Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አመራሩ የገቢ ግብር አወሳሰን ጥናቱ በትክክለኛ መረጃ ላይ እንዲመሰረት ማድረግ አለበት—የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር

0 806

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አመራሩ በክልሉ የሚካሔደው የግብር ከፋዮች የደረጃ ልየታ ጥናት በትክክለኛ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ እንዲሰራ ማድረግ እንዳለበት የአማራ ክልል ርዕሰ-መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አስገነዘቡ።

በቅርቡ የሚጀመረውን የግብር ከፋዮች የደረጃ ልየታ ጥናት አስመልክቶ ከምዕራብ አማራ ለተወጣጡ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች የምክክር መድረክ በባህርዳር ከተማ ተካሂዷል።

ርዕሰ-መስተዳደሩ በምክክር መድረኩ ላይ እንዳሉት ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ ተናቦ መስራትን ይጠይቃል።

“በክልል ደረጃ ከሚያዚያ 23 ጀምሮ ለአንድ ወር የሚካሔደውን የቁርጥ ግብር ጥናትና የግብር ከፋዮች የደረጃ ልየታ ትክክለኛና ሚዛናዊ መረጃ ላይ ተመስርቶ ለማካሄድ በየደረጃው የሚገኝ አመራር በቁርጠኝነት መስራት አለበት “ብለዋል።

“ጥናቱ በንግዱ ማህበረሰብ ዘንድ ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዲሰፍንና የክልሉን ልማት ለማፋጠን የሚያስችል መሆኑን ተገንዝቦ ወደ ስራ መግባት” እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት።

የቀን ገቢ ጥናቱ ሲካሄድም ሌላ የመልካም አስተዳደር ችግር ሊፈጥር በማያስችል መልኩ ፖለቲካዊ ትርጉም ሰጥቶ በዝርዝርና በጥንቃቄ ማጥናት እንሚያስፈልግ ተናግረዋል።

“መንግስት ለልማቱ ማግኘት የሚገባውን ያህል ገቢ በአግባቡ እንዲያገኝና የንግዱ ማህበረሰብ የሚያነሳውን የፍትሃዊነት ችግር ጥናቱ በዘላቂነት መመለስ ያስችላል” ብለዋል።

የንግዱ ማህበረሰብም በሚያገኘው ገቢ ልክ ግብር በመክፈል ለክልሉ ልማት መፋጠን ትክክለኛ መረጃ ለአጥኚዎቹ በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳያሬክተር አቶ መሀመድ አብዱ በበኩላቸው እንደገለጹት በየአካባቢው የሚነሱ የፍትሃዊነት፤ የአሳታፊነትና የግልፀኝነት ችግሮችን ሊፈታ በሚችል መልኩ ጥናቱን በውጤታማነት ለማጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል።

በጥናቱ የሚሳተፉ ከሶስት ሺህ 600 በላይ የቀን ገቢ ገማች ኮሚቴ አባላትም የህጋዊ ነጋዴዎችን መረጃ በአግባቡ ማጥናት የሚያስችላቸውን ስልጠና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ50 ሺህ የሚበልጡ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ወደ ንግድ መረቡ እንዲገቡ የማድረግ ስራም በትኩረት እንደሚከናወን አስረድተዋል።

ከሰሜን ጎንደር ዞን የመጡት የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ዘውዱ ማለደ “በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ ፍትሃዊነትን ያረጋገጠ የገቢ ግብርን ለመሰብሰብ የተዋጣለት ጥናት እንዲካሄድ ተገቢ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይጠበቅብናል”ብለዋል።

እሳቸውም በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ የገቢ ግብር መሰብሰብ የሚያስችል ጥናት ለማድረግ የሚረዳ መረጃ ለመሰብሰብ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ከ260 ሺህ 500 በላይ ህጋዊ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ከባለስልጣን መስሪያቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ትላንት በተካሔደው የምክክር መድረክ ላይም በምዕራብ አማራ ከሚገኙ ዞኖች፤ የከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች የተውጣጡ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy