NEWS

ትግራይ ክልል ምክር ቤት ከ978 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት አፀደቀ

By Admin

April 11, 2017

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ሰባተኛ መደበኛ ጉባኤው ከ978 ሚሊየን ብር በላይ ተጨማሪ በጀት እና የዳኞች ሹመትን አፅድቋል።

በጀቱ የተገኘው ከፌዴራል መንግስት ለመንግስት ሰራተኞች የደመወዝ ስኬል ማስተካከያ ከተፈቀደና በክልሉ ከተሰበሰበ ገቢ መሆኑ ተነግሯል።

ዛሬ ከፀደቀው በጀት ውስጥ ከ146 ሚሊየን ብር በላይ ለመደበኛ እና 78 ሚሊየን ብር ለካፒታል በጀት የተመደበ ሲሆን፥ 200 ሚሊየን ብሩ ደግሞ ለመጠባበቂያ የተያዘ በጀት መሆኑ ነው የተጠቀሰው።

ከተጨማሪ በጀቱ ውስጥ ከ549 ሚሊየን ብር በላይ በገጠር ወረዳዎች እና ከተሞች ለሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ስኬል ማስተካከያ እና ከዚህ ቀደም ለመምህራን የደሞዝ ማሻሻያ ወጪ የተደረገውን ብድር የሚተካ ነው።

ምክር ቤቱ በተለያዩ የወረዳ ፍርድ ቤቶች ተመድበው የሚሰሩ የ42 ዳኞችን ሹመትንም አፅድቋል።