Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

«ተግሳፅም ለጠባይ ካልሆነ አራሚ፤ መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ»

0 544

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ታላቁ የብዕር ሰው ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል አዝማሪና የውሃ ሙላትበሚል ርዕስ ካስቀሩልን ዘመን ተሻጋሪ ግጥም መካከል የመጨረሻዎቹ ሁለት ስንኞችን በማስቀደም ጽሁፌን ልጀምር፤

ተግሳፅም ለጠባይ ካልሆነ አራሚ፣ መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ

እውነት ነው! ተግሳፅም ለጠባይ ካልሆነ አራሚ፤ መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚ። መናገር ማዳመጥ ከሌለበት ጉንጭ ማልፋት እንጂ ከቶ ሌላ ምን ሊያተርፍ ይችላል፤ ምንም። እንደ አለመታደል ሆኖ ግን ዙሪያችንን የከበበን ሁሉ ተናጋሪ እንጂ ሰሚ አልሆነም፡፡ ሰሚ አልባ ከሆንም ሰነባበትን፡፡

ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሚዲያዎች ላይ ነግሰው ከሰነበቱ ወሬዎች መካከል በእውነት ከሆነ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስድስተኛ ዓመት በዓል ቀጥሎ የኢፌዴሪ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ይፋ ያደረገው ጥናት ነበር ብል ስህተት አይሆንም። መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንጻር የህዝብ ተሳትፎ ማነቆዎች፣ መንስኤዎች እና የመፍትሄ ሀሳቦችበሚል ይፋ የተደረገው የዚህ ጥናት ውጤት ለእኔ ከጥናትም በላይ ውስጤ የቀረ ሆኗል። ይሄንን ሰምተው ይሆን? ሰምተው ከሆነ ሰሚ ነዎት፤ ካልሆነ ግን ያው ነዎት ማለት ነው፡፡

ይሄ፣ ሰምተዋል? ያልኩዎት ጥናት የምናውቀውን ችግር በማናውቀው መንገድ የነገረን ክሽን ያለ ጥናት ነው። ምን ማለቴ ነው? በዚህ አገር ላይ በተለይም በሚዲያዎችና በህዝብ ምክር ቤቶች ዘንድ ያለው የህዝብ ተሳትፎ የይስሙላ ነው። ይሄንን እናውቃለን። የማናውቀው ወይንም ለማወቅም የማንተጋለት ለምን? የሚለውንና ከዚህ ችግር በስተጀርባ ላለው አውራ ችግር ሊሰጥ የሚችለውን ሳይንሳዊ ምላሽ ነው፡፡ እነሆ አሁን ደግሞ ምስጋና ለማዕከሉ ይሁንና ይሄንን ጥያቄ መልሶልናል።

በዚህ ጥናት መሰረት ለህዝብ ተሳትፎ አነስተኛ መሆን አስፈጻሚው አካል የአንበሳውን ድርሻ ይዟል። አስፈጻሚው ምክር ቤቱ ጠንክሮ እንዲወጣ አይፈልግም፤ ወይንም እንዲወጣ ያለው አመለካከት በሚፈለገው ደረጃ አይደለም ተብሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምክር ቤቱ ከተጠናከረ ይጠይቀኛል ያስጨንቀኛል ብሎ መፍራቱ እንደሆነ ጥናቱ አሳይቷል። ስለሆነም በተለያዩ የማይታዩ ተግባራት አማካኝነት ምክር ቤቱን እያዳከመ እንደሆነ ይሄው ጥናት ነግሮናል።

የአስፈጻሚው እጆች በምክር ቤቱ ላይ ብቻ የተገቱ አይደሉም። የህዝብ ዓይንና ጆሮ ይሆናሉ ተብለው በሚጠበቁትና በሚደከምላቸው ሚዲያዎች ላይም ጭምር እንጂ፡፡ ሚዲያዎች በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚ አካላት በሚያሳድሩባቸው ጫና ምክንያት ጠንክረው ሊወጡ እንዳልቻሉ ተረጋግጧል። በጥናቱ መሰረትም ሚዲያው የአስፈጻሚው ደጋፊ ነው ተብሏል፡፡ ይኸው ሚዲያ የመንግሥት አንዳንዴም የኢህአዴግ ብቻ ነው ብሎ የማሰብ ችግር በአስፈጻሚው ዘንድ ስለመኖሩም ታውቋል። በዚህም ምክንያት መልካም አስተዳደር ላይ አተኩረው የሚሰሩትን ጋዜጠኞችና ሚዲያዎች ችግር ፈላጊ አድርጎ መመልከት የአስፈጻሚው ባህሪ ነው ተብሏል።

ልብ ይበሉልኝ፤ እኔ ጥናቱን በሙሉ እዚህ ላይ ላቀርብ አቅሙም የለኝ፤ ገጹም አይበቃኝም፡፡ ነገር ግን ጥናቱ ከሚዲያው አንጻር የሄደበትንና የደረሰበትን ከራሴ አስተያየት ጋር አዋድጄ ማቅረብ እፈቅዳለሁ፡፡ ወደዚያም አለፍኩ፡፡

መልካም አስተዳደር ላይ ያሉ ህጸፆችን ነቅሶ የሚሰራ ሚዲያ ችግር ፈላጊ ተብሎ በሥራ አስፈጻሚው እየታየ ስለመሆኑ ጥናቱ አሳይቷል። በሚዲያው አመራሮችና ጋዜጠኞች ላይም ማጥላላት የእጃቸው ነው ተብሏል። በጣም የሚገርመው ግን አሁን ሚዲያውን እያዳከመ ነው ተብሎ የተለየው አስፈጻሚው፤ በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ መድረኮች ሚዲያው አላገዘንም፤ ሚዲያው በህዝብ ውስጥ ያለውን ችግር አላሳየንም፤ ሙስናን አላጋለጠልንም፤ ብልሹ አሰራርን አልገላለጠልንም ወዘተረፈ እያለ የወቀሳ ናዳ ሲያቀርብበት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው፡፡

እንዲያውም ሚዲያው አዝማሪ ሆኗል ተብሎም ተደምድሞ ነበር፡፡ በተለይ ይህች የአዝማሪነት ስያሜ በወቅቱ በጣም አነጋጋሪና ኮርኳሪም እንደነበረች የሚያውቅ ያውቃታል፡፡ ሚዲያው አዝማሪ እንዲሆን መሰንቆውን ያቀበለው ማነው? ዜማ ከአዝማሪው ቢሆንም ግጥም ወርዋሪው ማነው? አዝማሪውንስ የሚሸልመው ማነው? የሚሉት ጥያቄዎች በአግባቡ ሳይመለሱ ተደባብሰው ማለፋቸውን አንዘነጋም፡፡ ምስጋና ለዚህ ማዕከል ይሁንና ይሄን ጥያቄ ገላልጦ መልሶታል፡፡

እነሆ አሁን ደግሞ አስፈጻሚው ሌላ ስም በጥናቱ በኩል አቀብሎናል፡፡ የአሁኑ የሚዲያ ስያሜና ሚዲያው የተገለጸበት አግባብ ወይንም አስፈጻሚው የአገራችን ሚዲያ ባለሙያዎችን ምን አይነት ባለሙያ አድርጎ እንደሚያያቸው ልብ ብሎ ላጤነው ሁሉ የሚያስቆጭና የሚያንገበግብ ነው፡፡ ሚዲያው፤ የታዘዘውን ብቻ የሚያቀርብ ባሬስታነው ተብሏል፤ አስፈጻሚው ሚዲያውን እንደ ባሬስታ አድርጎ ይመለከተዋልም ተብሏል።

እውነት ነው። አሁን አሁን እኮ ሚዲያው የተነገረውን ይዞ ይሮጣል እንጂ ለምን ብሎ ስለተነገረለት ጉዳይ ወደ ታች ወደ ህዝቡ ወረድ ብሎ አይጠይቅም፤ እውነትና ውሸትነቱንም አያረጋግጥም፡፡ ስለዚህ ሚዲያው በአንዴ ከአዝማሪነት ወደ ባሬስታነት ተሸጋግሯል ማለት ነው፡፡ ምርጥ እድገትና ትራንስፎርሜሽን፡፡ ምርጥ ሽግግር፡፡ እኔ ግን ይሄ ትራንስፎርሜሽን በአፍንጫዬ ይውጣ እላለሁ፡፡ በበኩሌም ጋዜጠኝነት ከምንም በላይ የሚወደድ ሙያ ነው ብዬ ስለማምን፤ ሚዲያው አዝማሪም ባሬስታም አይመጥነውም ባይ ነኝ፡፡

ይህ ማለት ግን የአገራችን ሚዲያ በተጫባጭ አዝማሪ አልሆነም፤ ባሬስታም አይደለምብሎ መከራከር ውሃ የማያነሳ ክርክር መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ቁም ነገሩ ወይንም ክርከሩ ያለው ግን ሚዲያውን የዚህ አይነት ቅርጽ የሰጠው ማነው? የሚለው ላይ ነው፡፡ አሁን ጥናቱ ይሄንን በአግባቡ መልሶታል፡፡ የአንድ አገር ሚዲያ የአገሪቷ ፖለቲካል ኢኮኖሚ መገለጫ ስለመሆኑ ምንም የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ የሰሜን ኮሪያ ሚዲያ ከአሜሪካ ሚዲያ አንድ ሊሆን አይችልም፡፡

የኢትዮጵያም ሚዲያ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚመሩትን ሰዎች ይመስላል፡፡ ልብ ይበሉ ያልኩት የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚመሩ እንጂ የኢትዮጵያን ፖለቲካ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልዩነትን በአግባቡ የሚቀበል፣ ብዝሀነትንም የሚያስተናግድ፣ ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ የሚካሄድበት፣ ማንም ያመነበትን የሚጽፍበትና የመሰለውን የሚናገርበት፣ ያልመሰለውንም በግልጽ የሚቃወምበት ሆኗል፡፡

ይሄንን እውነታ መሬት ላይ የሚያስፈጽሙ ወይንም እንዲያስፈጽሙ ከአደራ ጋር በካርዳችን ኃላፊነት የሰጠናቸው በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚዎች ግን ሚዲያውን ከአገሪቷ ፖለቲካ በተቃራኒ እንዲጓዝ አድርገውታል፡፡ የህዝብ አገልጋይነታቸውን ዘንግተው የህዝብ አገልጋይ ይሆን ዘንድ እልፍ በጀት የሚበጀትለትን ሚዲያ የግላቸው አድርገው በማሰብ፤ ይሄን ጻፍ፤ ያንን አውጣ ይሄንን ተወውማለት አብዝተዋል፡፡ ይሄ የእኔ ድምዳሜ አይደለም፤ የጥናቱ እንጂ፡፡

ጥናቱ ዛሬ ይሄንን ነቅሶ ያውጣው እንጂ፤ ሁሌም የሚባል በተለይ በሙያው ውስጥ ያለን የምናውቀው፣ በተለያዩ የግምገማ መድረኮችም ስንለው የኖርነው ነው፡፡ ለዚያም ነው የዚህን ጽሁፍ ተግሳፅም ለጠባይ ካልሆነ አራሚ፣ መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚብዬ ርዕስ መስጠቴ፡፡ አዎና አዝማሪ መባል ተግሳፅ ነው፤ ባሬስታም መባል ተግሳጽ ነው፡፡ ግን ሰሚ ካልተገኘ ከንቱ ነው፡፡ ነገ ደግሞ ሌላ ስያሜ የእጃችን ነው፡፡

አስፈጻሚው በጋራ ሲሆን ስለሚዲያው የሚመክረውና የሚያስበው በግሉ ቢሮው ውስጥ ሲሆን ከሚያስበው ለየቅል ነው፡፡ ይሄ የእኔ ድምዳሜ ነው፡፡ ምክንያቱም ሚዲያው አዝማሪ ሆኗልያለ አስፈጻሚ፤ የሆነ ሥራውን የሚያጋልጥ ነገር ሲጻፍበት ወይንም ፕሮግራም ሲሰራበት ስልኩን ብድግ አድርጎ ለሚዲያ አመራሩ ይደውልና ምን እየሰራችሁ ነው፤ ይሄ ለማን ይጠቅማል፤ ህዝብና መንግሥትን ለማቃቃር ነው፤ ዓላማችሁ ምንድን ነውይባልልኛል፡፡ ቆይ ቆይ ቆይ በዚህ አይነቱ ዘገባ የሚቃቃረው ህዝብና መንግሥት? ወይንስ የዚያ ብልሹ አሰራር ባለቤት የሆነው ተቋም አመራርና ህዝብ? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ህዝብና እርስዎ ይጨርሱት፡፡

አሁን አሁን እኮ የአስፈጻሚው የልብ ትርታ እየታየ ሆኗል ዜናም ሆነ ፕሮግራም የሚሰራው፡፡ ይሄንን ብጽፍ ያንን ብሰራ እከሌን ያስደስተው ወይንስ ያስቀይመው ይሆን? ማለትም በርክቷል፡፡ ትንሽ ከዚህች ግለ ሳንሱር ወጣ ብሎ የሚሰራ ሚዲያና ጋዜጠኛ ከተገኘም ውርጅብኙ አይጣል ነው፡፡ ማሸማቀቁም የትየለሌ፡፡ በዚህም ምክንያት ይመስላል ዛሬ ዛሬ ሚዲያው ራሱ የህዝብን ብሶት ከማቅረብ ይልቅ ያልተባለውን ወይንም ዋና ጉዳይ ያልሆነውን መዘገብ ላይ ተጠምዶ ይታያል፡፡

አስፈጻሚው ከላይ የሰጠውን አቅጣጫ እንዳለ ማቅረብ፣ በህዝብና በመንግሥት መካከል እውነተኛ ድልድይ አለመሆን፣ የህዝብ አገልጋይ ነኝ ብሎ አለማሰብ፣ ልማታዊ ጋዜጠኝነትን በተሳሳተ መንገድ በመረዳት ስኬት ላይ ብቻ ማተኮር፣ ችግር ተፈጥሮ እንዳልተፈጠረ ማድረግ ሌላም ሌላም የዛሬዎቹ የህዝብ ሚዲያዎች መለያ ባህሪ ሆኗል፡፡ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው በዋናነት ራሱ አስፈጻሚው ቢሆንም የጋዜጠኛውና የሚዲያ አመራሩም ድርሻ ቀላል አይደለም፡፡

እውነት እናውራ ከተባለ እስኪ ጋዜጠኝነቱን በትክክል የሚቀበልና ጋዜጠኛ ነኝ ብሎ የሚናገር አለ? ጋዜጠኞች እንዳንተዛዘብ አስተውላችሁ መልሱ፡፡ በእርግጥ መታወቂያችሁ የሆነ የሥራ ደረጃንና ተቋምን በመጥቀስ ጋዜጠኛ መሆናችሁን ይናገራል፤ እናንተ ግን በጭራሽ በሙያው ውስጥ የላችሁበትም፡፡ አብዛኛዎቻችሁን ማለቴ ነው፡፡ ምክንያቱም የዛሬ ጋዜጠኝነት እኮ ከተቀረው የመንግሥት ሰራተኛ በምንም አልተለየም፡፡ ጠዋት ይገባል፤ 11 ሰዓት ይወጣል፡፡ ከቢሮው ውጭ ስለ ሥራ ማሰብ አይፈልግም፡፡ መንገድ ላይ የሚታይ የህዝብ ብሶት ወይንም ጥያቄ በቢሮ ደረጃ እስካልታዘዘ ድረስ የሚሰራም የሚወራም አይደለም፤ እንደማንኛውም መንገደኛ አይቶ ከንፈርን መጥጦ አይይይይይ መንግሥት ብሎ አማርሮ ይሄዳል እንጂ ለምን? ብሎ እንደ ህዝብ ድምጽ ለመናገር ወኔውም ፍላጎቱም የለም፡፡

ለምን?

ምክንያቱም ጋዜጠኛ መጠሪያ ስሙ እንጂ፤ ውስጡ የመንግሥት ሰራተኛነት መንፈስ ነው የነገሰው፡፡ ስምና ግብር ደግሞ ለየቅል ነው፡፡ ያ ባይሆን ኖሮማ ወርቅነህ የተባለ ሰው ለዕለት ጉርሱ ቸግሮት መንገድ ላይ ጫማ ባልጠረገ፣ ንግሥት የተባለች ሴትም የቢሮ ጽዳት ላይ ባልተቀጠረች፡፡ ስለሆነም የዛሬ ጋዜጠኛ ከቢሮ የተረፈ ሥራ ወደ ቤትህ ወስደህ ሥራ ሲባል ብሶት የሚደረድር፣ ሰበብ የሚያበዛ ሆኗል፡፡ የዚህ አይነቱ ጋዜጠኛ ስሙ እንጂ እንዴት በምግባሩ ጋዜጠኛ ሊባል ይችላል? እንዴትም፡፡

ከጋዜጠኛው መለስ የሚዲያ አመራሩም ለሙያው ባሬስታ መባል እጁ ከደሙ ንጹህ አይደለም፡፡ በየተቋሙ ያለው የሚዲያ አመራር ለትክክለኛው የጋዜጠኝነት መርህ የወገነ አይደለም፡፡ ይልቁንም ውግንናው እሱን በወንበሩ ላይ ላስቀመጡት አስፈጻሚዎች ነው፡፡ ስለሆነም ስለእነሱ ሲል ሙያው በማይፈቅደው መልኩ የሚሰነዘሩ ጣልቃ ገብነቶችን አሜን ብሎ ይቀበላል፡፡ አሜኑንም ወደ ታች በአቅጣጫ መልክ ያወርዳል፡፡ ከዚያ ሚዲያውን ከትክክለኛው መስመር ገፍትሮ ያስወጣዋል፡፡ ተንገዳግዶ ወደ መስመሩ ለመመለስ የሚሞክር ካለም ጥናቱ እንዳለው በማይታዩ እጆቹ መልሶ ያዳክመዋል፤ ይጥለዋል፡፡ ይሄንን አመራሩ አሳምሮ ያውቀዋል፡፡ አመራሩ ይሄን የሚያደርገው አምኖበት ነው ማለት አልችልም፡፡ ተገዶ እንጂ፡፡

በአጠቃላይ ማለት የምችለው ይሄ ሁሉ የሚዲያው ችግር የሚታወቅ፣ የሚባል፣ ሁሌም የሚዘመር ነው፡፡ አዲሱ ነገር ከችግሩ በስተጀርባ ያለው ተጠያቂ አካል ተለይቶ መውጣቱ ነው፡፡ አሁን ችግሩ ብቻ ሳይሆን የችግሩ ባለቤትም ተለይቶ ወጥቷል፡፡ ሰሚ ካለ ችግሩና ከነባለቤቱ ተነግሯል፡፡ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል እንዳሉት ግን ሰሚ ካልተገኘ አሁን የተነገረውም ከንቱ ጩኸት መሆኑ አይቀርም፡፡ ተግሳፅም ለጠባይ ካልሆነ አራሚ፤ መናገር ከንቱ ነው ካልተገኘ ሰሚማለቴ ለዚህ ነው፡፡

አርአያ ጌታቸው

 

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy