Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢሕአዴግ ያንዣበቡበትን ብዥታዎች አጥርቶ ወደ ጤንነት መመለሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ

0 358

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

  • በብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮች መካከል ጥርጣሬ ተከስቶ እንደነበር ይፋ አድርገዋል
  • መጠራጠሩ ቀጥሏል የሚል መረጃ ካለ በቀጣይ እንደሚገመገም ጠቁመዋል

ገዥው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) አንዣበውበት የነበሩ ውስጣዊ መደናገሮችን በማጥራት ወደ ጤናማነት መመለሱን፣ የግንባሩ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ፣ ኢሕአዴግን በፈጠሩት ብሔራዊ ድርጅቶች አመራሮች መካከል በዓይነቱ ሰፋ ያለ ‹‹መጠራጠር›› ተከስቶ እንደነበር በግልጽ ይፋ አድርገዋል፡፡ በግንባሩ ውስጥ የአማራ ብሔር የወከለው ፓርቲ ብአዴን ከወር በፊት ባሳተመው መጽሔቱ፣ እህት ድርጅቱ የሆነው የትግራይ ብሔርን በሚወክለው ሕወሓት ላይ መጠራጠር ውስጥ ገብቶ እንደበር ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ይህንን መሠረት አድርጎ ኢሕአዴግ አሁን ጤነኛ እንደሆነ ጋዜጠኞች ጥያቄያቸውን ለአቶ ኃይለ ማርያም አቅርበዋል፡፡ ‹‹የነበሩ ብዥታዎች በአብዛኛው የተቀረፉ በመሆናቸው አሁን ድርጅቱ (ኢሕአዴግ) እጅግ ጤናማ ነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ብአዴን በሕወሓት ላይ ተፈጥሮበት ስለበረው መጠራጠር በልሳን መጽሔቱ መግለጹ ተገቢ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ብዥታውና ጥርጣሬው ተከስቶ የነበረው ግን በሁለቱ ድርጅቶች አመራሮች መካከል ብቻ እንዳልነበር በዝርዝር አመላክተዋል፡፡

‹‹በብሔራዊ ድርጅቶቹ አመራሮች መካከል ተፈጥሮ የነበረው መጠራጠር ደረጃው የተለያየ ቢሆንም በኦሕዴድና በሕወሓት፣ በኦሕዴድና በብአዴን፣ እንዲሁም በደኢሕዴና በብአዴን መካከልም የተፈጠረ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በብሔራዊ ድርጅቶቹ መካከል ተከስቶ የነበረው መጠራጠርና ብዥታ አንዳንዱ በመለስተኛ እውነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስረዱት አቶ ኃይለ ማርያም፣ አንዳንዶቹ መነሻቸው ጥርጣሬ አንዳንዶቹ ደግሞ ምንም ‹‹እውነት ላይ ያልተመሠረቱ›› እንደነበሩ አስረድተዋል፡፡

በአመራሮች መካከል መጠራጠሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ፣ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ከዚህ ቀደምም በትጥቅ ትግሉ ወቅት ጭምር ፓርቲውን ገጥመውት ያውቅ እንደበር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን መሰል ችግሮች ሲከሰቱ የሚፈቱበት ግልጽ የአሠራር ባህልን የታጠቀ በመሆኑ በቀላሉ እንደሚፈቱ ገልጸዋል፡፡

ልክ ከዚህ በፊት በተፈቱበት መንገድ ግልጽ ውይይት በማድረግ የተፈታና መተማመንን የተፈጠረ በመሆኑ፣ በአስተማማኝ ሁኔታ ፓርቲው ወደ ጥንካሬው መመለሱን ጠቁመዋል፡፡

በቅርቡ በኢሕአዴግ ምክር ቤት በተደረገ ግምገማ በድርጅቶች አመራሮች መካከል ያለው ግንኙነት በእጅጉ መሻሻሉን ማረጋገጥ እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አሁንም መጠራጠሩ ቀጥሏል የሚል ካለና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ እኛም በቀጣይነት እንገመግመዋለን፡፡ በእኛ በኩል ግን ክፍተቶችን በመዝጋት አብሮ መሥራት ይቻላል የሚል መተማመን ላይ በመድረስ ከመቼውም በላይ አንድነታችን ተጠናክሮ እንዲወጣ አድርገናል፤›› ብለዋል፡፡

የመቀልበስ አደጋ

በቅርቡ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋት መሠረታዊ ምክንያቶች የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማዋል፣ ሥራ አጥነት፣ ለሕዝብ ጥያቄዎች በአፋጣኝ መፍትሔ አለመስጠት የመሳሰሉት መሆናቸውን ኢሕአዴግ በማዕከላዊ ኮሚቴው እንዲሁም በምክር ቤቱ መለየቱ ይታወሳል፡፡ በመፍትሔነትም ‹‹በጥልቀት መታደስን›› በማስቀመጥ በየደረጃው እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው የሰሞኑ ቆይታም በጥልቀት የመታደሱ እንቅስቃሴ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው ሥጋት በጥልቅ ተሃድሶ ንቅናቄው መፈታቱን መንግሥት እየገለጸ መሆኑን መሠረት በማድረግ፣ ሥጋቶቹ ተመልሰው ሊያገረሹ ወይም የተገኘው መረጋጋት እንደማይቀለበስ እርግጠኛ መሆን ይቻል እንደሆነ ከጋዜጠኞች ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡

‹‹በአገሪቱ ተከስተው የነበሩ ሥጋቶች በጥልቅ ተሃድሶው መቀልበሳቸው እርግጥ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ማንኛውም የፖለቲካ ሒደት አስተማማኝ መሆኑ የሚለየው በሕዝቡ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በመረዳት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹መቀልበሳቸውን የምናረጋግጠው ከሕዝባችን አመለካከት እንጂ ረብሻውን ከሚፈጥሩ ጥቂት ኃይሎች ተነስተን አይደለም፡፡ በዚህ ግምገማችን እናምናለን፣ ምክንያቱም ሕዝባዊ መንግሥት እንደ መሆናችን መጠን መነሻችንም መድረሻችንም ሕዝቡ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አሁን የተገኘው ሰላም የማይቀለበስ ደረጃ ላይ ቢሆንም አጠናክሮ ወደፊት መቀጠል እንደሚያስፈልግ ፓርቲው መገምገሙን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ምክንያቱም እኛ ካበላሸነው ሊበላሽ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

አስፈጻሚው አሁንም ችግሮች አሉበት መባሉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በተሃድሶ እንቅስቃሴው ከፍተኛ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑንና እንዲሁም በአገሪቱ ተፈጥረው የነበሩ ሥጋቶች በተሃድሶው መቀልበሳቸውን ቢገልጹም፣ በመንግሥት የምርምር ተቋም የቀረበው ሪፖርት ግን ይህንን አያረጋግጥም፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ እንዲሆን ተደርጎ ከሦስት ዓመት በፊት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል በመጋቢት ወር ይፋ ያደረገው የጥናት ውጤት ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡

‹‹መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር የሕዝብ ተሳትፎ ማነቆዎች፣ መንስዔዎችና የመፍትሔ ሐሳቦች›› በሚል ርዕስ ለአንድ ዓመት ሲያጠና የቆየውን ሪፖርት አቅርቧል፡፡

በዚህ ጥናት ውስጥ ግኝት ሆነው የቀረቡት በተፅዕኖ ሥር የመውደቅ ጉዳይ ነው፡፡ በተፅዕኖ ሥር ወደቁ ከሚላቸው መካከል ደግሞ መንግሥትን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለባቸው ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ ‹‹ዜጎች በግላቸውም ሆነ በማኅበር ተደራጅተው ወይም ባላቸው ኃላፊነት በሚመለከታቸው ጉዳይ ሲሳተፉና ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ ከአስፈጻሚው አካል በሚደርስባቸው ዛቻ፣ ማስፈራሪያ፣ ጥቃት፣ አድሎዓዊነት፣ ወዘተ ከፍተኛ እንደሆነ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

ሦስቱ የመንግሥት አካላት ተናበው አለመሥራት፣ በአስፈጻሚ አካላትና በአፈ ጉባዔዎች ዘንድ የሥልጣን ግጭት መኖሩ፣ ተግባብቶ በቅንጅት አለመሥራት፣ በቋሚ ኮሚቴዎች ያለመስማማትና በቅንጅት ያለመሥራት፣ ወዘተ በጥናቱ ተጠቅሰዋል፡፡

ጥናቱ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዓባይ ጸሐዬ፣ አስፈጻሚው በሁሉ ነገር ላይ የበላይ መሆን እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡

ለምክር ቤት የሚቀርበው ሕግ፣ ሹመት፣ ሪፖርት፣ በጀት የሚፈጸመው በጥድፊያ ነው ያሉት አቶ ዓባይ፣ በሰዓታት ውስጥ አስፈጻሚው እንዲፀድቅ እንደሚፈልግና ሕዝቡም በዚህ የተነሳ ለውጥ አይመጣም ብሎ እንደሚያምን ተናግረዋል፡፡

ይህንን ክፍተት ድርጅታዊ አሠራርም የሚገታው እንደማይመስላቸው የተናገሩት አቶ አቶ ዓባይ፣ ‹‹በድርጅታዊ አሠራር ችግሩን ለመቅረፍ መጀመሪያ ኢሕአዴግ መስተካከል አለበት፤›› ማለታቸውን ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ባቀረበው በዚህ ጥናት ላይ በሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሪፖርቱን እንደማያውቁት ተናግረዋል፡፡

‹‹የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል አቀረበ የተባለው ሪፖርት እኔ ጋ የደረሰ አይደለም፡፡ ስለዚህ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የለኝም፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከፓርላማ ክትትልና ቁጥጥር ጋር የጥናት ማዕከሉ አቀረበ ስለተባለው ሰምተው ኃላፊዎቹን እንዳነጋገሯቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹ጠይቄያቸው ነበር የፌዴራል ፓርላማን የሚመለከት አይደለም ነው ያሉኝ፡፡ ስለዚህ የተሳሳተ መረጃ ነው የተላለፈው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በማግሥቱ ሐሙስ ሚያዝያ 12 ቀን 2009 ዓ.ም. የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የምርመራ ሪፖርት ፓርላማው ያደመጠ ሲሆን፣ በዚሁ ዕለት የተገኙት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትሩ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበው ሪፖርት ለብዙ ጉዳዮች መልስ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ እየተፈጠረ ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ክትትልና ቁጥጥር (Check and Balance) እንዲረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ፣ ተጠያቂነት ለማስፈን የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚገታ ግዙፍ ችግር እንደሌለ፣ አስፈጻሚው እዚህም እዚያም ጣልቃ እየገባ ተፅዕኖ እየፈጠረ፣ አልጠየቅም ብሏል፣ አስቸግሯል ብለው ለሚረዱ አንዳንድ ወገኖች ምላሽ የሚሰጥ ሪፖርት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የክልሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ሥጋቶች

በፌዴራላዊ ሥርዓት አወቃቀር መሠረት ክልሎች ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ የማስተዳደር መብት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያም በሕግ የተረጋገጠ ነው፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሠረት በኢትዮጵያ አንድ ወጥ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የመንደፍና ተግባራዊነቱን የመከታተል ኃላፊነት የተሰጠው ለፌዴራል መንግሥት መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የመጨረሻ ግብ ተደርጎ የሚቆጠረውም በኢትዮጵያ አንድ ወጥ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማኅበረሰብ መፍጠር ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ክልሎች ያላቸውን ሉዓላዊ መብት በመጠቀም ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክቶችን “Public Private Partnership” (የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጋራ ኢንቨስትመንት) ሞዴል ተግባራዊ ማድረግ ጀምረዋል፡፡

ይህ ሞዴልና በክልሎቹ የተጀመሩት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ከፌዴራል መንግሥት ዕቅዶች ማለትም ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ፕሮራሞች ጋር ምን ያህል እንደሚጣጣሙ ሪፖርተር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር፡፡

ክልሎች የጀመሩት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም እንጂ፣ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጋራ ኢንቨስትመንት (Public Private Partnership) ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም ብለዋል፡፡

የጋራ ኢንቨስትመንቱ በሕግ መመራት እንዳለበት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፌዴራል መንግሥት የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጋራ ትብብር ፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ እያረቀቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹በሕግና በሥርዓት የሚመራ አገር ነው፣ ስለዚህም ምንም ዓይነት ሥጋት የግል ባለሀብቶች ላይ ሊያድር አይገባም፡፡ ይኼንን ላረጋግጣላችሁ እፈልጋለሁ፤›› ሲሉ በዚህ የክልሎች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ፍርኃት ያደረባቸው የኢንቨስትመንት ፈቃዳቸውን ከፌዴራል መንግሥት ያወጡ ባለሀብቶች እንዳይሠጉ አሳስበዋል፡፡

‹‹በቀጣይ ግን የተባለው ነገር ምን እንደሆነ የምናየው ይሆናል፤›› ሲሉ አቶ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡

በዚህ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የጋራ ትብብር የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ሥራ የጀመሩ ክልሎች መካከል የኦሮሚያ ክልልና የአማራ ክልል ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ክልል በተጠቀሰው የኢኮኖሚ ማዕቀፍ እስካሁን ወደ ሰባት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ የኢንቨስትመንት ካፒታል ሁለት ኩባንያዎችን ይፋ አድርጓል፡፡ ከእነዚህም መካከል ኦዳ ኢንተግሬትድ ትራንስፖርት ለተባለው ኩባንያ የአንድ ቢሊዮን ብር የአክሲዮን ሽያጭ ሲያካሂድ፣ በተመሳሳይ ኬኛ ቤቨሬጅስ ለባለው 5.7 ቢሊዮን ብር ለሚያወጣው የመጠጥ ኢንዲስትሪ 1.2 ቢሊዮን ብር አክሲዮን ሸጧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የክልሎች የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ማዕቀፍን በተመለከተ በገለጹ በማግሥቱ ደግሞ፣ የአማራ ክልላዊ መንግሥት በተጠቀሰው የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ካቀዳቸው 22 ኩባንያዎች ውስጥ የመጀመሪያው የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡

የአማራ ክልል በተጠቀሰው ማዕቀፍ ይፋ ያደረገው ዓባይ የኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር የተባለ ሲሆን፣ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 22 ታላላቅ ኢንዲስትሪዎችን ለመገንባት ዕቅድ ይዟል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy