NEWS

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ 2.7 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

By Admin

April 09, 2017

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚውል 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በስጦታና በቦንድ ግዥ ማበርከታቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡ሚኒስቴሩ ከክልል የዳያስፖራ ማህበራት ጋር ሰሞኑን በሀዋሳ ውይይት አካሂዷል ።

በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ደመቀ አጥናፉ በዚሁ ጊዜ ለኢዜአ እንደገለፁት በአውሮፓና አረብ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፉን ያደረጉት ባለፉት ሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ ነው ።

እንደ አቶ ደመቀ ገለፃ በየሀገራቱ በሚገኙ ሚሲዮኖች አማካኝነት ስለ ግድቡ ግንባታ አስፈላጊው ገለፃና ውይይት በመደረጉ ድጋፉ ተገኝቷል ።

በቦንድና በስጦታ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ በጊዜ ገደቡ ለመሰብሰብ ከታቀደው በ100 ሺህ ዶላር ብልጫ አለው ” ብለዋል

በሀገራቱ የሚኖሩ ኢትዮጰያውያንና ትውልደ ኢትዮጰያውያን ”በሀገሬ ልማት ዙሪያ አልደራደርም” በሚል መርህ ለግድቡ ግንባታ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል መግባታቸውን አስታውቀዋል ።

ባለፉት አመታት ለሁለት ጊዜ የተከበረው “የዳያስፖራ ቀን” በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጰያውያንና ትውልደ ኢትዮጰያውያንን በአገራቸው ልማት ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል ።

በየክልሉ የተቋቋሙ የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቶችና ማህበራት በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ግንዛቤ በማስጨበጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን አቶ ደመቀ አስታውቀዋል፡፡

የኦሮሚያ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ አብዱላዚዝ ኢብራሂም እንደገለፁት ማህበሩ በተለይ በሳውዲ አረቢያ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ በተደጋጋሚ ቦንድ ገዝተዋል፡፡

በክልሉ መንግስትና በኦሮሚያ ልማት ማህበር አማካኝነት በሚዘጋጁ የተለያዩ ስነ ስርአቶች ላይ በመገኘት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የማነሳሳት ስራ እየተሰራ መሆኑን አቶ አብዱላዚዝ ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ዳይሬክተር አቶ አብርሀም ስዩም በበኩላቸው ለተለያዩ አገልግሎቶች ወደ ጽህፈት ቤቱ ከሚመጡ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጰያውያን ጋር በህዳሴው ግድብ ግንባታ ዙሪያ ውይይት በማድረግ የቦንድ ግዥ እንደሚፈጽሙ እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡