በተቋማት ቀልጣፋና ውጤታማ አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ተግባራትን ለማጠናከር በእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር ኢንስቲትዩት የሚከናወኑ ድጋፎች እንዲቀጥሉ በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው የእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየርን ዛሬ አነጋግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ቀልጣፋና ውጤታማ ሥራ በማከናወን የአገልግሎት ተደራሽነት ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት በእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ብሌየር ኢንስቲትዩት የተጀመሩ የድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጠይቀዋል።
ኢንስቲትዩቱ የመልካም አስተዳደር ችግርን ለማቃለል በኢንቨስትመንት ቦታዎችና በኢንዱስትሪ ፓርኮች የተለያዩ የድጋፍ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ተጠቁሟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደተናገሩት፤ በአገሪቷ ውጤታማና ቀልጣፋ የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማምጣት የሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመቀመር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል።
ለዚህም በኢንስቲትዩቱ የተጀመሩ የድጋፍ ተግባራት ተጠናክረው እንደቀጥሉ ኢትዮጵያ ፍላጎት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም መግለጻቸውን ውይይቱን የተከታተሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እውነቱ ብላታ ተናግረዋል።
የእንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌየር በበኩላቸው እንደገለጹት፤ አገሪቷ በኢንዱስትሪው መስክ እድገት እያስመዘገበች ነው።
ይህን ለውጥ በመደገፍ “ውጤታማ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት ማረጋገጥ ያስፈልጋል” ብለዋል።
በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የአቅም ግንባታ ሥራ ማከናወንና የመሰረተ ልማትን ማሟላት ለአገሪቷ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንደሚሰጥም ገልጸዋል።
በኢንስቲትዩቱ የተጀመሩ የድጋፍ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አውስተዋል።