NEWS

በኢትዮጵያ ሽብር ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የተያዙ የአልሸባብ ምልምሎች በእስራት ተቀጡ

By Admin

April 28, 2017

በሽብር ቡድኑ አልሸባብ ተመልምለው በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ሊፈጽሙ ሲንቀሳቀሱ የተያዙ ሁለት ግለሰቦች በጽኑ እስራት ተቀጡ።

ተከሳሾቹ 1ኛ በድሪስ የሱፍ እና 2ኛ አኒስ ኡስማን ናቸው።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በግለሰቦቹ ላይ የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የተያዙ ናቸው በሚል ነው ክስ መስርቶባቸው የነበረው።

ግለሰቦቹ ራሱን አልሸባብ እያለ በሚጠራው አሸባሪ ቡድን ውስጥ በአባልነት ተመልምለው ስልጠና የወሰዱ መሆናቸውን ክሱ ያስረዳል።

ከዚህም ባለፈ በኢትዮጵያ አባላትን የመመልመልና ሴል የመመስረት እንቅስቃሴ አድርገዋል ይላል ክሱ።

ይህን ተከትሎ በተለያዩ የመንግስት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ላይ የሽብር ጥቃት ለመፈፀም የሚያስፈልጋቸውን ቦታዎች የማጥናት ስራ ሲሰሩ እንደነበር በክሱ ተጠቅሷል።

ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት የአልሸባብ የፈንጂ ባለሙያዎች የሽብር ጥቃት እንዲያደርሱና ፈንጂ ለመስራት እንዲችሉ መኖሪያ ቤት በመከራየት የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲዘጋጁ ነበር።

በተለይ 1ኛ ተከሳሽ መጋቢት 19 1999 ዓ.ም በአልሸባብ ተመልምሎስልጠና ከወሰደ በኋላ በ2000 ዓ.ም በሞቃዲሾ ከሌሎች የአልሸባብ አባላት ጋር በመሆን በሶማሊያ ካለው የአፍሪካ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አሚሶም) ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጉም በክሱ ተብራርቷል።

ሁለቱ ተከሳሾች በኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ላይ የአባላት ምልመላ ሲያደርጉ በርካታ ገንዘብ በተለያዩ ጊዜያት ለስራ ማስኬጃ በሚል ሲላክላቸው መቆየቱ በማስረጃ ተረጋግጧል።

በዚህ እንቅስቃሴ እስከ 2006 ዓ.ም ራሳቸውን በማደራጀት ላይ እያሉ ነው በቁጥጥር ስር የዋሉት።

አቃቤ ህግም ግለሰቦቹ የሽብር ድርጊቱን ለመፈፀም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማነሳሳት እና ሙከራ ወንጀል ነው ክስ የመሰረተባቸው።

ክሱን የተመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የግራ ቀኙን መርምሮ በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል።

በዚህም 1ኛ ተከሳሽን በስድስት አመት ከስድስት ወር ፅኑ እስራት፤ ሁለተኛ ተከሳሽን ደግሞ በ5 አመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህ የክስ መዝገብ ላይ ከ3ኛ እስከ 5ኛ ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ ግለሰቦች የአቃቤ ህግን ማስረጃ ማስተባበል በመቻላቸው በነፃ ተለቀዋል።