በኢትዮጵያ 10 በመቶ ህዝብ ለድብርት በሽታ ተጋላጭ መሆኑን ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በየዓመቱ መጋቢት 29 የሚከበረውን የዓለም የጤና ቀን “ ስለ ድብርት እንነጋጋር ” በሚል መሪ ቃል የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተከብሯል ።
የዓለም የአዕምሮ ጤና ችግር አካል የሆነው ድብርት በዓለም 300 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብን ለጉዳት እየዳረገ ሲሆን፤በኢትዮጵያ ደግሞ 10 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ለድብርት በሽታ ተጋላጭ መሆኑ ሚኒስቴሩ ያወጣው መረጃ ያመለክታል ።
የአዕምሮ ጤና ችግር በየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ላይ የሚከሰትና ዋና ዋና መንስኤዎችም ማህበራዊ ቀውሶች ፤ ድንገተኛ ህመምና የተለያዩ ሱሶች መሆናቸውን ሚኒስቴሩ ጠቁማል ።
በአዕምሮ ጤና ላይ የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር እያደገ በመምጣቱ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚገባቸው ተመልክቷል ።
መንግሥት ለአዕምሮ የጤና ችግር አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት በተገቢው መልኩ ለመሥጠት ከአማኑኤል የአዕምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተጨማሪ በኮተቤ ሁለተኛው የአዕምሮ ሆስፒታል ተከፍቷል ።