Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በቴክኖሎጂውም ዘርፍ ሉዓላዊ የሚያደርገን ፕሮጀክት

0 405

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በቴክኖሎጂውም ዘርፍ ሉዓላዊ የሚያደርገን ፕሮጀክት ዘአማን በላይ

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንጡራ ሃብት ነው። በዚህ ግድብ ላይ የሚነሱ ማናቸውም ጉዳዩች የሚመለከተው እነርሱን ነው። የሀገራችን ህዝቦች ይህን ግድብ የዛሬ ስድስት ዓመት ሲጀመሩ፤ “እንደ ጀመርነው እንጨርሰዋለን” ብለው ነበር። አሁን ደግሞ በርብርባቸው 56 በመቶ አድርሰውት፣ “እንደ አጋመስነው እንጨርሰዋለን” በማለት በድህነት ላይ የጀመሩትን ዘመቻ ለማሳካት ማናቸውንም በራስ አቅም የሚከወኑ ፕሮጀክቶች መስራት እንደሚችሉ እያረጋገጡ ነው።

ባለፉት ስድስት ዓመታትም ህዳሴያቸውን ቅርብ ለማድረግ ያከናወኑት ተግባር ግለቱን ጠብቆ ዛሬ ደርሷል። የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሶችና ህዝቦች የግድቡን ስድስተኛ ዓመት ክብረ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች “ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የአገራችን ህብረ ዜማ! የህዳሴያችን ማማ!” በሚል መሪ ቃል ሲያከብሩ ሰንብተዋል። ዛሬም ክብረ-በዓሉን ግድቡ በሚገኝበት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በጉባ ተገኝተው በዓሉን እያከበሩ ነው። በዚሁ ዕለት ግድቡን በራሳቸው ገንዘብ፣ ዕውቀትና ጉልበት እንደ ጀመሩት ከፍፃሜው ለማድረስ ቃል መግባታቸው የሚቀር አይመስለኝም።

ርግጥ የትናንቱን የአበውና እመው ታሪክን ባናነሳው እንኳን፤ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከዳር እስከ ዳር ያነቃነቁና በአንድ እስትንፋስ እንዲንቀሳቀሱ ያደረጉ ሁለት ጉዳዩች ይመስሉኛል። አንደኛው፤ ጦር ሰባቂው የኤርትራ መንግስት ሀገራችንን የዛሬ 19 ዓመት በወረረበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝቦች ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር በአንድ እስትንፋስ ቀፎው እንደተነካበት ንብ “ሆ!” ብለው ወረራውን መቀልበሳቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ፤ ዛሬ ስድስተኛ ዓመት ክብረ በዓሉ የሚከበርለትና በህዝቦች ባለቤትነትና ጠባቂነት እየተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው።

ይህ ግድብ ሁሉንም የሀገራችን ህዝቦች ላለፉት ስድስት ዓመታት ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው በማሳደግ የ“ይቻላል”ን መንፈስ በውስጣቸው መፍጠር የቻሉበት፣ ብሔራዊ አጀንዳቸው አድርገው ሃምሳ ሎሚ ለሃምሳ ሰዎች ሸክም አለመሆኑን ያሳዩበት፣ የራሳቸውን የውሃ ላይ ሃውልት በመገንባት አሻራቸውን ያሳረፉበትና ህዳሴያቸውን እውን ማድረግ እንደሚችሉ አንድ ማሳያ ያደረጉት ብሔራዊ ፕሮጀክት ነው። በአጭር አነጋገር ታላቁ የህዳሴ ግድብ ብሔራዊ መግባባትን የፈጠረ የሉዓላዊነታችን መገለጫ ፕሮጀክት ነው ማለት ይቻላል። ግድቡ እነዚህን ሀገራዊ ቁልፍ እሴቶች ከመገንባቱም በላይ፤ በቴክኖሎጂውም ዘርፍ ሉዓላዊ እንድንሆን እያደረገን ነው።      

በግዙፍ የኃይል ማመንጫነቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ፣ ከዓለም ደግሞ ሰባተኛ ደረጃን የያዘው ይህ የሉዓላዊነታችን መገለጫ ፕሮጀክት፤ ሳሊኒ ኢምፕሪጅሎ በተባለ የጣሊያን ኩባንያ የሲቪል ምህንድስና ስራው እየተከናወነለት ነው። ሀገር በቀሉ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ) ደግሞ፤ የኤሌክትሮ ሜካኒካልና የሃድሮሊክ ስቲል ስትራክቸሮችን የዲዛይን፣ የፕሮኩሪመንትና የግንባታ ብሎም ፈትሾ የማስረከብ ተግባራትን እየሰራ ይገኛል። ታዲያ እዚህ ላይ የተነሳሁበትን ግድቡ የሚያስገኝልንን የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ጥቅም ከመዘርዘሬ በፊት፤ ጥቅሙን እያስገኘልን ስላለው ሀገር በቀሉ “ብኢኮ” ጥቂት ማለት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። መነሻ ይሆነኝ ዘንድም “ለመሆኑ ‘ብኢኮ’ ማነው?” ብዬ እጠይቃለሁ።

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ብኢኮ) ወይም በእንግሊዝኛው አጠራሩ “METEC” (ሜቴክ) የተሰኘው ተቋም፤ የኢፌዴሪ መንግስት የኢንዱስትሪው ዘርፍ ቀልጣፋ ሚና እንዲጫወት ለማስቻል ካቋቋማቸው የልማት ድርጅቶች አንዱ ነው። ተቋሙ ሀገራችን ያላትን የቴክኖሎጂ አቅም በማቀናጀትና በማስተባባር ወደ ኢንዱስትራይዜሽን የሚደረገውን ሽግግር ለማቀላጠፍ ብሎም ኢንዱስትሪው የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመምራት የሚያስችለውን ሁኔታ ለማመቻቸት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 183/2002 በአስር ቢሊዮን ብር መነሻ ካፒታል እንዲቋቋም ተደርጓል።

ተቋሙ ሲቋቋም የሀገራችን ግብርና መር የልማት ስትራቴጂ ወደ ኢንዱስትሪ መር እንዲሸጋገር መደላድል የመፍጠር ዓላማን እንዲያነግብ ተደርጓል። ዓላማውን ማሳካት ይቻለው ዘንድም የተቀመጡለት ግቦች ኡት። ከእነዚህ ግቦች መካከል ሀገሪቱ ከውጭ የምታስመጣቸው ብረታ ብረት፣ ማሽነሪዎችና መለዋወጫዎች ሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በከፍተኛ እንዲቀረፍ ማድረግ አንዱ ነው። ይህን ግብ ለማሳካት ባደረገው ጥረትም፤ የማምረቻ ፋብሪካዎችን በሀገር ውስጥ በማምረትና አቅማቸውን በማሳደግ ከፍተኛና ፈጣን የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማረጋገጥ መጠነ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድል በማመቻቸት በጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ የስራ ዕድል መፍጠር የቻለ ተቋም ነው።

ከዚህ በተጨማሪ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍና ለማስተሳሰር እንዲሁም የአነስተኛ ጥቃቅን ተቋሞችን ከማኑፋክቸሪንግ የልማትና የአገልግሎት ዘርፍ ተቋማት ጋር በማስተሳሰር እንዲጠናከሩ የማድረግ ግብን የያዘ ነው። የአስራርና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን በመገንባትም ወደ ቀጣዩ የዕድገት እርከን የሚያሸጋግራቸውን ድጋፍና ትብብር ለማከናወን እንዲሁም ትላልቅ የመንግስት የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን መስራትና መገንባትን የመሳሰሉ ተደማሪ ግቦችን ይዞ ለውጥ በማምጣት ላይ የሚገኝ ሀገራዊ ተቋም ነው። እነዚህን ዓላማዎችና ግቦችን ይዞ በተቋቋመ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተንቀሳቀሰው ኮርፖሬሽኑ፤  በሀገራችን ፈር ቀዳጅ የልማት ሞተር በመሆን የህዳሴ ጉዟችንን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ሰፊ ጥረት ተልዕኮውን በሚገባ እየተወጣ ይገኛል።

ተቋሙ ከተወጣቸውና እየተወጣቸው ካሉት ተልዕኮዎቹ መካከል፤ የእርሻ መሳሪያዎችን፣ ትራክተሮችንና የተለያዩ ተሽከርካሪዎችን በማምረትና በመገጣጠም የአርሶ አደሩንና የከተማውን ነዋሪ ህይወት የመለወጥ፤ የማዳበሪያና የስኳር ፋብሪካዎችን የመገንባት፤ መንገድ የመስራት፤ ማዕድን የማውጣት ስራዎች ይጠቀሳሉ። እንዲሁም ‘ሀገራችን እንደ ወትሮው ቴክኖሎጂ የምትሸምት ወይም የምትዋስ ሀገር መሆኗ ማብቃት አለበት’ የሚል ፅኑ እምነት በመያዝ ተፈላጊ ቴክኖሎጂዎችን በአመርቂ ደረጃ በመቅሰም ኢትዮጵያ የራሷ ቴክኖሎጂ ያላት ሀገር (በቴክኖሎጂ ሉዓላዊ) እንድትሆን የመስራት እንዲሁም የኃይል ማመንጫ፣ ማሰራጫዎችና መሳሪያዎችን የመፈብረክ ተግባራቱ ተጠቃሽ ናቸው። ምንም እንኳን ኮርፖሬሽኑ የተሰጠው የስራ ድርሻ ሁሉንም የሃይል ማመንጫ አውታሮችን የሚመለከት ቢሆንም፤ በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የግንባታውን ሃምሳ በመቶ የስራ ተቋራጭ ኃላፊነት ወስዶ በመስራት ላይ ነው። በእስከ አሁኑ እንቅስቃሴውም ወገንን የሚያኮራና ሀገርን የሚጠቅም ተግባራትን ከውኗል።

“ዓባይን በጭልፋ” እንደሚባለው ስለ ኮርፖሬሽኑ አመሰራረት፣ ዓላማና ግብ እንዲሁም አለፍ…አለፍ ብዬ ስለ ውስን ተግባራቱን በጥቂቱ ይህን ያህል ካልኩ ዘንዳ፤ አሁን ደግሞ የህዳሴው ግድብ በቴክኖሎጂም ሉዓላዊ እያደረገን ነው ስላልኩት ዕውነታ ላውሳ። ርግጥ የህዳሴው ግድብ በቴክኖሎጂ ሉዓላዊ የሚያደርገን ይህን ስራ በተልዕኮ የተቀበለ አንድ አካል ሲኖር፣ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት የሚችል አመራርና ሰራተኛ ሲኖር መሆኑ አይካድም። በመሆኑም የህዳሴው ግድብ በቴክኖሎጂ ሉዓላዊ እያደረገን ነው ሲባል፤ ዋነኛው ተዋናይ በኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰው “ብኢኮ” መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም።

ታዲያ ተቋሙ ይህን የቴክኖሎጂ ቅመራ ሲያከናውን ሀገር በቀልና የራሱን የሆነ አቅም በመገንባት የቴክኖሎጂ ሽግገር አካሂዶ መሆኑ አይታበይም። ማንኛውም ሀገር የሚያከናውነውን ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ለመፈፀም ሁሌም ፊቱን ወደ ሌሎች ሀገር የሚያዞር ከሆነ የእኔ ነው የሚለው ሉዓላዊ መገለጫ አይኖረውም። ይህን አባባሌን ሰሞኑን ቢሮአቸው ተገኝተን ያነጋገርናቸው የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ደመቀ መኮንንም ይጋሩታል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሉዓላዊ ሀገር ማለት አንዱ በሀገር ቤት በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ‘ወርልድ ክላስ’ የሆነ ስራ ሊሰራ የሚችል ሀገራዊ አቅም መገንባት ነው። የስኬታማ ሀገራት ጉዞም የሚያሳየው ይህንኑ ነው። የህዳሴ ግድብ ላይ ሜቴክ (ብኢኮ) ገባ ማለት፤ ስኳር ፋብሪካ ላይ ሜቴክ ገባ ማለት፣ በዚህ ሥራ ውስጥ ዋናው ስራ ሳይበደል ግን ደግሞ ሜቴክ አቅም ገንብቶ እንዲወጣ የሚያደርግ አቅጣጫ መከተል ነው። ይህ ውሳኔ የዘላቂ ልማታችን እና የሉዓላዊነታችን አንዱ መገለጫ ነው። ይህ ካልሆነ ሀገር በጠንካራ መሰረት ላይ ሊገነባ አይችልም።…” በማለት ጉዳዩን ሰፋ አድርገው ገልፀውታል።

ርግጥ አቶ ደመቀ እንዳሉት የትኛውም ሀገር ‘የእኔ ነው’ የሚለው የቴክኖሎጂ ቀመር ከሌለውና ነባሩን ቴክኖሎጂ ወደ ራሱ በማምጣት ከተጨባጭ ሁኔታው ጋር ማጣጣም ካልቻለ፤ ሙሉ ለሙሉ የውጭ ቴክኖሎጂ ጥገኛ መሆኑ አይቀርም። ይህ ደግሞ ሀገር በቀል ተቋማት እንዲቀጭጩ አሊያም ራሳቸውን ችለው አንድም ጋት ፈቅ ሳይሉ ባሉበት እንዲረግጡ ማድረጉ አይቀርም። እናም ሀገራዊ አቅም መገንባት የሚችሉና በዓለም ደረጃ ተጠቃሽ ሊሆን የሚችል ፕሮጀክት ላይ የሚሳተፉ እንደ “ብኢኮ” ዓይነት ተቋማት ሊኖሩ የግድ ይላል። “ብኢኮ”ም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ላይ ተሳትፎ ለውጥ ማምጣት የቻለውም መንግስት ይህን ሀገራዊ አቅምን የማሳደግ እንዲሁም ኮርፖሬሽኑ ምናልባትም ወደፊት ማናቸውንም ፕሮጀክቶች በራሱ አቅምና ችሎታ እንዲገነባ የሚያስችለውን ትክክለኛ መንገድ በመከተሉ ነው—“የሀገሩን ሰርዶ፣ በሀገሩ በሬ” እንዲል የሀገራችን ሰው። ሌላ ምንም ዓይነት ምስጢር የለውም። ሊኖረውም አይችልም። ምናልባት ምስጢር ሊሆን ከቻለ፤ ይህን በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ የተለያዩ አካላት ዕይታ ስር ያለውን ፕሮጀክት በራስ አቅም አሳድጎ ለሀገርና ለህዝብ ጠቃሚ ነገር ሰርቶ ማለፉ ብቻ ይመስለኛል።

ሆኖም “በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣል” እንዲሉ፤ ይህን የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትንና ሀገራዊ ጥቅምን ያልተገነዘቡ፣ በጥላቻ ፈረስ ላይ ቁጭ ብለው ሽምጥ የሚጋልቡ አንዳንድ የኢትዮጵያን ዕድገት ማየት የማይሹ እንዲሁም በዳረጎት ቃራሚነት ለባዕዳን ተላላኪ የሆኑ ፅንፈኛ ኃይሎች የ“ብኢኮ”ን ሚና አሳንሰው አሊያም “አዛኝ መሳይ ቅቤ አምጓች” ሆነው ‘ተቋሙ ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት የመገንባት ልምድ የለውም’ ሲሉ ይደመጣሉ። በዚህ እኩይ ሴራቸውም ከተለያዩ ፀረ-ኢትዮጵያ አካላት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው የኮርፖሬሽኑን ስም ለማጠልሸት ያልወረወሩት የአሉባልታ ድንጋይ የለም። ግና የአሉባልታ ድንጋዩ ጭው ባለ በረሃ ላይ እንደተወረወረ ያህል የሚቆጠር እንጂ፤ ሀገራዊ አቅም በመቀመር የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን በመፍጠር ስራ ላይ ካለው ተቋምም ይሁን ህዳሴው ማማ ላይ ለመውጣት ነገን አሻግሮ ከሚተልመው የሀገራችንን ህዝብ ጋር የሚያገናኘው አንዳችም ጉዳይ የለም። “ለምን?” ከተባለ፤ በጥላቻ መርዝ ታሽቶ የተወረወረው የእነ ‘አያ እንቶኔ’ አሉባልታዊ ዲስኩር ምክንያታዊ ያልሆነና ኮርፖሬሽኑ በተጨባጭ እያከናወነ ያለውን እመርታ የማያውቅ ግልብ ስሜት ብቻ የሆነና የሀገራችን ህዝቦች በህዳሴው ግድብ ላይ ያላቸውን ቁርጠኛ አቋም የማያውቅ ‘የሞኝ ዘፈን’ ስለሆነ ነው።

ለዚህም ነው—ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን “ብኢኮ” በግድቡ ላይ ያከናወናቸውን ለውጦች አስመልክተው፤ “…ከዋናው ተቋራጭ ከሳሊኒ ኮንስትራክሽን ጋር ተያይዞ የሚሠራ ሥራ አለ። በዛ ውስጥ ንዑስ ተቋራጭ አድርጎ ሜቴክ እንዲሳተፍ ማድረግና አቅም እንዲገነባ መደረጉ በተጨባጭም አሁን ስንገመግመው ሜቴክ በጣም ውጤታማ እና አርኪ ስራዎችን እየሠራ ነው። የመጣበት ሁኔታን ስናየው እንዲሁ መለማመጃ አይደለም፤ እንዲሁ ለስምም አይደለም፤ ተጨባጭ የሆኑ በዓለም ላይ ታዋቂ የሆነውን የሳሊኒን ኩባንያ በአንዳንድ ሥራዎች የበለጠ ከሜቴክም ትምህርቶች እየወሰደ ስራውን የበለጠ እንዲያበለጽግ ያደረገበት ዕድልም እየፈጠረ ነው።…” በማለት ተቋሙ ላለፉት ስድስት ዓመታት ያለፈበትን የስኬት መንገድ ፍንትው አድርገው ይገልፁታል።

ታዲያ እዚህ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ብኢኮ” (ሜቴክ) የመጣበት መንገድ ውጤታማና አርኪ እንዲሁም ስራውን የበለጠ እንዲያበለፅግ አድርጎታል ያሉበትን አግባብ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል። እግረ መንገዱንም ‘ኢትዮጵያ ለምን ታድጋለች’ በሚል የጥላቻ ፈረስ ላይ ተቀምጠው ሽምጥ ለሚጋልቡ ኃይሎች ምላሽ ይሆናል ብዬ አስባለሁ—የሚሰማ ጆሮ ካለቸው ማለቴ ነው። ርግጥም አቶ ደመቀ እንዳሉት በቴክኖሎጂ ሉዓላዊ እንድንሆን በማድረግ ላይ የሚገኘው ኮርፖሬሽኑ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ሲያከናውናቸው የመጣው ለውጦች በርካታ ናቸው።

አዎ! ግድቡ በታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ መሰረት ሲጣል የተወጠነው የኃይል ማመንጨት መጠን 5 ሺህ 250 እንደነበር ከዚህ ፅሑፍ አንባቢ የሚሰወር አይደለም። ሆኖም “ብኢኮ” በሃድሮ ሜካኒካልና በሃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር ያከናወነው የዲዛይን ማስተካከያና ማሻሻያ ስራ፤ ታቅዶ የነበረውን የግድቡ የኃይል ማመንጨት አቅምን በ750 ሜጋ ዋት በማሳደግ ወደ ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት ከፍ እንዲል አድርጓል። ይህ ታላቅ ስራ የተከናወነው የህዳሴ ግድቡ ግንባታ መሰረት ከተጣለ ከአንድ ዓመት በኋላ መሆኑ ደግሞ ኮርፖሬሽኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን ከስራው ጋር ማዋሃዱን ያሳያል። በተለይም በዚህ የዲዛይን ማሻሻያ ስራ ለህዳሴ ግድቡ ከተያዘው በጀት አራት ቢሊዮን ብር የሚያህል ወጪን ማዳን መቻሉ “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” የመምታት ያህል ይቆጠራል—የማመንጨት አቅም መጨመርና ወጭን ማዳን።

ምን ይህ ብቻ። ኮርፖሬሽኑ ራሱ ያሳደገውን የግድቡን የማመንጨት አቅም ከስድስት ሺህ ወደ 6 ሺህ 450 ሜጋ ዋት ከፍ አድርጎታል። ወደፊትም ግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅም ይበልጥ ሊያድግ እንደሚችል መረጃዎች ይጠቁማሉ። የእነዚህ ድምር ውጤቶችም በዚህ ዘርፍ ብቻ ሀገራችን በቴክኖሎጂም ሉዓላዊነቷን እንድታረጋግጥ “ብኢኮ” ምን ያህል የላቀ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል። እናም ይህ በብቃት የታጀበ እንዲሁም ሊታይና ሊዳሰስ የሚችል ተጨባጭ ለውጦችን ማምጣት የቻለው የኮርፖሬሽኑ አመርቂ ተግባር በምንም ዓይነት ተቃውሟዊ ስሌት ‘….ግዙፉን ፕሮጀክት የመገንባት አቅም የለውም’ የሚያስብለው አይደለም። እንዲያው የነገር ክርን እየተረተሩ ከወዲያ ወዲህ በመወርወር በጭፍን ጥላቻ የሃሳብ ማዕበል ለመዋተት ካልሆነ በስተቀር።  

ለነገሩ እንደ “ብኢኮ” ዓይነት ቴክኖሎጂን በመቀመር ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የመገንባት አቅም እያጎለበተ የመጣ ተቋም፤ ሀገርን ወክሎ በግንባታ ስራው ላይ የሚሳተፍ እንደ መሆኑ መጠን ስራውን የመከታተል ኃላፊነትም አለበት። ይህን ኃላፊነት አስመልክተው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የማንደራደርባቸው፣ የትውልድና ብዙ ዓይን የሚያርፍበት ፕሮጀክት ከታች ከመሰረቱ የማይታዩት ሥራዎች፣ በግልፅ የሚታዩትም ስራዎች ደረጃቸውን የጠበቁ አስተማማኝ መሆን አለባቸው። ‘ሜቴክ’ በዚህ ደረጃ ሥራዎቹን እንዲያረጋግጥ፣ እንዲሠራ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አሉ ማለት ነው።…እግረ መንገዱንም ነገ ሜቴክ ራሱን ችሎ፣ ሌሎች ኩባንያዎች ራሳቸውን ችለው ብዙ ሳሊኒዎች ሆነው እንዲወጡ ሊያደርግ የሚችል ሁኔታ ነው።…” ሲሉ ያስረዳሉ። የአንድ ሀገር ዕድገት ሊረጋገጥ የሚችለው በዚሁ መንገድ መሆኑንና ይህ ካልሆነ ግን ያ ሀገር የውጭ ኩባንያዎችን ብቻ አንጋጥጦ የሚመለከት እንደሚሆን ጭምር በማስረዳት።

ይህ ዕውነታ “ብኢኮ” የሀገሩ ቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ቀማሪ ብቻ ሳይሆን፤ ግድቡ በራሱ ሀገር ህዝብ ሃብት የሚገነባ ስለሆነ፣ ጥራት ባለው ሁኔታ ሰርቶ የማሰራት ተደራቢ ኃላፊነትም ያለበት መሆኑንም የሚያመላክት ይመስለኛል። ላለፉት ስድስት ዓመታትም ከሳሊኒ ኮንስትራክሽን የቀመረውን የቴክኖሎጂ ሽግግር በመጠቀምና የራሱንም በመጠቀም ቀደም ሲል የተጠቀሱትን የግድቡን እመርታዎች ሊያስመዘግብ የመቻሉም ምስጢር ይኸው ይመስለኛል።

ማን ያውቃል?!—ነገ ደግሞ የዛሬው “ብኢኮ” ነገ አያሌ “ብኢኮ”ዎች አፍርቶ በዓለም ደረጃ የታወቁ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ሌሎች የሀገራችንን የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት የሚያሳዩ ተግባራትን መከወናቸው አይቀርም። ለአሁኑ ግን በሀገራችን ህዝብ ቀጥተኛ ባለቤትነትና ጠባቂነት እንዲሁም በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ቴክኖሎጂ ቀማሪነት በመገንባት ላይ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በቴክኖሎጂው ዘርፍም ሉዓላዊ ሀገር እያደረገን ነው። ላለፉት ስድስት ዓመታት ህዝቦች በባለቤትነት መንፈስ በግድቡ ግንባታ ላይ ሌት ተቀን መረባረባቸው እንዲሁም ሀገር በቀሉ “ብኢኮ” የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነታችንን ለማረጋገጥ ያደረጉት ጣምራ ጥረት ሲታይ፤ ነገና ከነገ በስቲያ የሌላ የቴክኖሎጂ እመርታ ታሪክ ባለቤት መሆናችን የሚቀር አይመስለኝም—የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃልና። ታዲያ እኔም በዚህ ሊፈፀም በሚችል ምኞቴ ፅሑፌን ስቋጭ፤ እንደ ግድቡን ገንቢ ዜጋ መላው የሀገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንኳን ለህዳሴው ግድብ ስድስተኛ ዓመት የግንባታ ክብረ በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት ነው።       

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy