Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በቻይና መንግሥት ዓለም አቀፍ ግዙፍ ዕቅድ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ዋነኛ ተዋናይ ሆና ተመረጠች

0 1,299

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የቻይና መንግሥት ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት በመደበለት አኅጉርን ከአኅጉር የሚያገናኙ የዓለምን የተለመደ የንግድ ግንኙነት የመቀየር አቅም አለው ተብሎ በሚጠበቀው ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶች ጉባዔ ላይ፣ የምሥራቅ አፍሪካዎቹ ኢትዮጵያና ኬንያ ተጋበዙ፡፡ ኢትዮጵያ የቻይና ግዙፍ ዕቅድ ዋነኛ ተዋናይ እንድትሆን ይፈለጋል፡፡

‹‹አንድ መንገድ››፣ ‹‹አንድ ቤልት›› በሚል ስያሜ የቻይና መንግሥት ፕሬዚዳንት ዢ ፒንግ አነሳሽነት እ.ኤ.አ. በ2013 ይፋ የተደረገው ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክትን፣ የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ ከግንቦት 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የሁለት ቀን ዓለም አቀፍ ጉባዔ ተጠርቷል፡፡

በዚህ ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ያካተተ የልዑካን ቡድን ይዘው የሚጓዙ ሲሆን፣ ከጉባዔው በኋላ በተመረጡ የቻይና ግዛቶች ውስጥ ከባለሥልጣናትና ከኢንቨስተሮች ጋር ውይይትና ጉብኝት ይደረጋል ሲሉ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የቻይና መንግሥት በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች (ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳንና ጂቡቲ) በመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ይሳተፋል፡፡ ከዚህም በጥልቀት በመሄድ እነዚህ አገሮች ከየብስ በተጨማሪ ከቻይና ግዛቶችና በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከተካተቱ አገሮች ጋር የሚገናኙበት የማሮን ወሽመጦችንና ወደቦች የማልማትና የመሠረተ ልማት አውታሮችን የማመቻቸት ዕቅድ ይዟል ተብሏል፡፡

ይኼ የቻይና ግዙፍ ዕቅድ በ65 አገሮች በአጠቃላይ 4.4 ቢሊዮን ሕዝቦች ያቀፈ ሲሆን፣ የምሥራቅ አፍሪካው ፕሮጀክት ከጂቡቲ ተነስቶ ኢትዮጵያ በመዝለቅ እስከ ኦጋዴንና ድሬዳዋ ድረስ፣ ከዚያም ደቡብ ሱዳንና ኡጋንዳ፣ እንዲሁም ኬንያ ናይሮቢን አቋርጦ እስከ ሞምባሳ ወደብ ይዘረጋል፡፡ ከታንዛኒያ እስከ አንጎላም ይለጠጣል፡፡

ኢትዮጵያ የዚህ ግዙፍ ዕቅድ አካል ሆና የተመረጠች በመሆኗ፣ የዕቅዱ ተጠቃሚ ለመሆን ቀደም ብላ ዝግጅት እያደረገች መሆኑ ተገልጿል፡፡

በተለይ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር እየሠራች የምታገኝባቸውን በርካታ ፕሮጀክቶች የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ አራት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጓን፣ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የመጀመሪያቸው የመሠረተ ልማትና የፋይናንስ አቅርቦት ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የባቡር መስመር ግንባታ፣ የኢነርጂ አውታሮች ግንባታ፣ የመንገድና የግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታዎች ይገኙበታል፡፡

ሁለተኛው ንግድ ነው፡፡ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በማምረቻ ዘርፍ  በርካታ ዓይን ገላጭ ፕሮጀክቶች በማካሄድ ላይ የምትገኝ እንደ መሆኗ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በሚመላከት ቻይናን ዋነኛ መዳረሻ የማድረግ ዕቅድ ተይዟል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የተፈጥሮና የታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት በመሆኗ፣ ይኼንንም በማልማት ላይ የምትገኝ ስለሆነች የቻይና ቱሪስቶች ኢትዮጵያን በሰፊው እንዲጎበኙ ለማድረግ ታቅዷል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቻይና አራት ግዛቶች የበረራ መስመሮች አሉት፡፡ አየር መንገዱ ወደ ቻንግዱ ግዛት በቅርቡ በረራ ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

በአራተኛ ደረጃ የተቀመጠው ኢንቨስትመንት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ላይ ይገኛሉ፡፡ በእነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የቻይና ኢንቨስተሮች በስፋት ተሳታፊ እንዲሆኑ ይፈለጋል፡፡  reporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy