Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

በድንገተኛ አደጋ የተፈተነው የወጣቱ ህልም

0 412

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ምናልባት አይታወቀው ይሆናል እንጂ ሁሉም ሰው የየራሱ ተሰጥኦ አለው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ተጠቅመውበት ሲለወጡ ከፊሎቹ ደግሞ መክሊታቸውን ሳያወቁት ቀርተው ሲባክኑ ይታያሉ። የማታ ማታም ውስጣቸውን ተረድተው የሚጠቀስ ተግባር አበርክተው የሚያልፉ አይጠፉም። ለዛሬ በጉብዝናው የወጣትነት ወቅት ተሰጥኦውን ተረድቶ ለለውጥ ከሚተጋ እንግዳ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንዲህ አቅርበነዋል።

ወጣት ቢኒያም አማረ ይባላል። ከልጅነቱ ጀምሮ የቅርጻ ቅርጽ ጥበብ ይማርከው ነበር። ቤተ ክርስቲያን አካባቢ የሚያያቸው የቅርጻቅርፅ ሥራዎች ግርምትን ይፈጥሩበት ስለነበር፤ እንዴት እንደተሠሩ ማወቅ ይፈልጋል፡፡ ያያቸውን ነገሮች አስመስሎ ለመሥራትም ይሞክራል፡፡ ተሰጥኦውን በአካባቢው ባሉ ነገሮች በመጠቀም ያዳብራል፡፡ ከእንጨትና ከድንጋይ ቅርጻ ቅርጽ ይሠራል፡፡ ይህ ችሎታና ፍላጎት አብሮት አደገ፡፡ እያደርም በሙያው መሰማራት ፍላጎቱ ሆነ፡፡ የተፈጥሮ ችሎታውን ያግዘው ዘንድ በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ሥልጠና ኮሌጅ በኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ዲፕሎማውን አገኘ፡፡

ወጣቱ በ1995 .ም አንድ ሥራ መሥራት ጀመረ፡፡ ድንጋይን ወደተፈለገው ቅርጽ በመለወጥ ለተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ማስዋቢያነት ያውላቸዋል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ ነገሮችን በማስጌጥ ሥራ የጀመረው ወጣት ቢኒያም ሥራ ቀስበቀስ እያደገ ሄደ፡፡ አሁን የተለያዩ መንግሥት ተቋማትን፣ ትምህርት ቤቶችንና የግል መኖሪያ ቤቶችን የሕንፃ አጨራረስ የማስዋብ ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጪም የተለያዩ ቤተ እምነቶችን የበረንዳ መደገፊያና ሌሎች ጌጣ ጌጥ ሠርቷል፡፡

በአዲስ አበባ መርካቶ የሚገኘውን የቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን የመግቢያ በር፣ጉለሌ የሚገኘውን የእግዚአብሔር አብ ቤተክርስቲያን የበረንዳ ጌጣ ጌጥ የእርሱ የእጅ ሥራ ውጤቶች ናቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪም በሻሸመኔ የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንን በሮች የሠራ ሲሆን፤ ይህንን የተመለከቱ የአርባ ምንጭ መዲኃኒያለም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችም በእርሱ የእጅ ሥራ ቤተክርስቲያኑን እንዲያስውብ ተዋውለዋል፡፡

ከቤተ እምነቶች በተጨማሪም ሆቴሎችን፣ ተቋማትንና መኖሪያ ቤቶችን ያስውባል፡፡ በአዲስ አበባ ሽሮሜዳ እየተሠራ ያለውን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ቤተ መንግሥት እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህ የግንባታ ሥራ ላይ የዛምራ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ንዑስ ተቋራጭ በመሆን ቢኒያም አማረ የተፈጥሮ ድንጋይ ዓርት ኢንዱስትሪ የማስጌጥ ሥራውን እንዲሠራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

የወጣት ቢንያም ሥራ እየታወቀና ሙያው እያደገ ሲሄድ በሥሩ ሌሎች ባለሙያዎችን ቀጥሮ ማሠራት ጀመረ፡፡ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረው ይህ የድንጋይ ጥበብ ‹‹ቢኒያም አማረ የተፈጥሮ ድንጋይ ዓርት ኢንዱስትሪ›› ተብሎ ተሰየመ፡፡ ኢንዱስትሪው በየካ ክፍለ ከተማ ካራ በሚባለው አካባቢ የራሱ የድንጋይ ጌጣጌጥ ማምረቻ ፋብሪካ አለው፡፡ በፋብሪካው ውስጥ ድንጋዮች ወደሚፈለገው ቅርጽ የሚለወጡበትና የሚጠረቡበት ማሸኖች አሉ፡፡

ቢኒያም አማረ የተፈጥሮ ድንጋይ ዓርት ኢንዱስትሪ ለ250 ወጣቶች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ኢንዱስትሪው ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ በተጨማሪ ራሳቸውን ችለው ሥራ እንዲፈጥሩ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም በፋብሪካው ውስጥ በነበራቸው ቆይታ የድንጋይ ቅርጻቅርጽ ሙያቸውን በማሳደጋቸው ነው፡፡

ኢንዱስትሪው በውስጡ ተቀጥረው ለሚሠሩ ወጣቶች ሥልጠና ይሰጣል፡፡ እንደሚታወቀው በብዙ የማሰልጠኛ ተቋማት ሥልጠና የሚሰጠው ተማሪዎች እየከፈሉ ነው፡፡ በቢኒያም አማረ የተፈጥሮ ድንጋይ ዓርት ኢንዱስትሪ ግን ሠልጣኞች እየከፈሉ ሳይሆን እየተከፈላቸው ነው እውቀት የሚሸምቱት፡፡ ለዚህም ሲባል በአዲስ አበባ ለገጣፎ ለገዳዲ ማሠልጠኛ በመክፈት ወጣቶችን አሠልጥኖ በቋሚነት ቀጥሯል፡፡ እንደ ቢኒያም ዕቅድ የማሠልጠኛ ተቋሙ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ሙሉ ኮሌጅነት ያድጋል፡፡ ሙያው በአገሪቱ ብዙም ያልዳበረና በሠፊው ሊሠራበት የሚገባ በመሆኑ በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት የቢኒያም ዕቅድ ነው፡፡ ይህ ይሳካ ዘንድም ከመንግሥት የመስሪያ ቦታ ይሰጠው ዘንድ እየጠየቀ ነው፡፡

ለኢንዱስትሪው እዚህ ደረጃ መድረስ እስከአሁንም ብዙ የመንግሥት ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡ ለሥራው የሚያገለግሉ ማሽነሪዎችንና የተለያዩ የቅርጻቅርጽ ማውጫዎችን ያለቀረጥ የማስገባት መብት ከመንግሥት ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም ማሽነሪዎችን ከቻይና እያስገባ ይሠራል፡፡ ለማሽነሪዎች የመለዋወጫ ዕቃ ደግሞ በራሱ ኢንዱስትሪ ያመርታል፡፡ በራሱ ባለሙያዎችም ገጣጥሞ ይለዋውጣል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኢንዱስትሪው በተለያዩ አገራት ያሉ የቅርጻቅርጽ ሙያ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ወደ አገር ውስጥ ያመጣል፡፡ የኢንዱስትሪው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ራሱ ወጣት ቢኒያም አማረ በቻይናና በሌሎች አገሮች በመሄድ ሙያውን የሚያዳብሩ ሥልጠናዎችን ወስዷል፡፡

ወጣት እንዳልካቸው መካሻ በቢኒያም አማረ የተፈጥሮ ድንጋይ ዓርት ኢንዱስትሪ ተቀጥረው ከሚሠሩት አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ ወደእዚህ ኢንዱስትሪ ከመግባቱ በፊት ያለ ሥራ ተቀምጦ ነበር፡፡ ሥራ ከጀመረ ሦስት ዓመታት ሆነውታል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከራሱም አልፎ ቤተሰቦቹን ማገዝ ችሏል፡፡ ወጣቱ እንደሚለው ከዚህ ሥራ ያገኘው ገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡ የሥራ ፍቅርንና ሙያን አግኝቷል፡፡ ‹‹ምንም አይጠቅምም የምለው ድንጋይ ዳቦ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፤ ጥበብ ሆኖ አግኝቼዋለሁ›› የሚለው ወጣት እንዳልካቸው ሥራ ሠርቶ ማደር እንደሚያኮራ አይቷል፡፡

ሌላኛው ወጣት ዲታ ጣሰው እንደሚለው ወደ እዚህ ኢንዱስትሪ ሲገባ ገና የሥራውን ባህሪም አለመደውም ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ግን ሥራውን መልመድ ብቻ ሳይሆን የሙያ ባለቤትም እየሆነ መጣ፡፡ አሁን ላይ የፈጠራ ክህሎት በማዳበር የተለያዩ አዳዲስ ቅርጻ ቅርጽን መሥራት ችሏል፡፡ በሙያም በገንዘብም ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ ከራሱም አልፎ ቤተሰቦቹን ማገዝ ችሏል፡፡

ይህ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድልን የፈጠረ፤ የቅርፃ ቅርፅና የጌጣጌጥ ሥራዎችን በስፋት ያስተዋወቀው ቢኒያም አማረ የተፈጥሮ ድንጋይ ዓርት ኢንዱስትሪ በቅርቡ አንድ አደጋ ደርሶበታል፡፡ ባሳለፍነው ዕሁድ መጋቢት 24 ቀን 2009 .ም ቀን ድንጋይ ሙሉ የጫነ ከባድ የጭነት መኪና ከመስመር በመውጣት በፋብሪካው ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡ በውስጡ የነበሩት ማሽኖችና ሌሎች ቁሳቁስ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል፡፡ ሰባ ያህል ሠራተኞችም ለጊዜው ሥራ ፈተዋል፡፡ በተፈጠረው አደጋ የሰው ሕይወት ባለማለፉ ፈጣሪውን ያመሰገነው ቢኒያም ‹‹ዕለቱ ዕሁድ ባይሆን ኖሩ የብዙ ሠራተኞች ሕይወት ያልፍ ነበር›› ይላል፡፡ እንደ ወጣት ቢኒያም ገለጻ ፋብሪካው ለዚህ አደጋ የተጋለጠው ያለበት ቦታ ከጎዳና ዳር በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በፋብሪካው በኩል ያለው መንገድ ተዳፋትነት ስላለው ለእንዲህ ዓይነት አደጋ ይጋለጣል፡፡

በተፈጠረው አደጋ ሥራ የሚሠራባቸው ማሽኖች በመበላሸታቸው ለጊዜው ሥራው ቆሟል፡፡ አንዳንዶቹ ሠራተኞች ለገጣፎ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ የሄዱ ቢሆንም ዋናው ፋብሪካ ላይ ያሉት ለጊዜው ከሥራ ውጪ ሆነዋል፡፡

ወጣት ቢኒያም እንደሚለው በአደጋው ወደ አራት ሚሊዮን የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡ በቋሚነት ለተቀጠሩ ሠራተኞች ደመወዝ ይከፍላል፡፡ ይህ ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል የፈጠረ ኢንዱስትሪ ወደነበረበት እንዲመለስና በድንገተኛው የመኪና አደጋ ፈተና ያጋጠመው ህልሙ ይሳካለት ዘንድ የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ያሳስባል፡፡ በተለይም ከቦታው አስቸጋሪነት የተነሳ በቀጣይም ተመሳሳይ አደጋ ያጋጥማል የሚል ሥጋት አለው፡፡ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት ምቹ ቦታ ቢሰጡት ለብዙ ወጣቶች የሥራና የሙያ ዕድል የመፍጠር ዓላማ እንዳለው ተናግሯል፡፡

ዋለልኝ አየለ

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy