና አስራተ ማሪያም የተባሉ  ሰባት ግለሰቦችን በመግጨት ህይወታቸው እንዲያልፍ በማድረጉ በፈፀመው በቸልተኝነት ሰውን የመግደል ወንጀል ክስ ሊቀርብበት ችሏል፡፡

ይህም በ1996 ዓመተ ምህረት የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 572 በመተላለፍ የተመሰረተው ክስ የተከሳሽን የቤተሰብ ሁኔታና ሌሎች የቅጣት ማቅለያ ደንቦችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚታሰብ ስምንት ዓመት ከአራት ወር ፅኑ እስራት እና ሁለት ሺህ ብር ቅጣት በመጣል ፋይሉን ዘግቷል፡፡

ተመሳሳይ ባይሆንም አንድ አነስ ያለ የቅጣት ውሳኔ የተጣለበትን ፋይል እንመልከት፡፡ ከሳሽ  አሁንም የፌደራል ዓቃቤ ህግ ሲሆን ተከሳሽ ደግሞ አዳነ ጌታቸው ይባላል፡፡

የክስ መዝገቡ እንደሚያትተው ከሆነ ተከሳሽ የሰውን ህይወት እና ደህንነት የመጠበቅ የሙያ ግዴታ እያለበት ይህን ባለማድረጉ በታህሳስ 3 /2007 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ  አንድ ሰዓት ሲሆን ቄራ አካባቢ ልዩ ቦታው ቄራ መስጊድ አካባቢ በመንገዱ ላይ ከቀኝ ወደ ግራ ትጓዝ የነበረችውን ስሟ ያልታወቀውን ሟች የመንገዱንና የትራፊኩን እንቅስቃሴ መሰረት አድርጎ በማሽከርከር ቅድሚያ ሰጥቶና ጥንቃቄ አድርጎ  ሊያልፍ ሲገባው ይህን ሳያደርግ በመኪናው የፊት የግራ ክፍል ሟችን በመግጨት ባደረሰባት ጉዳት ህይወቷ እንዲያልፍ ማድረጉን ያትታል፡፡

በዚህም ሳቢያ በተከሰሰበት በቸልተኝነት የሰው መግደል ወንጀል ክስ የቅጣት ውሳኔ አግኝቷል፡፡

የቅጣት ውሳኔው እንደሚያስረዳው ከሆነ ተከሳሹ ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የወንጀል ድርጊት የሌለው በመሆኑ የቤተሰብ አስተዳዳሪነቱን እና ተከሳሹ ሟችን ከወደቀችበት አንስቶ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በመውሰድ  ህክምና እንድታገኝ ሙከራ ማድረጉ በመረጋገጡ የወንጀሉን ድርጊት ያቀለለት መሆኑን ያብራራል፡፡

በመሆኑም ተከሳሹ  በስድስት ወር ቀላል እስራትና በአንድ ሺህ ብር እንዲቀጣ ውሳኔ በመስጠት ፋይሉን ዘግቷል፡፡

እዚህ ጋር የቅጣት ውሳኔው በእጅጉ እንዲቀል ካደረገው ነጥብ አንዱ ከደረሰው አደጋ በሁዋላ ህይወትን ለማዳን የተደረገው ጥረት ይመስለኛል፡፡

በተለይ በምሽት በመኪና አደጋ የሚቀጠፉ ሰዎች በአብዛኛው ህይወታቸው የሚያልፈው አደጋ አድርሰው ጥለው በሚሸሹ አሽከርካሪዎች ሳቢያ መሆኑ ሲነገር ይሰማል፡፡ በተለይ ጠጥተው በሚያሽከረክሩ ግለሰቦች አማካይነት መሆኑ ነው በስፋት የሚነገረው፡፡

በቅርቡ የገጠመኝን አንድ የአደጋ ወሬ ላውጋችሁ ጉዋደኛዬ በዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነው፡፡ ዝዋይ የምትኖር አንድ አብሮ አደግ እህት አለችው፡፡ ያደጉት ደብረብርሃን አጎታቸው ጋር መሆኑን አጫውቶኛል፡፡

ታድያ እኚህ አሳዳጊ አጎቱ ይታመሙና ደብረብርሃን ሄዶ ጠይቆ ሲመለስ ዝዋይ ለምትኖረው መሰሉ ይነግራትና ወደ ዲላ ይወርዳል፡፡

ነዋሪነቷን በዝዋይ ለበርካታ አመታት ያደረገችወና በንግድ ስራ የምትተዳደረው መሰል ታድያ የእረፍት ቀኗን ለመጠቀም እሁድን ጠብቃ በአባዱላ ተሳፍራ ወደ ደብረብርሃን ጉዞ ትጀምራለች፡፡

ዳሩ ምን ያደርጋል አዲስ አበባም ሳትደርስ ገና በንጋቱ 12 ሰዓት ላይ 12 ሰዎችን ጭኖ ይበር የነበረው አባዱላ የህዝብ ማመላለሻ ‹‹ቀይ ሽብር›› የሚል ቅጥያ ከተሰጠው ሲኖ ትራክ ጋር ይገጣጠማል፡፡ ይህ ጣዕረ ሞት የተጫጫነው ሲኖ በፍጥነት ከሚሽከረከረው አባዱላ ጋር ይላተማል፡፡ በዚሁ ዘገናኝ አደጋም በተሸከርካሪው  ውስጥ የነበሩ 12ቱም ሰዎች በዛ የእረፍት ቀን መጀመሪያ በደንብ እንኩዋን መንጋቱን ሳያዩ ላይመለሱ እስከወዲያኛው ተሰናበቱ፡፡

ነዋሪነቷ ዝዋይ እድገቷ ደግሞ ደብረብርሃን የሆነችው አመለ ሸጋዋ መሰሉ በሁለቱ ከተሞች የሚያውቋትን ነዋሪዎች እምባ ካስረጨች ሶስት ወር እንኩዋን እንዳልሞላት ነበር ያጫወተኝ ጓደኛዬ ፡፡

በኢትዮጵያ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣው የትራፊክ አደጋ በቀን ከሚሞቱት 10 ሰዎች በተጨማሪ 31 ሰዎች ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ የትራንስፖርት ባለስልጣን ከሚያወጣው ሪፖርት መረዳት ይቻላል፡፡

ታድያ በቀን 10ን እና 31ን በዓመት ሲያሰሉት አያስፈራም ለዚህም ሁሉም ህብረተሰብ ክፍል ተሳታፊ መሆን የሚችልበት የንቅናቄ መድረኮች በየጊዜው ሊፈጠሩ ይገባል መልእክታችን ነው፡፡

ሚስባህ አወል

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy