CURRENT

በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ለደረሰው ጉዳት የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር አባላት በሕግ እንዲጠየቁ ሐሳብ ቀረበ

By Admin

April 08, 2017

‹‹ጠባቂዎች እስረኞች ላይ የተኩስ እሩምታ ከፍተው ነበር››

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን

ነሐሴ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከደረሰው የእሳት አደጋ ጋር በተያያዘ በሕግ በመጠየቅ ላይ ከሚገኙት በተጨማሪ የማረሚያ ቤቱ የጥበቃ አስተዳደር አባላት በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለሕዝብ  ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳቡን አቀረበ፡፡

ኮሚሽኑ የአደጋውን መንስዔና ጉዳት በመመርመር ሪፖርቱን ለምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቡዕ መጋቢት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. አቅርቧል፡፡

አመፁንና ቃጠሎውን እንደቀሰቅሱ የተጠረጠሩ ታሳሪዎች ሊጠየቁ እንደሚገባ የገለጹት ኮሚሽነር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር)፣  የማረሚያ ቤቱ የጥበቃ አባላትና ኃላፊዎችም በተመሳሳይ ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

‹‹ሳምንቱን ሙሉ ረብሻ ሊነሳ እንደሚችል የሚያሳዩ ምልክቶች ነበሩ፤›› ያሉት ኮሚሽነሩ፣ እሳቱን ለማቀጣጠል የተጠቀሙባቸው ቁሶችም ኃላፊነታቸውን በዘነጉ የጥበቃ አባላት ሊገቡ መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አብዛኞቹ (እስረኞች) ከእሳቱ ራሳቸውን ለማዳን ከማጥፊያ ክፍሎቻቸው ለመውጣት ሲጥሩና በጩኸት ዕርዳታ ሲጠይቁ፣ የጥበቃ አባላት የተኩስ እሩምታ እንደከፈቱባቸው ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ስምንት ታራሚዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸው፣ ጠባቂዎቹ ተለይተው በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ምርመራውን ሲያደርግ አመፅኑና እሳቱን በማስነሳት የተጠረጠሩትን ታሳሪዎች ስለማነጋገሩ የተጠየቁ ቢሆንም ምላሽ ሳይሰጡ አልፈዋል፡፡

ኮሚሽነሩ ያቀረቡት ሪፖርት በድጋሚ ማክሰኞ ሚያዝያ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፓርላማው ጠቅላላ ጉባዔ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡ በፓርላማው የአሠራርና ሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት ለፓርላማው ጠቅላላ ጉባዔ ሪፖርት ሊቀርብ የሚችለው በሕግ መሠረት መንግሥታዊ አካሉ ለፓርላማው በቀጥታ ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ ካለበት፣ መንግሥታዊ አካሉ አንገብጋቢ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ መስጠቱ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ መንግሥታዊ አካሉ ላይ ከፓርላማው አባላት ተደጋጋሚ ጥያቄዎች የሚነሳ ከሆነ፣ እንዲሁም መንግሥታዊ አካሉ ለቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ሲያደርግ ወይም በኮሚቴው የክትትልና የቁጥጥር ሒደት መሠረታዊ ችግር የታየበት ከሆነ ነው፡፡