CURRENT

ቱሪዝም አዲሱ የቻይና-አፍሪካ የአጋርነት ሀዲድ

By Admin

April 28, 2017

ባለፈው ዓመት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች በአሉታዊ ውጤታቸው ሁሉንም ተጎጂ አድርጓል፡፡ በተለይም የፀጥታ ጉዳይ በቀጥታ ከገቢያቸው ጋር የሚገናኙትን የቱሪዝም መዳረሻዎች ማዳከሙን ለመናገር ብዙ ጥናት አይፈልግም፡፡ እንኳንስ መዳረሻዎቹ ባሉባቸው አካባቢዎች የሚፈጠር የፀጥታ ችግር ቀርቶ በማንኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚኖር ውስጣዊ አለመረጋጋት ጎብኚዎችን ለማራቅ በቂ ምክንያት መሆን ይችላል፡፡

ይሄ ደግሞ ወትሮም ቢሆን ከፍተኛ ውድድር ባለበት የቱሪዝም ዘርፍ ላይ በብርታት ከመዝለቅ ይልቅ ጉዞውን አንድ ወደፊት ሁለት ወደኋላ ያደርገዋል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ባለሙያዎች የቱሪዝም መስክ ላይ የተካሄዱ ዓለም አቀፍ ጥናቶች አሉ፡፡ እናም አብዛኞቹ ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እ.አ.አ 1950 በኋላ ባሉት ዓመታት ውስጥ የዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ቀዳሚ ፍላጎት ሰላምና ፀጥታ መሆናቸውን ያረጋገጡ ሆነዋል፡፡

ለዚህም ሁለት አብይ ምክንያቶች በቀዳሚነት ይቀመጣሉ፡፡ በቀዳሚነት ከተጠቀሰው ዓመት በኋላ ከመኖሪያ አካባቢ ተነስቶ አገር መጎብኘትና በተለያዩ ጉዳዮች ከአገር አገር መንቀሳቀስ ለብዙሃን ‹‹ቅንጦት›› መሆኑ አብቅቷል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዘመን ከአንድ አካባቢ ወደ ሌሎች ስፍራዎች መንቀሳቀስ በአንድ ማሕበረሰብ የኢኮኖሚ መደብ ልዩነት የሚወሰን መሆኑ እየጠበበ መጥቷል፡፡ እንደ አለም አቀፍ ሁኔታ ዘርፉ ላይ ገና ብዙ መስራት ቢጠይቅም፤ ሰዎች ከወር ገቢያቸው ቀንሰውም ቢሆን ለጉብኝታቸው ማዋልን የኑሯቸው አካል ማድረግ ጀምረዋል፡፡ በመሆኑም የጉብኝት ጊዜያቸው ጤናማና ደህንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን አጥብቀው ይሻሉ፡፡

በሌላ በኩል የቱሪዝም ዘርፍ የበለፀጉት አገሮች ብቻ አጀንዳ አይደለም፡፡ አፍሪካን ጨምሮ ሌሎች በማደግ ላይ የሚገኙ አህጉሮችም ሳይቀሩ የትኩረት ማዕከል ሆነዋል፡፡ ስለዚህ እነዚህ አገሮች ከዘርፉ በስፋት ተጠቃሚ ለመሆን የውስጥ ፀጥታቸውን ማስጠበቅ የህልውና ጉዳይ ማድረጋቸው አይቀርም፡፡ በመሆኑም ቱሪዝምን ከውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት ነጥሎ መመልከት ስለማይቻል ‹‹ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ›› የሚሰኘውን ዘርፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ ‹‹ሁከት አልባ›› ማድረግ ቀዳሚ አጀንዳ ይሆናል፡፡

በእርግጥ ቀዳሚው ጉዳይ ሰላም ይሁን እንጂ የአገልግሎት ጥራት ከሌለ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ተወዳድሮ ማሸነፍ የማይታሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ቱሪዝምን ከሰላም ነጥሎ መመልከት ካለመቻሉ ባሻገር አገሮች የቱንም ያህል በመስህብ ቢሞሉ መስተንግዷቸው ጎብኚን ካላረካ ውድድሩ ይከብዳል፡፡ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ በጊዜያዊነት አጋጥሟት የነበረውን ሰላም ወደ ነበረበት አስተማማኝ ደረጃ መመለስ ቀዳሚ ስራዋ ቢሆንም የአዳዲስ ጎብኚዎችን ቀልብ ለመሳብ መዳረሻዎቿን ምቹ ማድረግ ይጠይቃታል፡፡ ……

ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ አጋፋሪነት ተካሂዶ የነበረው 59ኛው የተባበሩት መንግስታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የአፍሪካ ኮሚሽን (ካፍ) ስብሰባ፤ ትኩረት ከሰጣቸው ክንውኖች መካከል የሩቅ ምስራቅ እስያ አገሮች በተለይም ከክፍለ አህጉሩ የግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቷ ቻይናን ወደ አፍሪካ ለመሳብ በሚያስችል ብልሀት ዙሪያ መክሯል፡፡

በአሁኑ ወቅት ቻይና የበለፀጉትንም ሆነ ገና የእድገት ማማን በርቀት የሚያማትሩ ታዳጊ አገሮች ለመቋደስ የሚጓጉትን ሰፊ ሃብት ይዛለች፡፡ በጉብኝትና በስራ ጉዳይ የሚያሳልፉ ቻይናውያን ቁጥር በእጅጉ እያደገ መምጣቱ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብቻ ቻይናውያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ አገራትን ለመጎብኘት 261 ቢሊዮን ዶላር ከኪሳቸው አውጥተዋል፡፡

በአጠቃላይ በመላው ዓለም ከ130 ሚሊዮን በላይ ቻይናውያን ከቦታ ቦታ መዘዋወራቸውን የሚጠቅሱት ሪፖርቶች፤ በወቅቱ አዲስ ክብረወሰን ማስመዝገባቸውን ያሳያል፡፡ የተጠቀሰው የቻይናውያን ዜጎች አጠቃላይ ወጪ ከ2015 ጋር ሲነፃፀር 12 በመቶ ማደጉን ያሳያል፡፡

እንደአለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት ሪፖርት ከሆነ፤ የቻይናውያን ጎብኚዎች ቁጥር በየዓመቱ በአማካይ ስድስት በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ እ.አ.አ 2012 ጀምሮም ቻይናውያን በየአገሩ ሲጓዙ የሚያወጡት ወጪ በሁለት አኃዝ አድጓል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ግልፅ ነው፡፡ ቻይናውያን ለረጅም ዘመናት ከኋላቀር ኢኮኖሚ ለመውጣት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ዛሬ የደረሱበትን የስኬት ደረጃ በመቆናጠጣቸው ዜጎቻቸው ለኢንቨስትመንትም ይሁን ለእረፍት ጊዜ ባህር መሻገርን ባሕላቸው አድርገዋል፡፡ ኢትዮጵያም ከዚህ የቻይናውያን ስኬት ተሞክሮ መቅሰሟ እንደተጠበቀ ሆኖ ለሁሉም ክፍት የሆነውን ውድድር ፈጥና መቀላቀል ይገባታል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተው ‹‹በቻይና የቱሪዝም ዘርፍ ከ10 በመቶ በላይ የኢኮኖሚ ድርሻ አለው›› ያሉት የቻይና ብሔራዊ የቱሪዝም አስተዳደር ምክትል ሊቀመንበር ሻዎ ዌ፤ ይሄም ለአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትና የሥራ ዕድል የላቀ አስተዋጾ እያበረከተ እንደሚገኝ ይጠቅሳሉ፡፡ በሰው ልጆች ቀደምት ስልጣኔ ውስጥ የረጅም ታሪክ ባለቤቷ አፍሪካም በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ድርሻዋን እያሳደገች በመሆኑ ቻይና በአዳዲስ መስኮች አብራ የመስራት ፍላጎቷ አሻቅቧል፡፡

አፍሪካና ቻይና በሁለትዮሽ ስትራቴጂክ አጋርነት የጀመሩትን የትብብር መንገድ በቱሪዝም ዘርፍ መድገም የአዲሱ ጅምር ማሳያ ይሆናል፡፡ ለዚሁ ሲባልም ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ምክትል ሊቀመንበሩ ይጠቅሳሉ፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የቻይናውያን ዓለም አቀፍ ጎብኚ ቁጥር ወደ 700 ሚሊዮን ያሻቅባል ተብሎ ተናግረው፤ የአፍሪካውያን አገሮች መዳረሻነት ሰፍቶ የአህጉሪቱ ተጠቃሚነት እንዲያድግ ያላቸውን ፍላጎት አመልክተዋል፡፡ በተቃራኒውም አፍሪካውያንን ጎብኚዎች ወደ አገራቸው ጋብዘዋል፡፡

ለሁለትዮሽ አጋርነቱ አስፈላጊ ጉዳዮች በማለት ያነሷቸው ነጥቦች መካከል የመጀመሪያው የጋራ ውይይትን ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ወኪል ቢሮዎችን በመክፈት የጉብኝቱን ሂደት ማሳለጥ ቅድሚያውን ትኩረት ያገኛል፡፡ በመቀጠልም የቱሪዝም ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የአፍሪካ አገሮች ጥብቅ የቪዛ ፖሊሲያቸው ላይ ማሻሻያ እንዲያደርጉ ያላቸውን ፍላጎት ጠቁመው፤ በተለይም ለቪዛ የሚከፈል ገንዘብ መቀነስ እንደሚኖርበት ነው ያነሱት፡፡

‹‹አፍሪካውን ያሏቸውን የቱሪስት መዳረሻዎች ለቻይናውያን ይበልጥ ማስተዋወቅ ይጠይቃቸዋል›› የሚሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ በተለይም በቻይና በስፋት የሚዘጋጁ የቱሪዝም አውደ ርዕዮች ላይ ቢሳተፉ አትራፊ ይሆናሉ፡፡ በሌላ በኩል ያነሱት ነጥብ በተለይ ለኢትዮጵያ የተሻለ ነጥብ የሚያስገኝ ይመስላል፡፡ ይኸውም ቻይና እና አፍሪካ ካላቸው ርቀት አንፃር የጎብኚዎችን ጉዞ ለማቀላጠፍ የሚያስችል የቀጥታ በረራ መጀመር ነው፡፡ በዘርፉ የካበተ ልምድ ያለውና በአህጉሩ መሪ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዚህ አገልግሎቱ እንደማይታማ ግልፅ ነው፡፡

ከፍተኛ ቁጥር ካለው የቻይናውያን የጉብኝት ጥቅም ተቋዳሽ ለመሆን አፍሪካውያን ብዙ የቤት ስራ እንዳለባቸው የሚናገሩት ደግሞ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያም ናቸው፡፡ በቅድሚያ አፍሪካን በተመለከተ በቻይናውያን ዘንድ ያለውን የመረጃ እጥረት በመፍታት በኩል ብዙ መስራት ይጠይቃል፡፡ ‹‹ቻይናውያን ጎብኚዎቻችን ብቻ ሳይሆኑ የልማት አጋሮቻችንም ናቸው›› በማለት የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ ከጉብኝት በሻገር በሚጎበኙ አካባቢዎችም የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ተሳትፏቸው የላቀ መሆኑን ያነሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ በኩልም ይሄን ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ የማስቀጠል ፅኑ ፍላጎት መኖሩን ለቻይናውያን ገልጸውላቸዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ዋና ፀሐፊ ዶክተር ታሌብ ሪፋይ፤ ስለቻይና አፍሪካ አጋርነት ማውራት ከምንም በላይ የወቅቱ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ሁለቱም ወገኖች በፈጣን የምጣኔ ሀብት እመርታ ውስጥ መገኘታቸው ነው፡፡ ይሁንና በቱሪዝም መስክ ተነጥሎ ሲነፃፀሩ በተለያየ ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ቻይናውያን ለዓለም ከሚያበረክቱት አስተዋፅኦ አፍሪካ የምትቋደሰው ከአምስት በመቶ የማይበልጠውን ነው፡፡ በመሆኑም ይሄን ታሪክ በተሻለ መልኩ ለመቀልበስ የሚስችለው መልካም አጋጣሚ ከፊት ነው፡፡

በአጠቃላይ አፍሪካ ተነግረው የማያልቁ የታሪክ መገለጫዎች ቢኖሯትም በውስጧ ባጣችው ሰላም የበይ ተመልካች ለመሆን ተገዳ ቆይታለች፡፡ አሁን ይሄ ጊዜ ማብቃት የሚገባው ቻይናውን ጎብኚዎችን ለመማረክ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ገፅታዋን ለመቀየርም ጭምር ይሆናል፡፡ አህጉሪቱ በአብዛኛው አካባቢዎች አንፃራዊ ሰላም ቢኖራትም ዘላቂነትን በማረጋገጥ በኩል ብዙ መስራት ይጠይቃታል፡፡ ይሄ መሆን ሲችል አፍሪካን ከቻይና የሚያስተሳስረው አዲሱ ሀዲድ ቱሪዝም መሆኑ እርግጥ ይሆናል፡፡

ብሩክ በርሄ

– See more at: http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/business-market/item/12380-2017-04-27-18-12-51#sthash.RjDKQVVG.dpuf