Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በአዲስ አበባ ጽዱና ንጹህ አካባቢን መቼ እናይ ይሆን?

0 1,288

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የገላ መታጠቢያ ወይም ሻወር ቤት ያለው መፀዳጃ ቤት እና በቅርቡ የጀመረው የህዝብ ንፅህና መጠበቂያና የመንገድ ማረፊያ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚው ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየሰራ ይገኛል፡፡ ጽዳትና አስተዳደር ኤጀንሲም በበኩሉ 76በመቶ ከመኖሪያ ቤት፣ ቀሪውን 24 በመቶ ደግሞ ከተቋማትና ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ በመሰብሰብ ያስወግዳል፡፡ ይሁን እንጂ አካባቢን ጽዱና ውብ በማድረግ ምቹ መኖሪያ ለመፍጠር ጥረቶች ቢደረግም ዛሬም አዲስ አበባ ከተማን ከቆሻሻ የፀዳች ማድረግ አልተቻለም፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው እንዲሁም በተለያየ አነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች በአቅራቢያቸው የመፀዳጃ ቤት ባለመኖሩ በአካባቢያቸው በሚገኝ ሜዳ ላይ ለመጠቀም ተገደዋል፡፡ የአብዛኞቹ የሥራ ቦታ በመኖሪያ መንደርና መተላለፊያ ሥፍራ በመሆኑ የአካባቢ ንጽህናን በማጉደልና ለጤና ችግርም ስጋት እየሆነ ይገኛል፡፡

ችግሩ ከሚስተዋልባቸው አንዱ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ጀሞ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በማህበር ተደራጅተው በመኪና እጥበት ሥራ የተሰማሩትን፣ሱቅ በደረቴ እና በአነስተኛ ንግድ ላይ የተሰማሩት ለአብነት ይጠቅሳል፡፡ «ገብረእግዚአብሄር እና መሃሪ ጓደኞቹ» በሚል ስያሜ 8 አባላትን ይዞ በመኪና እጥበት ላይ የተሰማራው ማህበር ከግንቦት ወር 2008.ም ጀምሮ በሥራው ላይ ሲቆይ አባላቱ የሚጠቀሙበት የመፀዳጃ ቤት በአካባቢው የላቸውም፡፡

የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ መሃሪ ገብረሥላሴ፣ አባላቱ አቶ ገብረእግዚአብሄር ኪዳነማርያም እና አቶ ኪዳኔ ሐፍተይ እንዳስረዱት፣ ከማህበሩ አባላት ሁለቱ ሴቶች መሆናቸውንና መፀዳጃ ቤት ባለመኖሩ በበለጠ እየተጎዱ ነው፡፡ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት እስከ ምሽት 1230ድረስ በሥራ ላይ ሲቆዩ ይቸገራሉ፡፡ ተገልጋዮችም አገልግሎቱን አግኝተው እስከሚሄዱ መፀዳጃ አለማግኘ ታቸውም ሌላው ችግር ነው፡፡ ማህበሩ ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ቢያሳውቅም መፍትሄ አልተሰጠውም፡፡ በራሱም መፀዳጃ ቤት ለመስራት ጥያቄ ቢያቀርብም ፈቃድ አላገኘም፡፡

በአካባቢው ሊስትሮና ሱቅ በደረቴ የሚሠራው ወጣት ማቲዎስ ዲላሞም ችግሩን በተመሳሳይ ገልጿል፡፡አንዳንድ ጊዜ ለመፀዳዳት ወደቤቱ የሚሄድበት አጋጣሚ መኖሩንም ተናግሯል፡፡ ሌሎችም በአነስተኛ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ አስተያየት ሰጪዎች መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ሰለሞን አበበ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እርሳቸው እንዳስረዱት ግንባታው የሚከናወነው ከፍተኛ የህዝብ እንቅስቃሴ ባለባቸው በቀን ቁጥሩ እስከ ሁለት መቶ ሰዎች በሚስተናገዱበት ሥፍራዎች ሲሆን፤ በዚሁ መሠረትም በጀሞ አካባቢ ከፍተኛ የህዝብ እንቅስቃሴ ባለባቸው 8አካባቢዎች ተገንብቷል፡፡ ባለስልጣኑ ግንባታ ለማከናወን የዕቅድም ሆነ የበጀት ችግር እንደሌለበትም አስታውቀዋል፡፡ እንደ አስተባባሪው ገለጻ ባለስልጣኑ ተግዳሮት የሆነበት ለግንባታ የሚሆን ቦታ በቀላሉ አያገኝም፡፡ ቦታውን ለማመቻቸት የክፍለ ከተሞች ትብብር አነስተኛ ነው፡፡የመፀዳጃ ቤት አስፈላጊነት በአመራሮች በኩል ትኩረት አላገኘም፡፡ የግንባታ ሥራው ከተጀመረ በኋላም በአካባቢ ነዋሪዎች እንዲቆም የሚደረግበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ያጋጥማል፡፡

ባለስልጣኑ ከ2007 እስከ 2008.170 የህዝብ መፀዳጃ ቤቶችን መገንባቱንና በበጀት ዓመቱም 320የህዝብ ንፅህና መጠበቂያና የመንገድ ማረፊያ ለመገንባት ታቅዶ 44ቱ በግንባታ ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድና ያለውን ችግር በተመለከተም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በዋና የሥራ ሂደት የጥናት ግንዛቤ ኮንትራት አስተዳደር ባለሙያ አቶ ምትኩ ሄርጳ እንዳስረዱት፣ በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ በተለያየ መንገድ የሚመነጨውን ቆሻሻ ነዋሪዎች ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በአካባቢው የሚሠሩ ተቋማት እስከ 50ሜትር ድረስ የማጽዳት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሁሉም ኃላፊነ ታቸውን ካልተወጡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ደረቅ ቆሻሻ በማንሳት ላይ የተሰማሩ ማህበራት ክትትል ማድረጊያ የዞናል አሠራር አላቸው፡፡

እንደ አቶ ምትኩ ማብራሪያ 76 ከመቶ የሚሆነው ቆሻሻ የሚመነጨው ከመኖሪያ ቤት ሲሆን፤ ቀሪው ደግሞ ከተቋማትና ከመንገድ ላይ ነው፡፡ ከመኖሪያ ቤት የሚመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ በጥቃቅንና አነስተኛ በማህበር በተደራጁ 610ማህበራት አማካኝነት ተሰብስቦ በጊዜያዊ ማስቀመጫዎች እንዲከማች ይደረጋል፡፡በጎዳና ላይ የሚጣሉ ቆሻሻዎች ደግሞ በመንገድ ጽዳት ሠራተኞች ይፀዳል፡፡ከተለያዩ ተቋማት የሚመ ነጩት ደረቅ ቆሻሻዎች ደግሞ በግል ተደራ ጅተው በሚሰሩ የጽዳት ድርጅቶች ይከናወናል፡፡ ኤጀንሲው ደግሞ በማህበራትና በመንገድ ጽዳት ሠራተኞች በጊዜያዊ ቦታ የተከማቸውን ደረቅ ቆሻሻ ወደማስወገጃ ቦታ ያጓጉዛል፡፡

አቶ ምትኩ «ሥራዎች ይሰራሉ ግን ህብረተሰቡም የሚጠበቅበትን ኃላፈነት ባለመወጣቱ የኤጀንሲውን ጥረት እጀ ሰባራ አድርጎታል» ይላሉ፡፡ አፈጻጸም ላይ ክፍተት መኖሩንም አልሸሸጉም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ከሥራ ዕድል ፈጠራው ጎን ለጎን እንደመፀዳጃና ሌሎችንም ማህበራዊ አገልግሎቶች አብሮ በማመቻቸት ስላደረገው እንቅስቃሴ በቢሮው የንግድና አገልግሎት ሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ነብዩ ውድነህን ጠይቀናቸው ነገሩን በጥልቀት እንዳላዩትና በክፍተት እንዳዩት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

አሁን መረዳት እንደቻልነው ሁሉም የየራሱን ሥራ ከመወጣት ባለፈ አንዱ የሌላውን ሥራ በመደገፍም ሆነ ሃሳብ በመለዋወጥ መንቀሳቀስ ላይ ክፍተት መኖሩን ነው፡፡ ህብረተሰቡንም ያሳተፈ ሥራ አለመስራታችን የጽዳት ጉድለት ጉዳይ በተደጋጋሚ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል፡፡ እኛም የጽዳት ጉዳይ ዘላቂነት መፍትሄ አግኝቶ ንጹህና ጽዱ አዲስ አበባን እስከምናይ ችግሩን በተደጋጋሚ ማንሣታችን ይቀጥላል፡፡

ለምለም መንግሥቱ

– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/news/national-news/item/12390-2017-04-28-16-47-30#sthash.F0oaueaS.njoYyXLE.dpuf

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy