NEWS

አገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

By Admin

April 04, 2017

ኢትዮጵያና ጋና አህጉራዊ አጀንዳና ፍላጎቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማንጸባረቅ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የስልጣን ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን በኢትዮጵያ የጋና አምባሳደር ሚስተር አልበርት ያንኬይን ትናንት በፅህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።

ዶክተር ወርቅነህ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከጋና ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ትልቅ ግምት የምትሰጠው በመሆኑ ለሁለቱ አገራት ህዝቦች የተሻለ ህይወት በጋራ ይሰራሉ።

ተሳናባቹ አምባሳደር የሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ትብብር እንዲያድግ በማድረግ በኩል ያደረጉት አስተዋጽኦም የሚደነቅ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ አጀንዳና ፍላጎቶች በአህጉሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲንጸባረቅ በማስተዋወቅና አስተዋጽኦ በማድረግ ሁለቱ አገራት የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።

አገራቱ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት አቅም ሙሉ ለሙሉ በመጠቀም ለህዝብ ትስስር ማደግ መስራት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት ዶክተር ወርቅነህ።

ተሳናባቹ የጋና አምባሳደር ሚስተር አልበርት ያንኬይ በበኩላቸው በቆይታቸው የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት መሰረት ያደረገው የፓን አፍሪካኒዝምን ፅንሰ ሀሳብ መሆኑን ገልጸው አገራቱ የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች ወደ ተግባር በመቀየር ለሁለቱ አገራት ህዝቦች የጋራ ጥቅም መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያና ጋና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1959 ነው።

አገራቱ ከአፍሪካ ሕብረት ምስረታ ጀምሮ በሰላም ማስከበርና በሌሎች የአፍሪካ ጉዳዮች በጋራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያና ጋና በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ሌሎች መስኮች በትብብር ለመስራት የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ መፈራረማቸው ይታወቃል።

ጋና እንደ አወሮፓውያን አቆጣጠር ከ1992 ጀምሮ ወደ ብዝሃ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ከተሸጋገረች በኋላ በምዕራብ አፍሪካ የተረጋጋች አገር መሆኗ ይነገርላታል።