Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በክልሉ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ 117 የፍትህ አካላትና ሠራተኞች ላይ እርምጃ ተወሰደ…የክልሉ ፍትህ ቢሮ

0 1,083

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

በትግራይ ክልል ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ 117 የፍትህ አካላትና ሠራተኞች ላይ ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ሥራ እገዳ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ ።

በሌላ በኩል በክልሉ በመንግስትና በህዝብ ሃብት ላይ ምዝበራ ፈጽመዋል፣ ፍትህን አዛብተዋል የተባሉ 577 ግለሰቦች ጉዳይ እየተጣራ መሆኑን የክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል።

ላለፉት ሁለት ቀናት የተካሄደው 6ኛው የክልሉ የተጠያቂነት ኮንፍረንስ ትናንት ተጠናቋል ።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አረጋይ ገብረእግዚአብሔር በወቅቱ እንደገለጹት በጥልቅ ተሀድሶ የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰድ ጀምረዋል።

በፍትህ ዘርፍ ሕብረተሰቡ ሲያማርር የቆየውን ችግር ለማጣራት ከዚህ ቀደም ውሳኔ ያገኙት ከ12 ሺህ በላይ የክስ መዛግብት ዳግም እንዲመረመሩ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአቃቤ ህጎች፣ በጠበቃዎችና በድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ላይ ዳሰሳዊ ምርመራ መደረጉን ነው የጠቆሙት።

በዚህም በሙስና ተከሶ ፍርድ የተሰጠውን ግለሰብ የጥብቅና ፈቃድ የመስጠትና ከግለሰቦች ጋር ባለ ቅርበት የፍትህ መዛባት የተፈፀመባቸው መዝገቦች መገኘታቸውን ጠቁመዋል፡

በተጨማሪም ሚስጥር የማውጣት፣ በጥቅማጥቅም መደለልና በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የክስ አቀራረብ ጥንቃቄ ጉድለት ጨምሮ ተገቢው ፍርድ እንዳይሰጥ የተደረጉ በርካታ መዝገቦች በፍተሻው መገኘታቸውን ተናግረዋል።

መረጃውን መነሻ በማድረግ በ270 ዓቃቤ ህጎች፣ ጠበቆችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ላይ የዲስፕሊን ክስ መመስረቱንና 117 በሚሆኑት ላይ ደግሞ ከጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ሥራ ማባረር እርምጃ መወሰዱን አቶ አረጋይ አስረድተዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አማኑኤል አሰፋ በበኩላቸው በክልሉ ከሚገኙት 458 ዳኞችና የሬጅስትራር ሠራተኞች ውስጥ በ233ቱ ላይ የዲስፕሊን ክስ መቅረቡን ጠቅሰዋል።

ከነዚህ ውስጥ 59 የሚሆኑት ጥፋተኞች ሆነው መገኘታቸውና 15ቱ ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጉን ጠቁመዋል።

የክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ብርሃነ ተኹሉ በበኩላቸው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሕዝብና የመንግስት ሃብት አጥፍተዋል ተብለው የተጠረጠሩ 577 ግለሰቦች ጉዳይ ላለፉት ስድስት ወራት እየተመረመረ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጽቢ ወንበርታ ወረዳ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ያለአግባብ ለአበል የተከፈለ 102 ሺህ ብርና ከመሬት ካሳ ጋር በተያያዘ በግለሰቦች ተወስዶ የነበረ ከ400 ሺህ ብር በላይ ተመላሽ መደረጉን ጠቅሰዋል ።

የመንግስትን ሃብት ዘርፈው የጠፉ የውሃ ሃብት ቢሮና የውሃ ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ  የሥራ ኃላፊዎች መኖሪያቤቶች እንዲወረሱ መደረጉንም ኃላፊው ተናግረዋል።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ የመንግስትና የሕዝብ ሀብትን ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል የሚያደርጉ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት የፍትህ ተቋማት ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል ።

የተጠያቂት ኮንፍረሱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው  የሕዝብና የመንግስትን ሀብትና ንብረት የሚያባክኑ ግለሰቦችን በመከታተል ወደ ህግ የማቅረብ ሥራ በዘላቂነት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

በአጥፊዎች ላይ እርምጃ መወሰድ መጀመሩንም ተሳታፊዎቹ  አድንቀዋል ።

የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ነዋሪ ወይዘሮ ወይኒ ኃይለማሪያም በሰጡት አስተያየት “በጥልቅ ተሃድሶ የተነሱ ችግሮችን መነሻ በማድረግ ጥፋት በፈፀሙት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ አስደስቶኛል “ብለዋል።

እርሳቸው እንዳሉት በሑመራ ከተማ ከስምምነት ውጭ የኤሌክትሪክ ምሰሶ የሚያመርትሥራ ተቋራጭ በህግ ተጠያቂ እንዲሆንና ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ እንዲያደርግ ተደርጓል።

በተጨማሪም ሕብረተሰቡ ፍትህ የለም እስኪል ድረስ ቅሬታ የፈጠሩበት ዳኞችና የፍትህ አካላት ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መንግስት ቁርጠኝነቱን ማሳየቱን ወይዘሮ ወይኒ ለአብነት ጠቅሰዋል።

የፍትህ አካላት፣ የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንዲጠናከሩ መደረጉ የተጠያቂነት አሰራርን ለማጎልበት እንደሚያግዝ የገለጹት ደግሞ የትግራይ ሰሜናዊ ምዕራብ ዞን ነዋሪ ወይዘሮ አብርኸት አባይ ናቸው።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy