NEWS

«በባሕላዊ መንገድ የተመረተው ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በአግባቡ እየቀረበ አይደለም» – አቶ ሞቱማ መቃሳ የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር

By Admin

April 07, 2017

በወርሃ መስከረም መጀመሪያ የተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በአዲስ መልክ እንዲዋቀሩ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የቀድሞው ማዕድን ሚኒስቴር አሁን የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በሚል መቀየሩ ይታወሳል፡፡ የማዕድን ዘርፉ ለውጪ ምንዛሪ ከሚያስገኘው ከፍተኛ ጥቅም አንፃር ይበልጥ ትኩረት እንዲያገኝ ቢደረግም፤ በዓመቱ አጋማሽ የተካሄደው ግምገማ የሚያሳየው ብዙ እንደሚቀረው ነው፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ይቀመጣሉ፡፡ እኛም በዚህና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡

አዲስ ዘመን፦ በዘንድሮ የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት መሰረት የማዕድን ዘርፍ ኢንቨስትመንት መጠን ከ256 ሚሊዮን ብር በላይ ለማድረስ አቅዳችሁ፤ ያሳካችሁት 33 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ወይም 13 በመቶ አካባቢ ነው፤ የአፈፃፀሙ ማነስ የዘርፉን እምቅ አቅም በአግባቡ ካለማስተዋወቅ ጋር ይያያዝ ይሆን?

አቶ ሞቱማ፡– ትክክል ነው፤ የማዕድን ልማት ሀብቱን ለመጠቀም የመጀመሪያው ነገር ሀብቱን በሚገባ ማወቅ ነው፡፡ ምን አለን? የት ? ምን ያህል አለን? የሚለውን ማወቅ የግድ ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ከታወቀ በኋላ በዓለም ላይ ላሉት ኩባንያዎች ማስተዋወቅ መቻል ነው፡፡ እንደሚታወቀው የማዕድን ሀብት ልማት ትልቅ ካፒታል የሚጠይቅ ነው፡፡ በቀላሉ የሚሰራ አይደለም፡፡ ብዙ ዓመትና ብዙ ካፒታል ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ይሄን በአግባቡ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለንን የማዕድን ሀብት በሙሉ ገና አውቀን አልጨረስንም፡፡ በርካታ ስራዎች ይጠብቁናል፡፡ የማዕድን ሀብት እምቅ አቅም የመለየት ጥናቱ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡

በኢንቨስትመንት በኩል አነስተኛ አፈፃፀም ለተባለው ግን እንደጠቀስኩት ዘርፉ ብዙ ሀብት መጠየቁ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ከዓለም ገበያ ዋጋ ጋር የሚሄድ በመሆኑ ነው፡፡ ለምሣሌ የወርቅ ልማት ከዓለም የወርቅ ገበያ ጋር የሚሄድ ነው፡፡ ገበያው ከፍ እያለ ሲሄድ ብዙ ኢንቨስተሮች ይመጣሉ፤ ወደዚህ ይሳባሉ፡፡ ዋጋው ዝቅ ሲል ደግሞ ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ ፈጣን አይደለም፡፡

ከነዳጅ ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ገበያ አሁን ዋጋው ዝቅተኛ ነው። ከውጪ ስለምናስገባ ለእኛ የነዳጅ ዋጋ መቀነስ ለኢኮኖሚያችን ጥሩ ቢሆንም፤ በሌላ በኩል በነዳጅ ፍለጋ ላይ የሚሰማሩ ኩባንያዎችን ከመሳብ አንፃር ደግሞ አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ኩባንያዎች ገበያውን አይተው ነው የሚሳቡት፡፡ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ኩባንያዎቹ ይሳባሉ፡፡ ስለዚህ የማዕድን ዘርፍ ከዓለም ገበያ ጋር የመዋዠቅ ባሕሪ አለው፡፡ አፈፃፀሙ ዝቅተኛ መስሎ የሚታየውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ አፈፃፀሙ በተፈለገው ልክ ያልመጣውም በነዚህ ምክንያቶች ነው፡፡

አዲስ ዘመን፦ በአጠቃላይ በዘርፉ የታየው አነስተኛ አፈፃፀም የተጠቀሱት ጉዳዮች ብቻ ውጤት ነው?

አቶ ሞቱማ፦ ሁሉም ባይሆንም በአብዛኛው ተያያዥ ነው፡፡ ዘርፉ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ በርካታ ኩባንያዎች ይመጣሉ፤ ይጠይቃሉ፡፡ በተለያዩ መድረኮችም ተገኝተን እናስረዳለን፡፡ ምላሻቸው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን መጥተው ወደ ስራ በመግባት ላይ መጓተት አለ፡፡

አዲስ ዘመን፦ በዚህ ዓመት ምን ያህል አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ ገብተዋል?

አቶ ሞቱማ፡– ቀደም ሲል የነበሩ እንጂ አዲስ የመጡ የሉም፡፡ ነገር ግን በፊትም የነበሩ ትላልቅ በነዳጅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩ ስምንት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እየሰሩ ነው፡፡ በወርቅ ፍለጋ ላይ የተሰማሩም አሉ፡፡ ለማምረት የሚያስችላቸውን ፈቃድ ለማውጣትም ሂደት ላይ ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡– የወርቅ ኮንትሮባንድ ንግድ እና በድንበር አካባቢ የሚታይ ሕገወጥ የማዕድናት ዝውውር መስፋፋት አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ከፍተኛ ጥቅም እያሳጣት መሆኑን በቅርቡ ተገልጿል፤ ይሄን ለመከላከል ምን አይነት መፍትሄዎች እየተወሰዱ ነው?

አቶ ሞቱማ፡– አገሪቱ ከምታመርተው አጠቃላይ የወርቅ ሀብት 60 በመቶ የሚመረተው በባሕላዊ አምራቾች በኩል ነው፡፡ ይሁንና በባሕላዊ መንገድ የተመረተው ወርቅ በአግባቡ ወደ ብሔራዊ ባንክ እየቀረበ አይደለም፡፡ ምርቱ ቢኖርም በኮንትሮባንድ ንግድ እየወጣ ነው፡፡ የባሕላዊ ምርቱ የሚከናወንባቸው ክልሎች አምስት ኦሮሚያ፣ ትግራይ፣ ቤኒሻንጉል፣ ደቡብ እና ጋምቤላ ናቸው።

ወርቅ በብዛት የሚገኘውና የሚመረተው ጠረፍ በሆኑ አካባቢዎች ነው፡፡ ከእዚህ ጋር ተያይዞ የተመረተውን ምርት ወደ ባንክ ከማቅረብ ይልቅ ወደ ውጪ በኮንትሮባንድ የመሸጥ ሁኔታ ይታያል፡፡ ይሄንን ችግር ለመግታት አገራዊ ንቅናቄ ተጀምሯል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው፡፡ የሁሉንም ትኩረትና ርብርብ ይጠይቃል፡፡ በተለይ ደግሞ የአካባቢዎቹ አስተዳዳሪዎች መስጠት የሚገባቸው ትኩረት ከፍተኛ መሆን ይገባዋል፡፡ አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጪ ምንዛሪ ሳታገኝ በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ የሚሄድበት ሁኔታ እየታየ ነው፡፡ ችግሩ በሚፈለገው ደረጃ እየተገታ አይደለም፡፡

አዲስ ዘመን፦ ችግሩን ለመፍታት ከክልሎች ጋር በመሆን የተከናወኑ ተግባራት አሉ?

አቶ ሞቱማ፦ የሁሉንም አካላት ቅንጅት ይጠይቃል፡፡ የአካባቢ አስተዳደር፣ የክልል ኃላፊዎች፣ ፖሊስ እንዲሁም ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የጋራ ስራ ነው፡፡ እስከአሁን ለችግሩ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ ነበር፡፡ ባሕላዊ አምራቾቹ ብሔራዊ ባንክ ወርቁን ከሚገዛበት ትንሽ ጭማሪ ካገኙ ለሌላ ወስደው ይሸጡታል፡፡ በፊት በባንኮች ተደራሽ አለመሆን ምክንያት ችግሩ ያጋጥም ነበር፡፡ አሁን ግን ይሄ እየተፈታ ይገኛል፡፡

ከክልሎች ጋር በቅርበት የሚሰራበት ድጋፍ አለ፡፡ ግንዛቤ መፍጠሩ ላይ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከሕብረተሰቡና ዘርፉ ላይ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላትም ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ መፍትሄ የሚሆነውም ይሄ ነው፡፡ ሁሉም ተቀናጅቶ የዚህን ጉዳት በመገንዘብ ወርቅ ወደ ጎረቤት አገር ከማሸሽ ወደ ባንክ ቢመጣ ለአገር ጠቀሜታ እንደሚኖረው መታወቅ አለበት፡፡

በነገራችን ላይ ብሔራዊ ባንክ ወርቅ የሚገዛው በዓለም አቀፍ ዋጋ አይደለም፡፡ በዓለም ገበያ ላይ አምስት በመቶ ጭማሪ አድርጎ ነው፡፡ ይሄ የተደረገው ወርቁን ለአገር ኢኮኖሚ በአግባቡ መጠቀም ስለሚያስፈልግና የውጪ ምንዛሪ እጥረቱን ይቀርፋል ተብሎ ስለታመነ ነው፡፡ ነገር ግን ጭማሪ ተደርጎም ወርቅ ወደ ሕገወጥ ንግድ እየሄደ ነው፡፡ ለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ ወርቅ ለምንድነው ነጋዴዎች ወደ ውጪ የሚወስዱት? የሚለው ችግር መታወቅ አለበት፡፡ እኛም ትኩረት አድርገን እየሰራን ያለነው ችግሩ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ ለወጣቶቹ የማምረቻ ሼድ እና መሸጫ ቦታ በሚኒስቴሩ ድጋፍ እንዲሁም በክልሎች ፈፃሚነት እየተሰራ ይገኛል፡፡

አዲስ ዘመን፡– በአፋር ክልል የፖታሽ ማዕድን ልማት ላይ ተሰማርተው የነበሩ ኩባንያዎች ፕሮጀክት አቋርጠው መውጣታቸው ይታወቃል፤ ለማቋረጣቸው ‹‹የመሰረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ ከመንግስት በቂ ድጋፍ አልተደረገላቸውም›› የሚል ምክንያት እንደተሰጠ ይነገራል፤ እርግጥ ምክንያቱ ይህ ነው?

አቶ ሞቱማ፡– ኢትዮጵያ ሰፊ የፖታሽ ሀብት አላት፡፡ ይሄን ሀብት ለመጠቀም በቅርቡ ሦስት ኩባንያዎች ተሰማርተው ነበር፡፡ ከሦስቱ መካከል አንደኛው ስራውን አቋርጦ እየወጣ ነው፡፡ የወጣበት ምክንያት የመሰረተ ልማት አለመሟላት አይደለም፡፡ ኩባንያው ይሄን ሊል ይችላል፡፡ ነገር ግን እርሱ ብቻ አይደለም መሰረተ ልማት የሚፈልገው፡፡ እንዲያውም ከሌሎች አገሮች በተለየ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት ለአልሚዎች መሰረተ ልማት በመዘርጋት ላይ ይገኛል፡፡ በብዙ አገሮች እነዚህን መሰረተ ልማቶች የሚዘረጉት ባለሀብቶቹና ኩባንያዎቹ ራሳቸው ናቸው፡፡

እዚህ ግን ቶሎ እንዲለማ ስለምንፈልግ መሰረተ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ ብቸኛ መንግስት ነው ሊባልም ይችላል፡፡ ይሄ ስራ የሚከናወነው በሚኒስቴር መስሪያ ቤት ብቻ አይደለም፡፡ መንገድ ከሆነ ትራንስፖርትን፤ የኃይል አቅርቦት ከሆነ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ እና ሌሎችም ያሉት አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን ይከታተላል፡፡ ይሄን ተሞክሮ ለሌሎች አገሮች በምናጋራበት ወቅት ከፍተኛ አድናቆት ይሰጠዋል፡፡ ጥራትም ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ለምሣሌ የአገሪቱ የመንገድ ደረጃ (ስታንዳርድ) ከ58 በላይ መሸከም አይችልም ነበር፡፡ ነገር ግን ለፖታሽ አምራች ኩባንያዎች በማሰብ ግን 78 ቶን የመሸከም አቅም እንዲኖረው ተደርጎ ነው እየተሰራ የሚገኘው፡፡ ይሄ የሚያሳየው መንግስት ምን ያህል ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት እየሰጠ እንደሚገኝ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡– ስለዚህ አቋርጦ ለመውጣቱ የተሰጠውን ምክንያት አትቀበሉትም?

አቶ ሞቱማ፡– አንቀበለውም፡፡ በእኛ በኩል ሁሉንም ኩባንያዎች የምንመለከተው በእኩል ደረጃ ነው፡፡ በጥሩ ሁኔታ እየሰሩ የሚገኙም አሉ፡፡ ለፕሮጀክት ማቋረጥ የመሰረተ ልማት ጉዳይ ግን ምክንያት ሊሆን አይገባም፡፡

አዲስ ዘመን፡– በዘርፉ የሚስተዋለው አንዱ ችግር የገበያ ትስስሩ በቂ አለመሆን ነው፤ ይሄን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረት አለ?

አቶ ሞቱማ፡– ባሕላዊ አምራቾች ላይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል፡፡ ግን በቂ አይደለም፡፡ እራሳቸው ድርጅቶች ፈልገው የሚያገኟቸው ገበያዎች አሉ፤ በዚህ መንገድ ብዙ የጌጣጌጥ ምርቶች ወደ ውጪ ይላካሉ፡፡ ሂደቱ ግን በእኛ በኩል ነው የሚመቻቸው፤ ወደተለያየ አገር እንዲሄድ የሚፈቅደውና ድጋፍ የሚያደርገው ሚኒስቴሩ ነው፡፡ ገበያ ማፈላለጉ ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ ዳይሬክቶሬት አለ፡፡ በበቂ ሁኔታ አልሰራንም፡፡ ወደፊት አጠናክረን መሄድ አለብን፡፡ ካልሆነ ግን ያለአግባብ ለሕገወጥ አሰራር የሚጋለጡ ማዕድናት ይኖራሉ፡፡

አዲስ ዘመን፡– የማዕድን ዘርፍ በስፋት ተጠቃሚ ከሚያደርጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ወጣቶች ይጠቀሳሉ፤ የኦሮሚያ ክልል በቅርቡ ‹‹የኢኮኖሚ አብዮት›› በሚል የጀመረው ለውጥ አለ፤ ይሄ ጅምር ከባለሀብቶች ፍላጎት ጋር እንዳይጋጭ ከክልሉ ጋር የተደረገ ውይይት አለ?

አቶ ሞቱማ፡– የአገሪቱ ልማት በተቻለ መጠን ሁሉንም ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ መከናወን አለበት የሚል የጋራ እምነት አለ፡፡ ከዚህ አኳያ በግል ኩባንያዎችም ሆነ በመንግስት የሚሰሩ የዘርፉ ልማቶች የሚንቀሳቀሱበትን አካባቢ ሕብረተሰብ ተጠቃሚ ማድረግ አለባቸው፡፡ አገሪቱንም ተጠቃሚ ማድረግ አለበት፡፡ በቅርቡም ከወጣቶች ስራ ማጣት ጋር በተያያዘ የተነሱ ጥያቄዎች ተከትሎ የደረሱ ጉዳቶች እናስታውሳለን፡፡ በመሆኑም ለወደፊት ወጣቶቹን ወደ ስራ ማስገባት የግድ ይላል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በዋናነት የሚነሱ መሰረታዊ ጉዳዮች የአካባቢውን ሕብረተሰብ ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ነው፡፡ ይሄን ስንል ግን ድርጅቶቹን በማጥፋት ወይም በመዝጋት አይደለም፡፡ ድርጅቶቹም ሳይጎዱ፤ ወጣቶቹም ስራቸውን ሳያጡ እንዴት ነው በጋራ መጠቀም የሚቻለው? በሚል ነው የኦሮሚያ ክልል እየሰራ የሚገኘው፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ወጣቶችን እንዴት ተጠቃሚ ያደርጋሉ በሚለው ላይ ከክልሉ ጋር ብዙ ጊዜ ውይይት ተደርጓል፡፡

አዲስ ዘመን፡– በዓለም ባንክ በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ የጃፓን ማሕበራዊ ልማት ፈንድ ፕሮጀክት ከ36 ሚሊዮን ብር በላይ ቢመደብም እስከ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ የተጠቀማችሁት ስድስት ሚሊዮን ብር እንደማይሞላ ሚኒስቴሩን ለሚከታተለው ቋሚ ኮሚቴ ባቀረባችሁት ሪፖርት ጠቅሳቹሃል። አሁን የፕሮጀክቱ ጊዜ ተጠናቅቋል፤ የበጀት አጠቃቀሙ ለምን ዝቅተኛ ሆነ?

አቶ ሞቱማ፡– ይሄ መረሃግብር የተጀመረው እ.አ.አ ህዳር 2011 ነበር፡፡ ስድስት ዓመት ሞልቶታል፡፡ በተባለው ጊዜ ባለመጠናቀቁም አንድ ጊዜ እንዲራዘም ተደርጎ ነበር፡፡ አሁን መጨረሻው ላይ ይገኛል፡፡ የተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎች አሉ፡፡ መጀመሪያ ወደ ስራ ሲገባ የፍላጎት ጥናት ተካሂዶ ነበር፡፡ ሁለተኛ ላይ የተከናወነው የአቅም ግንባታ ስራ ነው፡፡ የአቅም ግንባታው በጥሩ መልኩ ቢከናወንም ግዢው ግን ተጓትቶ ነበር፡፡ አንዱ ችግርም ይሄ ነው፡፡ ፕሮግራሙ የሚሰራው በባሕላዊ አምራቾች በተለይም ሴቶች ላይ በመሆኑ ስራቸውን ቀላል ለማድረግ መገዛት የነበረባቸው ግብዓቶች ነበሩ፡፡ ይሄን ግዢ በወቅቱ በማከናወን በኩል ችግሮች ታይተዋል፡፡

ሦስተኛው ደግሞ ‹‹ዋሽ›› የሚባለው የመጠጥ ውሃ እና ሳኒቴሽን ፕሮግራም ነው፡፡ ይሄም በብዙ ቦታዎች ቢሰራም አንዳንዶቹ በተለያዩ ምክንያቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አልተጠናቀቁም፡፡አራተኛው ነገር መርሃግብሩን ማስተዳደር ነው፡፡ ከመጀመሪያው ፕሮግራሙ ሲነደፍ ችግሮች ነበሩበት፡፡ ሚኒስቴሩ ምን ይፈፅማል? የክልሎች ድርሻ ምንድነው? የሚሉት ነገሮች ላይ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ እነኚህ ክፍተቶች በየጊዜው እየተዘጉ መምጣት ነበረባቸው፡፡ ምን ተይዞ ምን መፈፀም አለበት? የሚለውም በደንብ አልተጨበጠም፡፡ በክልሎች ደረጃ የትኩረት ማነስ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማዋቀርና ለክልሎች በማስተዋወቅ የተሻለ ስራ ተከናውኗል፡፡

በጀቱንም ከዚህ አንፃር ለመጠቀም ተሞክሯል፡፡ አሁን በሰራነው መልኩ ባለፉት አራት ዓመታት ሰርተን ቢሆን ይሄ ብር ብዙ አልነበረም፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በደንብ ተከታትለን አልፈጸምንም፡፡ በክልልም ሆነ በሚኒስቴሩ የታየው ችግር ይሄ ነበር፡፡ አሁን ግን በተሻለ ደረጃ ሄደናል ማለት ይቻላል፡፡ ከተመደበውም በጀትም ትንሽ ገንዘብ ቢቀር ነው፡፡ ወደ ግዢ ገብተናል፤ ሌሎች መሰራት ያለባቸው ነገሮችም ከዓለም ባንክ ጋር ተነጋግረን እናጠናቅቃለን፡፡ ነገር ግን የተወሰነ ገንዘብ ሊቀር ይችላል፡፡

አዲስ ዘመን፡– ፕሮግራሙ ሲነደፍ ጀምሮ ችግሮች ከነበሩ እንዴት ሊተገበር ቻለ?

አቶ ሞቱማ፡– ፕሮግራሙ ሲነደፍም ችግር ነበር ያልኩት አካሄዱን በተመለከተ ነው። ለምሣሌ ባሕላዊ የወርቅ ማዕድናት አምራቾቹ የሚገኙት በጣም ሩቅ ቦታ ነው፡፡ የደቡብ ክልልን ብንወስድ ጠረፍ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ጨረታ ብታወጣ እነዚህ ጠረፎች ላይ ተጫራች ወይም ተቋራጭ (ኮንትራክተር) አታገኝም፡፡ ሄዶ መስራት የማይፈልግ አለ፡፡ ስለዚህ እንዴት ነው እዚያ ያለውን የመንግስት መዋቅር ተጠቅመን መስራት የምንችለው የሚለው በአግባቡ ሊታሰብበት ይገባ ነበር፡፡ ሌሎች አማራጮች መቀመጥ ነበረባቸው፡፡ ለዚያም ነው ሄዶ ሄዶ የቆመው፡፡ እንዴት ፈፀማችሁ? ለሚለው ግን፤ በተቻለ መጠን ጨረታዎች ወጥተው ከባንክ ጋር በመነጋገር ልናከናውን ችለናል፡፡

አዲስ ዘመን፡– የማዕድን ናሙና ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል ቤተሙከራው አገር ውስጥ ቢኖርም ‹‹አይ ኤስ ኦ-17025›› እውቅና ባለማግኘቱ አሁንም ናሙና የሚላከው ወደ ባሕር ማዶ ነው፤ እውቅናው ለምን ዘገየ?

አቶ ሞቱማ፡– ትክክል ነው፡፡ ሁሉም ባይሆን የተወሰኑት ማዕድናት የሚመረመሩት ወደ ውጪ ተልከው ነው፡፡ የእኛ ተጠሪ በሆነው የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ስር የጂዮ ኬሚካል ላቦራቶሪ አለ፡፡ ላቦራቶሪው ‹‹አይ ኤስ ኦ-17025›› አውቅና ማግኘት አለበት ተብሎ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች እውቅና ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በቅርቡም በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ስራው ተጓቷል፡፡ እውቅናውን ለማግኘት መሟላት የሚገባቸው ነገሮች አሉ፡፡ የሠው ኃይል እና የግብዓት ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ ስራውን ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ይዞ የሚሄድ ባለሙያ መኖር አለበት፡፡ አስፈላጊውን ስራ በጊዜ አጠናቆ ለምርመራ ወደ ውጪ የሚሄደውን እዚሁ እንዲመረመር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን፡– ከመቼ ጀምሮ ናሙና በአገር ውስጥ ይመረመራል?

አቶ ሞቱማ፡– በዚህ ዓመት ወይም በ2010 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ይሄን ጉዳይ መፈጸም አለብን ብለን እየሰራን ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡– ነዳጅ ፍለጋውን በተመለከተ ምን አዲስ ነገር አለ?

አቶ ሞቱማ፡– ስምንት የሚሆን ድርጅቶች ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ አንደኛው የቻይና ኩባንያ የሆነው ፖሊ ሲ ጄ ኤል የሚባል ኩባንያ ተፈጥሮ ጋዙን አግኝቷል፡፡ አሁን የተገኘውን ጋዝ ከኦጋዴን ተፋሰስ ወደ ውጪ ለመላክ እስከ ጅቡቲ ወደብ የ700 ኪሎ ሜትር የቧንቧ መስመር ዝርጋታ ድርድር ተጠናቋል፡፡ በቅርቡም ወደ ዝርጋታ ይገባል፡፡ የቧንቧ ዝርጋታው ለአንድ ኩባንያ ብቻ ሳይሆን ኦጋዴን ተፋሰስ ውስጥ ለሚገኙ ሁሉ የሚያገለግል ነው፡፡ ነዳጅን በተመለከተ ግን ፍለጋው እንደቀጠለ ቢሆንም አዲስ ነገር የለም፡፡ ሆኖም ይገኛል ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው፡፡

አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታና ለሰጡኝ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ !

አቶ ሞቱማ፡– እኔም አመሰግናለሁ !

ብሩክ በርሄ

– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/business-market/item/12070-2017-04-06-17-53-07#sthash.9PY7WxlU.dpuf