NEWS

በቻይና የልማት ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ሆናለች – አምባሳደር ላ ይፋን

By Admin

April 26, 2017

ኢትዮጵያ በቻይና መንግሥት ለአፍሪካ በሚቀርበው የልማት ኢንሼቲቭ በአግባቡ እየተሳተፈችና እየተጠቀመች መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ላ ይፋን ገለጹ።

የቻይና ኤምባሲ በፕሬዚዳንት ዥ ጂንፒንግ የተዋወቀውን “ዋን ቤልት ዋን ሮድ” የተሰኘውን የልማት ኢኒሼቲቭ በተመለከተ በኢትዮጵያ ከሚገኙ የዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ ጋር ተወያይቷል።

ኢኒሼቲቩ በመሰረታዊነት ቻይና ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ያላትን የልማት ትስስር አንድም በየብስ አልያም በባህር ትራንስፖርት በማጠናከር ውህደትን ለመፍጠር ያለመ ነው።

ይህን ለማድረግም ኢኒሼቲቩ በተለይም አፍሪካን በተመለከተ በዋና ዋና የልማት መርሃ-ግብሮች ላይ በሚወጡ የፓሊሲና የስትራቴጂ ጉዳዮች ላይ ትብብር ማድረግን ያስቀድማል።

ተግባራዊ በሚደረጉ የመሰረተ ልማት አውታሮችና በኢንቨስትመንት ሥራዎች ላይም ተቀራርቦ በመሥራት በተለያዩ አካባቢዎች መካከል ግንኙነትን ለመፍጠር ይሰራል ተብሏል።

በንግዱ ዘርፍም በተለያዩ ህዝቦችና አገራት መካከል ግንኙነት ለመፍጠር ምርቶች ወደሌሎች አካባቢ ገበያ እንዲያገኙ ኢኒሼቲቩ ትኩረት አድርጎ የሚሰራባቸው መስኮች ናቸው።

በሌላ በኩል በአገራት መካከል ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር የተለያዩ የልዑክ ቡድኖችን በመላክና በመቀያየር እንዲሁ ትስስሩን ለማሳለጥ ይተጋል።

ኢኒሼቲቩ በተለይም በፖሊሲ ትብብር መስክ ላይ ኢትዮጵያና ቻይና የተለያዩ የፖሊሲ ባለሙያዎችን በመቀያየር በጋራ እንዲሰሩ አስችሏል ይላሉ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ላ ይፋን።

በኢንዱስትሪ ልማትና በንግድ ጉዳዮች ላይ በአገራቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መካከል ጠቃሚ ውይይት መደረጋቸውን በመጠቆም።

በመሰረተ ልማትም፤ የባቡር መስመር ዝርጋታና በጊቤ ሶስት የኃይል ማመንጫ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተው በሌሎች መርሃ-ግብሮችም ፍሬያማ ትብብሩ መኖሩን አስረድተዋል።

በንግድ ግንኙነትም ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ሴራሚክና ሻይ ቅጠሎችን ከቻይና ማምጣት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ አሁንም ድረስ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ ንግዱ እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በሚባል መልኩ በኢኒሼቲሹ ባለፉት ሦስት ዓመታት ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዳላትና ተጠቃሚነቷንም የዛኑ ያህል ያረጋገጠች መሆኑን ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።

በቀጣይም ኢኒሼቲቩ ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ በበኩላቸው ኢኒሼቲቩ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ፤ ብሎም ለዓለም ውህደት ወሳኝ ነው።

ከፖሊሲ ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ በጋራ ለመሥራት የሚያስችልና አገራት ያላቸውን የመሰረተ ልማት አውታሮች ለማዘመን የሚያግዝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ይህንን ለማድረግ ቻይና የኢንቨስትመንት ሥራዋንና ባለኃብቶቿን ወደ አፍሪካ በመላክ የአህጉሪቱ አገራት ያላቸውን ኃብት አሟጠው እንዲጠቀሙ እድል መክፈቷን አስረድተዋል።

በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት ቻይና ለአፍሪካ የሚጨበጥ ድጋፍ እንዳደረገችና በዚህም ቻይና ለአፍሪካውያን የዋለችው ትልቅ ውለታ መሆኑን ነው ያሰመሩበት።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ካፒታልን በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ በማዋል ልማቷን እያካሄደች ባለችበት ወቅት ኢኒሼቲቭ ተግባራዊ መደረጉ ተጠቃሚ ያደርጋታል ብለዋል።

በተለይም የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ የልማት ውጥኖቹ እውን እንዲሆኑ እያሳየች ያለውን አጋርነትና ወዳጅነት መንግሥት በአድናቆት እንደሚመለከተው ገልጸዋል።

በቀጣይም ይህንን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደላቀ ደረጃ ለማድረስና የቻይና ኢኒሼቲቭን እውን ለማድረግ ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በመጪው ግንቦት በቻይና ቤጂንግ በኢኒሼቲቭ ላይ በሚመክረው ዓለም አቀፍ መድረክ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ በርካታ የዓለም አገራት መሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።