Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

አይን አውጣው ሙስና !!

0 314

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

አይን አውጣው ሙስና !! / ይነበብ ይግለጡ/

በሙስናና በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ በብሔራዊ ደረጃ የተጀመረው ትግል ገና ያልተነካና ብዙ ያልተሄደበት ጅምር እንቅስቃሴ ነው፡፡አንድ ሰሞን በሚዲያ ደረጃ ሞቅ ብሎ ይቀርብ የነበረው የሙስናና የሙሰኞች የመልካም አስተዳደር ችግር ጉዳይ አሁን አሁን ደግሞ እየደበዘዘ ከአጀንዳነትም እየወጣ ያለ ይመስላል፡፡ዛሬም ዋናው የሀገሪቱ ችግር መነሻና መወለጃ መፈታትና መቀረፍ ያለበት ችግር ከዚሁ ጋር የተሳሰረና የተቆራኘ ነው፡፡

በዚህ ረገድ ሚዲያው መሄድ ያለበትን ርቀትና መስራት ያለበትን ስራ አልሰራም፡፡አንድ ሰሞን የደመቀ ከበሮ ሲመታ ዙሪያ ገባውን ሲያምሰው ይከርማል፡፡ትንሽ ቆይቶ ተው የተባለ ይመስል ጭርሱንም ርእሱን ማንሳት ተስኖት የጎድን ሲሄድ ይታያል፡፡እንዲህ አይነቱ ሁኔታ በሕዝቡ ውስጥ ትኩረት የማስቀየር መንገድ ተደርጎ እየተወሰደ ነው ያለው፡፡ችግሩ ውስብስብና አስቸጋሪ የተቆላለፈም ነው፡፡ጊዜን ይጠይቃል፡፡ቀድሞውንም ባልዘፈንሽ  ከዘፈንሽም ባላፈርሽ  የሚለው አባባል አይነት መሆኑ ነው፡፡አለመጀመር ከጀመሩም በተገቢው መንገድ ዳር ማድረስ ይገባል ነው የሚለው የሕዝቡ አስተያየት፡፡

በሀገሪትዋ ላለው ችግር ሁሉ መነሻው አይን ያወጣው ሙስናና ምዝበራ ነው፡፡አንድ ሰሞን መላው የሀገሪቱ ባለስልጣኖች ትልቁ ትግላችን ከሙስናና ከመልካም አስተዳደር ችግር ጋር ነው ትግላችን የሞት የሽረት ነው ሲሉ ቀን ከሌሊት ይደመጡ የነበሩበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ዛሬ ወራት ባልሞላ ግዜ ስለጉዳዩ የሚነገር ነገር የለም፡፡ወሬውም ደብዛውም እልም ጭልም እያሉ ነው፡፡እንደ ሀገር ያስፈራል፡፡

ሕዝቡን ያስመረረው ለአመጽ ያስነሳው አይን ያወጣው ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግር በወራት ግዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተፈታ ተወገደ ማለት አይቻልም፡፡ምንስ ጉልህ የሚታይና የሚጨበጥ እርምጃ ተወሰደ የሚለው ጥያቄ የሕዝብ የመወያያ ርእስ ሁኖ እንደቀጠለ ነው፡፡አንዳንዴ የተወሰነ እፎይታ ሲገኝ ኢሕአዴግና የሚመራው መንግስትም የመዘናጋትና ሁሉንም ችግር ተወጥተነዋል የሚል ድምዳሜ ላይ የሚደርሱ ይመስላሉ፡፡ ውሀ ሲወስድ አሳስቆ እንዲሉ፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ጅምር እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡በዋነኛነት አልተገፋበትም፡፡እራስን ማታለልም ይመስላል፡፡ በመሰረታዊነት አልተፈታም፡፡ችግሩ የሚፈታው በተግባር ሕግን መሰረት ባደረገ ሁኔታ እንጂ በውይይት በኮንፈረንስ  አይደለም፡፡ከሕዝብ ጋር በሚደረገው ውይይት ሀሳቦችን ለማግኘት የችግሩን አቅጣጫ ለመለየት ያግዛል፡፡ወሳኝ እርምጃ በመውሰድ ማስተካከል ያለበት በትረ መንግስቱን የጨበጠው መንግስት ነው፡፡ ሕዝብ የሚታይና የሚጨበጥ እርምጃ ማየት ይፈልጋል፡፡

አዎን በአነስተኛ ደረጃ ሊቆጠሩ የሚችሉ የጸረ ሙስና እንቅስቃሴዎችና እርምጃዎች መኖራቸውን መካድ አይቻልም፡፡እነዚህ የተገኙት በተሀድሶው ለውጥ ውስጥ ነው፡፡ ሊበረታቱም ይገባል፡፡ተሀድሶው ራሱ ጅምር እንጂ መቋጫ አይደለም፡፡በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት መረብና ሕገወጥ ጥቅም ፍለጋ ውስጥ ተነክረው በተገኙ አባላቶቹ ላይ ኢሕአዴግ የተለያየ እርምጃ መውሰዱን ይፋ አድርጎአል፡፡ የተዘረፈው የመንግስትና የሕዝብ ሀብት ስለመመለሱ መናገር መግለጽ አለበት፡፡ግልጽነትና ተጠያቂነት ከዚህ ይጀምራል፡፡

የሀገሪትዋ ዋነኛ ባለቤት ሕዝብ መሆኑን  የሚያምነው ኢሕአዴግ አሁንም ቢሆን የችግሮቹን መነሻ ትንተና በብቃት መፈተሸና መገምገም አለበት፡፡ ሌቦችን ሌቦች ናችሁ ብሎ ለይቶ ማወጣትና የሚገባቸውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ወሳኙ ጉዳይ ነው፡፡ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ሌሎችም ችግሮች በሂደት የሚፈቱ መሆናቸው ቢታወቅም መሰረታዊ የመንግስትን እርምጃዎች ይጠይቃሉ፡፡ችግሩ በአንድ ግዜ ተፈቶአል የሚል ካለ ጤነኛነቱ አጠራጣሪ ነው የሚሆነው፡፡ ጅምር ሂደቶች አሉ፡፡ትግሉ ገና አልተነካም፡፡ ችግሩም በይፈታል ተስፋ እንጂ ገና አልተፈታም፡፡ዛሬም የውስጥ እግር ቁስል ሁኖ በሕዝቡ ውስጥ ቀጥሎአል፡፡ኢሕአዴግ ያገኘውን ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም መሮጥ ያለበት ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው፡፡

የሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በፍጹም እንዲነሳ የማይፈልጉ ቁስላቸውን የሚነካቸው የሚያሳክካቸው እንዲሁ ተሸፋፍነው መዝለቅ የሚፈልጉ እንዳሉም ሕዝቡ ያውቃል፡፡እንዲህ አይነቱ ሁኔታ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅምና ሰላም አይበጅም፡፡

በሀገሪቱ ለተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ችግር ዋናው መነሻና መንስኤ ሙስና ኪራይ ሰብሳቢነት የመልካም አስተዳደርና የፍትህ መዛባት ችግር ነው፡፡እዚህ ላይ በአቀጣጣይነት የተሰለፉ የተለያዩ ኃይሎች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ቀዳዳውን ስለሚፈልጉት ይጠቀሙበታል፡፡የሚገርመው ሳይጠቀሙበት ቢቀሩ ነው፡፡ብሶቱን በማቀጣጠል ወደ ራሳቸው አጀንዳ ሊወስዱት ስለሚፈልጉ የሚችሉትን ሁሉ ያደርጋሉ፡፡የነበረም የሚጠበቅም ነው፡፡

የቅራኔ አያያዝና አፈታት የደረጃ ምደባ ሕጉን በማወቅም ባላማወቅም መተላለፍ አዛብቶ የመተርጎም ነገር ያለ ይመስላል፡፡ዋናው የችግሩ መነሻ ሰንኮፉ ያለው በራሱ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ሁነው ስርአቱን ሲቦረቡሩትና ሕዝባዊ መሰረት ሲያሳጡት ከሕዝብ ጋር ሲያላትሙት የነበሩት ሕዝብን መንግስትን በመዝረፍ ስራ ተሰማርተው የነበሩና ያሉ ኃይሎች ናቸው፡፡ለዚህ ነው ኢሕአዴግ በጣም ወደ ውስጥ ወደራሱ በጥልቀት መፈተሽ መመልከት የነበረበት፡፡አሁንም ያለበት፡፡

የሕዝቡ መብቴ ይከበርልኝ ጥያቄ መነሻው ችግር በገዢው ፓርቲ ወስጥ መሽገው ሲጫወቱ የነበሩ ኃይሎች ናቸው፡፡ከውጭ ሁኖ ችግሩ እንዲባባስ እሳት የማንደድ ስራ ይሰራ የነበረው ኃይል ችቦውን የተቀበለው ዋናውን ስራ ከሰሩት አንዳንድ የኢህአዴግ ሰዎች ናቸው፡፡ስለዚህ በቅራኔ አያያዝና አፈታት ሕጉ መሰረት በመጀመሪያ ደረጃ መቀረፍ መፈታት መወገድ ያለበት ችግር የውስጡን ሙሰኛና ኪራይ ሰብሳቢ የማጥራትና ተጠያቂ የማድረግ ስራ ነው፡፡ በተወሰነ ደረጃ ተሰርቶአል፡፡ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡

ሕዝብ መብቴ ይከበርልኝ በሚል ያነሳውንና መንግስት እራሱ ያመነውን መሰረታዊ ችግር ሌላ ባለቤት ፈልጎ መስጠቱ አዋጪ አይደለም፡፡ትልቅ ግድፈት ሲሆን ሕዝቡ የሚያውቀውን መንግስት የተቀበለውን ትክክለኛ ጭብጥ ማፋለስም ነው የሚሆነው፡፡ መሰረታዊ መፍትሄም አያመጣም፡፡ችግሩ ለዘለቄታው እንዲፈታም አያደርግም፡፡ብዙ መልካምና ሊበረታቱ የሚገባቸው የተሀድሶው ጅምር ስራዎች አሉ፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች መስሪያቤቶች ድርጅቶች ሙሰኞችን ኪራይ ሰብሳቢዎችን በሕግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ውጤቱም ለሕዝብ ይፋ የሚሆንበትም የማይሆንበትም ጊዜ አለ፡፡መሆን ግን አለበት፡፡ሙስናን በተመለከተ አሁን አሁን ጉዳዩ ብዙ ከሚዲያ የራቀ ቢመስልም በክልሎችም ሆነ በተለያዩ ተቋማት የማጥራት እርምጃዎች በስፋት እየተወሰዱ ነው፡፡በትግራይ ክልል በሙስና ወንጀል የተከሱ 114 ግለሰቦች ከአንድ እስከ ሀያ ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት መቀጣታቸውን የክልሉ የጸረ ሙስናና ስነ ምግባር ኮሚሽን ያስታወቀ ሲሆን ይሄም ትልቅ እርምጃ ነው፡፡

ግለሰቦቹ በፈጸሙት የሙስና ወንጀል ተመዝብሮ የነበረው ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ በፍርድ ቤት ትእዛዝ ወደ መንግስት ካዝና ተመላሽ ተደርጓል፡፡የእስር ቅጣቱ በግለሰቦቹ ላይ የተላለፈው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በመንግስትና በግል ስራ ላይ ተሰማርተው ሰጪና ተቀባይ በመሆን የከተማ መሬት ያለ አግባብ ሲዘርፉና ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸው በማስረጃ ስለተረጋገጠባቸው መሆኑም ተገልጾአል፡፡

የክልሉ የጸረ ሙስናና ስነ ምግባር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ብርሃነ ተክሉ ለመገናኛ ብዙሀን እንደገለጹት በእስራት ከተቀጡት ግለሰቦች መካከል በተለይ በቅየሳና በግንባታ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችና የመንግስት የምሕንድስና ባለሙያዎች ያልተገባ ውልና ክፍያ እንዲፈፀም ያደረጉም ይገኙበታል፡፡ተመላሽ ከተደረገው ገንዘብ በተጨማሪም በመቀሌ ከተማ በመንግስት ሀብትና መሬት አለአግባብ ተገንብተው የነበሩ ሶስት ዘመናዊ ቪላ ቤቶች ተሸጠው ለመንግስት ገቢ እንዲሆን በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል፡፡

ከዚሁ ከሙስና ጋር በተያያዘ  ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን 11 ሚሊዮን ብር ካሳ እንዲከፈል ያደረጉና የወሰዱ አስር ተከሳሽ ግለሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጥተዋል፡፡ የክስ መዝገቡም ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደሴ ምድብ ችሎት ቀርቦ ለተከሳሾች የተነበበ ሲሆን፤ ተከሳሾችም የቀረበባቸውን ክስ አላስተባበሉም፡፡ተከሳሾቹ በዳዋ ጨፋ ወረዳ ግንባታው በመካሄድ ላይ በሚገኘው የአዋሽ ወልዲያ የባቡር መስመር ግንባታ ወቅት ያለአግባብ 11 ሚሊዮን ብር ካሳ እንዲከፈል በማድረጋቸውና በመውሰዳቸው ምክንያት ነው ክሱ የተመሰረተው፡፡

ከተከሳሾቹ ውስጥ አምስቱ የካሳ ኮሚቴ ገማች ኮሚቴ አባላት ሲሆኑ፤አንዱ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የመንገድ መብት ጥበቃ ተወካይ እንዲሁም ቀሪዎቹ ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የወንጀሉ ተሳታፊዎች መሆናቸው በአቃቤ ሕግ ክስ ላይ ተብራርቷል፡፡ተከሳሾቹ በጋራ በመሆን ለ7ኛ ተከሳሽ አቶ ሰኢድ የሱፍ ምንም አይነት መሬት ሳይኖረው በባቡር ግንባታ ፕሮጀክቱ መሬቱን አጥቷል በሚል 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን እንዲከፈለው አድርገዋል፡፡ለ9ኛ ተከሳሽ አቶ አደም አርጋው ምንም አይነት መሬት ሳይኖረው መሬቱ ተወስዷል በሚል 3 ነጥብ 263 ሚሊዮን ብር መስጠታቸው ተመልክቷል፡፡ ለ10ኛ ተከሳሽ ወይዘሮ ጀማዬ ዓሊ ባለቤቷ የሆነው 9ኛ ተከሳሽ የወሰደውን ካሳ በድጋሚ እንድትወስድ መደረጉ በክሱ ላይ ተገልጿል፡፡ይሄን አይነት አይን አውጣነት ነው ሙስና ማለት፡፡ሀገርና ትውልድ ገዳይ፡፡

ይህ የአንድ ዘርፍ መገለጫ ሲሆን ሌላም በእጅጉ አስገራሚ ክስተቶች እንዳሉ ልንዘነጋው አይገባም፡፡በዚህ መልኩ ነው የመንግስትና የሕዝብ ሀብት የሚዘረፈው፡፡ለዚህም ነው መንግስት ጠንካራ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት የሚባለው፡፡

በተጨማሪም ለ8ኛ ተከሳሽ አርሶ አደር አደም ሁሴን የሸንኮራ እርሻ መሬት ሳይኖረው የአትክልት መሬት ሲሆን ግምቱ ይጨምራል በሚል ለባዶ መሬት ከ180 ሺህ 843 ብር በላይ ገምተው ሰጥተዋል የሚለውም በክሱ ላይ ሰፍሯል፡፡ተከሳሾቹ በአጠቃላይ በዚህ መልኩ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን 11 ሚሊዮን ብር ያለ አግባብ እንዲከፈል ማድረጋቸው  ነው የተገለጸው፡፡ሊሰጥ ከታሰበው ከ11 ሚሊየን ብር በላይም ሳይንቀሳቀስ በባንክ የተያዘ በመሆኑ ለመንግስት ተመላሽ እንዲሆን ትእዛዝ መተላለፉ በመገናኛ ብዙህን ተገልጾአል፡፡  

ከዚሁ ከሙስና ጋር በተያያዘም በኦሮሚያ ክልል በሙስና ድርጊት ተሳታፊ ሆነው በተገኙ አካላት ላይ ተገቢ እርምጃ እንደሚወሰድ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ገልጸዋል፡፡የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ 59 ወረዳዎችና 12 ዋና ዋና ከተሞች በሙስናና በሕብረተሰቡ ግንዛቤ ላይ ትኩረት በመስጠት ያካሄደውን ጥናት ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው ፕሬዚደንቱ ሀሳቡን የገለጹት፡፡

በክልሉም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ሙስና መልኩን እየቀየረና እየተስፋፋ መምጣቱን በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ወረዳዎች የተካሄደው ጥናት ሙስና በክልሉ ለሕብረተሰቡ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና እድገት ማነቆ መሆኑን በግልጽ ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሙስና በክልሉ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ከመሆኑ በተጨማሪ ሕዝብን ለምሬትና ለቅሬታ እየዳረገ በመምጣቱ በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍታት ጥናቱ ጠቃሚ መሆኑን  አስረድተዋል፡፡      

ፕሬዚዳንቱ የፍትሕ አካላት በሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ፍትሕ በማጓደል በሕብረተሰቡ ላይ ተደራራቢ ወንጀል እየፈጸሙ ስለመሆኑ ጥናቱ ማመላከቱን ገልጸዋል፡፡ችግሩን ለማስወገድ የጥናቱን ውጤት መሰረት በማድረግ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የኃይማኖት አባቶችና መላውን ሕብረተሰብ ያሳተፈ ሥራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡  

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚደንት አቶ ለማ በፍትህ ተቋማት፣ በገቢዎች፣ በግብርና ታክስ፣ በግዥ አስተዳደር፣ በመሬት፣ በመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማትና በሌሎች ተያያዥ ሴክተሮች ላይ ሕብረተሰቡ አገልግሎትን በገንዘብ እየገዛ ስለመሆኑ ጥናቱ ማመላከቱን ገልጸው ጥናቱ ሙስናን የማይሸከም ተተኪ ትውልድ ማፍራት እንደሚገባ የጠቆመ ጥናት ነው ብለዋል፡፡

ጥናቱ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎች፣ የችግሩን ምንጭ እንዲሁም ሙስና የሚያስከትለው ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ  ጉዳቶችን  አመላክቷል፡፡በዚህም የፍትሕ፣ የገቢዎች፣ የመሬት አስተዳደር፣ የግዥ ዘርፍ፣ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎት፣የጤና ተቋም፣ የልማት ድርጅቶችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሙስና በስፋት የሚታይባቸው ተቋማት መሆናቸው ተለይቶ ታውቆአል፡፡እነዚህም በመንግስት ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ሴክተሮች ናቸው፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy