Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ነውጥና ሁከት ናፋቂዎችን የገታ አዋጅ

0 1,023

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ነውጥና ሁከት ናፋቂዎችን የገታ አዋጅ

  ታዬ ከበደ

መንግስት አውጆት በህዝቡ ባለቤትነት እውን እየሆነ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በርካታ ማሻሻያዎች ተደርገውለታል። እነዚህ ማሻሻያዎች የሚያመለክቱት ነገር በሀገራችን ያለው ሰላም ወደ ቦታው እየተመለሰ መሆኑን ነው። ሆኖም አንዳንድ ፅንፈኞች አዋጁ የዜጎችን መብቶች እንደተጣሰ አድርገው በማውራት ላይ ናቸው። ሆኖም እንኳንስ አሁን በርካታ የአዋጁ አንቀጾች ተነስተው ይቅርና በመጀመሪያም ቢሆን አዋጁ በዜጎች የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ ጫና አዕፈጠረም። እርግጥ እነዚህ ነውጥና ሁከት ናፋቂዎች ይህን የሚያስወሩት የአዋጁ መኖር ለእኩ ተግባራቸው ምቹ ስላለሆነ መሆኑ ግልፅ ነው።  

አዋጁ እነዚህ ሃይሎች የሚፈልጉትን ነገር እንዳያሳኩ ያደረጋቸው ነው። በመሆኑም ነውጥና ሁከት ናፋቂዎቹ አዋጁን በማጣጣል ስራ ላይ ቢጠመዱ የሚገርም አይሆንም። እንደሚታወቀው ሀገራችን ውስጥ ሰላም ሰፍኖ ህዝቡ ከሰላሙ ተጠቃሚ በመሆን ወደ ጀመረው የልማት ተግባራት ላይ እንዳያተኩር የሚሹ የነውጥና የሁከት ሃይሎች፤ “አዋጁ መብቶችን የጣሰ ነው” የሚል ውዥንብር በመንዛት ላይ ይገኛሉ።

በፅንፈኞቹ የሚሰነዘረው አሉባልታ ከአዋጁ መንፈስ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል—የአዋጁ ዓላማ የሰላሙ ባለቤት ለሆነው ህዝብ ተጨማሪ ጉልበት ለመስጠት እንጂ፣ እነዚህ አካላት እንደሚሉት መብቶችን የጣሰ  አይደለም። እርግጥ የፅንፈኖቹ ፍላጎት ለህዝብ ከማሰብ የመነጨ አለመሆኑ ግልጽ ነው። እንዲያውም ከመንግስትና ከህዝቡ በላይ ለዚህች ሀገር አሳቢ ሆነው በመቅረብ በተዘዋዋሪ አዋጁን ለማጥላላት የሚሰነዝሩት አባባል መሆኑ ከማንም የሚሰወር አይመስለኝም።

ያም ሆኖ መሬት ላይ ያለው ዕውነታ እነርሱ ከሚሉት ጋር የሚጣረስ ነው። ይጋጫል። ይኸውም የአዋጁ ግብና ዓላማ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተስተዋለውን የፀጥታ መደፍረስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር ለማዋል ብሎም የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ ወደ ነበረበት ቦታ ለመመለስ ስለሆነ ነው። በተለይም አዋጁ በየቦታው ለታየው ሁከት፣ ረብሻና ስርዓት አልበኝነት ዋነኛ ምክንያቶችን በመግታት ለፅንፈኞች የማይመች ምህዳርን መፍጠር ችሏል።

የሀገራችን ሰላም ላለፉት 26 ዓመታት በጥሩ መሰረት ላይ የተገነባ በመሆኑ የነውጥና የሁከት ሃይሎቹ እንደሚመኙት እንደ ደንቡሽት ቤት በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሚፈራርስ አይደለም። ምንም እንኳን በየትኛውም ማህበረሰብ ውሰጥ ሰላም ያለው እሴታዊ ዋጋ የሚታወቅ ቢሆንም፤ የተረጋጋና አስተማማኝ ሰላም ያላቸው ሀገራት ሰላማቸው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሲደፈርስ ብሎም በትርምስና ሁከት ውስጥ ሲቆዩ የተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ጥቂት አይደሉም።

ከእኛ ሀገር አንፃር ግን ሰላማችን ሲጀመር የተገነባው በህዝቦች ፅኑ ፍላጎት በመሆኑ በቀላሉ ሊናጋ የሚችል አይመስለኝም። ሆኖም ልክ እንደ አለፈው አንድ ዓመት ሰላማችን የመሸራረፍ ሁኔታ ሲያጋጥመው የሰላሙ ባለቤቶች የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በመሆናቸው በቀላሉ ከህዝቡ ጋር በመሆን የተለያዩ ድንጋጌዎችን በማውጣት መጠገን ይቻላል፤ እየተቻለም ነው።

እርግጥ ሁከትና ብጥብጥ በነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው የንብረት ውድመት ምንም ዓይነት አሉታዊ ተፅዕኖ አልፈጠረም ሊባል አይቻልም። ይሁንና ችግሩ ከመንግስትና ከህዝብ አቅም በላይ የሚሆን አይደለም። በቀላሉ በመንግስትና በህዝቡ ጥረት ሊስተካከል የሚችልና በመስተካካል ላይ ያለ ጉዳይ ነው። የሰላም ማጣት ትንሽ ባይኖረውም፤ ከጠቅላላው የሀገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ፣ ችግሩ ያስከተለው የልማት መስተጓጎል እዚህ ግባ ሊባል የሚችል አይመስለኝም።

በመሆኑም በተለያዩ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረው የሰላም እጦት በመንግስትና በህዝብ ቅንጅታዊ ስራ በቀላሉ በቁጥጥር ስር እየዋለ በመሆኑ እንዲሁም ዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋማት የመሳሰሉ ድርጅቶች ሀገራችን የምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የኢኮኖሚ ባለቤት እንደምትሆን መተንበያቸው ምስጢርም በሀገራችን የተፈጠረው ችግር በመንግስትና ህህዝቡ ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደሚውል ስለሚያውቁ ነው። ይህ ደግሞ በምንም ዓይነት ምክንያት ሰብዓዊ መብትን የሚጥስ አይደለም። እናም የነውጥና የሁከት ናፋቂዎቹ አሉባልታ ሚዛን የማይደፋ ነው።

እርግጥ ሰላም ከሌለ የህግ የበላይነት ብሎ ነገር የለም። መብት አይከበርም። መብት ሰጪና ነሺዎች ጥቂቶች ይሆናሉ። ጉልበት ያለው የህግ አስፈፃሚ ይሆናል። በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይም በህግና በስርዓት ሳይሆን በጉልበተኞች የሚወሰን ይሆናል። ጉልበተኞቹ ከሚፈልጉት ጊዜና ዕውቅና ውጭ ማንም ሰው መነቃነቅ አይችልም። ህግ የበላይነቱን ስለሚነጠቅም በእነዚህ ሃይሎች እጅ ይወድቅና ሁሉም ነገር ምስቅልቅሉ ይወጣል።

ይህን የሰላም እጦት ፈተና የትኛውም ሀገር ህዝብ ይገነዘበዋል። ያለ ሰላም አንዳችም ነገር መፈፀም እንደማይቻል የሁሉም ሀገር ህዝብ በሚገባ ያውቃል። አንድ ሀገር ሰላምን ለማስፈን ሰላምን ሊያረጋግጡ የሚችሉ አዋጆችን ሊያወጣ ይችላል። አዋጁ ግን በህዝቡ ይሁንታ ሊደገፍ ካልቻለ ተፈፃሚነቱ አጠራጣሪ ይሆናል።

እርግጥም ህዝቡ ያልደገፈው አዋጅ የታለመለትን ግብ ሊመታ አይችልም። ይህም የሰላም ዋነኛው ምሶሶና ማገር የዚያች ሀገር ህዝብ እንጂ አዋጅ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳይ ነው። እናም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በህዝቦች ባለቤትነት የሚንቀሳቀስ በመሆኑ መልሶ ህዝቡን እንደማይጎዳ ፅንፈኞቹ ሊያውቁት ይገባል።

ታዲያ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ የህዝቡን ስሜት በማጤንና ተገቢውን ጥናት በማካሄድ አዋጁ ለአራት ወራት እንዲቀጥል መደረጉ ተገቢ ነው። ከዚህ ውጪ ግን ሁከትና ብጥብጥ ናፋቂዎቹ በሐሰት መብትን ይጋፋል ስላሉ የሚቀር አይደለም። ፅንፈኞችና የፀረ-ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪዎች ዛሬም እንደ ትናንቱ ቀዳዳ እናገኛለን በሚል ቀቢፀ-ተስፋ የአዋጁን መነሳት ይፈልጉት ይሆናል። ግን ይህ ቀዳዳ በህዝቡ ፍላጎት ለቀጣዩቹ አራት ወራት ተዘግቷል። ምንም መፈናፈኛ ሊያገኙ አይችሉም።

ያም ቢሆን ፅንፈኞቹ ያሻቸውን ያህል የአሉባልታ እምቢልታቸውን ቢጎስሙም፤ ገና ከመጀመሪያው አዋጁ ሲወጣ የህዝቡንና የሀገራችንን ሰላም ለማስጠበቅ በመሆኑ አሁንም የቀጠለው ይህንኑ ሃቅ ተመርኩዞ ነው። እናም አዋጁ የህዝቡን መብት የሚያስጠብቅ እንጂ የሚጎዳ አለመሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።

ፅንፈኞቹና የፀረ- ኢትዮጵያ ሃይሎች ተላላኪዎችም ቢሆኑ ይህን ሃቅ በማወቅ፤ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ቦይ ውሃ እነርሱ በሚፈልጉት መንገድ የሚነጉድ ህዝብ ሊኖር እንደሌለ ከጥላቻ ቆፈናቸው ወጥተው መገንዘብ ይኖርባቸዋል።

እናም የሀገራችን ህዝብ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያገኘው ውጤት የመብት ጥሰት ሳይሆን ሰላምና መረጋጋትን መሆኑ እነዚህ ሃይሎች ሊያውቁት ይገባል። እነርሱን የሚሰማበት ምንም ዓይነት ጆሮ ስለለሌውም ሃሳባቸው የማይሳካ መሆኑን ሊያውቁት የግድ ይላል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy