Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ልትከተለው የምትችለው አዲሱ የፖሊሲ አማራጭ

0 673

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከአሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ ቅኝ ገዥው ጣሊያን በመጀመሪያ አሰብን፣ ቀጥሎም ምፅዋን፣ ከዚያም ቀስ በቀስ እየተጓዘ እስከ መረብ ወንዝ ድረስ ያሉትን አውራጃዎች ‹‹ኤርትራ›› ብሎ በመሰየም ቅኝ ግዛቱ አድርጎ ከማወጁ በፊት፣ ይህ ክፍለ አገር ‹‹መረብ ምላሽ ወይም ምድረ-ሀማሴን›› እየተባለ ይጠራ እንደነበር ዘውዴ ረታ ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› በሚለው መጽሐፋቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነገሥታት መንበር ከአክሱም ወደ ላስታ፣ ከላስታ ወደ ጎንደር እንደገናም ወደ አክሱም በተዘዋወረበት ዘመን ይህን አገር ጣሊያን ‹‹ኤርትራ›› ብሎ በጦር ኃይል እስከያዘበት 1885 ዓ.ም. ድረስ ‹‹ባህረ ነጋሽ›› እየተባለ በንጉሠ ነገሥት በሚሾሙ ታላላቅ ሰዎች ሲተዳደር የኖረ መሆኑን፣ ዘውዴ ረታ በመጽሐፋቸው አብራርተዋል፡፡

የዛሬዋ ኤርትራ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የምትዋሰንና ትንሽ የቆዳ ስፋት ያላት አገር ነች፡፡ በአሁኑ ወቅትም የሕዝቧ ቁጥር ከስድስት ሚሊዮን እንደማይበልጥ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኤርትራ በሰሜን ምሥራቅ በኩል ካሉ የአፍሪካ አገሮች መካከል ቀይ ባህር የሚያዋስናት አገር ነች፡፡ ቀይ ባህር ከአሰብ ወደብ ጋር የተያያዘ በመሆኑ ለንግድና ሌሎች እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው ነው፡፡ አሰብ ወደብ ከቀይ ባህር፣ ቀይ ባህር ደግሞ ከስዊዝ ካናልና ሌሎች አካባቢዎች ጋር የሚገናኝ በመሆኑ በርካታ አገሮች ትኩረት ሲያደርጉበት ይታያል፡፡ የአሰብ ወደብ ባለቤት ለሆነችው ኤርትራ ብዙ አገሮች፣ በተለይም የዓረብ አገሮች የተለየ ቦታ ሲሰጧት ይስተዋላል፡፡

በዚህ ስትራቴጂካዊ ሥፍራ የበላይነቱን ለመያዝ የዓለም አገሮች በአሁኑ ወቅት ዓይንና ጆሮአቸውን በዚህ አካባቢ እንዳደረጉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ሩሲያና ሌሎች በርቀት የሚገኙ አገሮች በቀይ ባህር ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርገው ከሚንቀሳቀሱ አገሮች ጥቂቶች ሲሆኑ ከቅርብ አገሮች ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኢራን፣ ግብፅ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ኳታር፣ እስራኤል፣ ቱርክና ሌሎች አገሮች ከፍተኛ ትኩረት የሚያደርጉበትና ፍላጎታቸውንና ኃይላቸውን የሚያሳዩበት አካባቢ መሆኑን በቅርብ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህን ከአሰብ ወደብ ጋር የተያያዘውን የቀይ ባህር አካባቢ የጂኦ ፖለቲካ የበላይነት ለመውሰድ እንደ አሜሪካ፣ ቻይናና የአውሮፓ ኅብረት የመሳሰሉት አገሮች ለዚህ ስትራቴጂካዊ ቦታ ቅርበት ባላት ጂቡቲ ላይ ወታደራዊ የጦር ሠፈር መሥርተው እንደከተሙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አሜሪካ ብቻ በጦር አውሮፕላኖችና በድሮኖች የሚደገፍ ከ4,500 በላይ የሚሆን ወታደራዊ ኃይል በጂቡቲ እንዳሰፈረች መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ቻይናም በዚች ትንሽ አፍሪካ አገር ወታደራዊ የጦር ሠፈሯን  ሠርታ ጨርሳለች የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ከ4,000 በላይ ወታደሮች የሚይዘው የፈረንሣይ የጦር ሠፈር ደግሞ ቋሚነቱ አገሪቱ ነፃ ከወጣችበት ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ የቀጠለ መሆኑ ይነገራል፡፡

አሁን ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያ የየመን ሁቲዎችን በዓረብ አገሮች የጋራ ቅንጅት ለመዋጋት በሚል ሰበብ በጂቡቲ ወታደራዊ የጦር ሠፈር ለመመሥረት ደፋ ቀና እያለች እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በፈጸመችው ወታደራዊ ውል መሠረት በአሰብና አካባቢው ለፈጣን ወታደራዊ አውሮፕላኖች፣ ሔሊኮፕተሮች፣ ወታደራዊ ጀልባዎች፣ ወዘተ. የሚሆን የጦር ሠፈር በማቋቋም ላይ እንደምትገኝ ይነገራል፡፡ የግብፅ መንግሥትም እንዲሁ፡፡ እነዚህ ወታደራዊ አሠላለፎች በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ ጂኦ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ሁለቱ መንግሥታት አሁን ባለው ፍጥጫ ከቀጠሉ፣ ፖለቲካዊ አሠላለፉ አንዱ ሌላውን ለመጉዳት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ የሚናገሩም አሉ፡፡

የእነዚህ ሁለቱ አገሮች ፍጥጫና በዓይነ ቁራኛ የመተያየት አባዜ የበለጠ እየከረረ የመጣው ግን ከ1990 ዓ.ም. የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ ነው፡፡ ይህ ‹‹የባድመ ወረራ›› እየተባለ የሚጠራው ጦርነት ድፍን ሃያ ዓመት ሊሞላው የተቃረበ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ድረስ ሁለቱ አገሮች ‹‹ሰላም የለሽ፣ ጦርነት የለሽ›› ቀጣና ውስጥ እንዲገኙ አድርጓቸዋል፡፡

እነዚህ በዚህ ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ሁለቱ አገሮች ለአሥራ ዘጠኝ ዓመታት ያህል ዓይንና ናጫ ሆነው፣ አንዱ በአንዱ ላይ የበላይና አሸናፊ ለመሆን የሚያደርጉት እሰጥ አገባ እስከ ዛሬ ድረስ እልባት አላገኘም፡፡

ከጦርነቱ በኋላም ቢሆን አንዱ አንዱን በመክሰስና በመወንጀል ጂኦ ፖለቲካዊ የበላይነትን ለመውሰድ እየተደረገ ያለው ጥረት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ሁለቱም ከድንበር ግጭቱ ወዲህ የሚከተሉት ፖሊሲ ሌላ ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖር ‹‹አትንካኝ፣ አልነካህም›› ወይም ‹‹ጦርነት ካልከፈትክብኝ እኔም አልነካህም›› ዓይነት ሁኔታ በሁለቱ አገሮች መካከል እንዳለና እንደሚያራምዱ አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ በኩል ይህንን ችግር ለመፍታት ብዙ ሙከራዎች ሲደረጉ የቆዩ ቢሆንም፣ እስከ ዛሬ ድረስ ግን ጠብ የሚልና የመፍትሔ አካል የሆነ ጉዳይ አልታየም፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያለውን ውዝግብና ግጭት ‹‹በውይይትና በድርድር መፍታት››፣ ይህ ካልሆነ ግን ለሚደረጉ ትንኮሳዎችና ዕርምጃዎች ሁሉ ‹‹ተመጣጣኝ ዕርምጃ በመውሰድ›› ጉዳዩን አስታግሳለሁ ዓይነት ፖሊሲ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እንዳላመጣና መፍትሔ እንዳላሳየ አሁን ያለው ሁኔታ ገላጭ ነው፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ሳይቀሩ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ፣ ‹‹ኤርትራ ድረስ ሄጄ የሁለቱን አገር መሪዎች አወያያለሁ፡፡ ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ አደርጋለሁ፤›› የሚል ሐሳብ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ጉዳዩ ተፈጻሚ ባይሆንም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ሥልጣን በመጡ ሰሞን አስመራ ድረስ በመሄድ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር መነጋገር ካለባቸው እሱን ለመፈጸም ዝግጁ እንደሆኑ ለዓለም አቀፍ ሚዲያዎች መግለጻቸውም አይዘነጋም፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ኤርትራን በተመለከተ አዲስ ፖሊሲ ልትከተል እንደምትችል በቅርቡ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህ በፊት ስታራምዳቸውና ስትከተላቸው የነበሩ ፖሊሲዎች ፍሬ እንዳላፈሩና የዚህን ችግር ከሥር መሠረቱ እንዳልቀረፉ በመረዳት፣ አዲስ ፖሊሲ ልታወጣ መሆኑን ባለፈው ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ትግራይ ክልል አቅንተው ከሕዝቡ ጋር ውይይት ባደረጉበት ጊዜ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ የስድስት ወራት ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ኤርትራን በተመለከተ ከዚህ በፊት ታራምደው ከነበረው ሕግ ለየት ያለ ይዘት ያለው ፖሊሲ መረቀቁንና በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን ይፋ አድርገዋል፡፡

ኤርትራ ቀይ ባህር የሚያዋስናት አገር በመሆኗና ይህ አካባቢ ደግሞ በዓረቡ ዓለም፣ ለመካከለኛው ምሥራቅ ቅርቡ በሆኑ የአውሮፓ አገሮች የትኩረት ማዕከል በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በዚህ አካባቢ የነበራትን ቀጣናዊ የበላይነት ልትነጠቅ የምትችልበት አጋጣሚ እንዳለ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሪፖርተር አንዳንድ ባለሙያዎችን አነጋግሯል፡፡

ስለአፍሪካ ታላላቅ ጉዳዮች ሰፋ ያለ መረጃና ትንታኔ የሚሰጠው ‹‹ዲስኮርስ›› የተሰኘው መጽሔት ዋና አዘጋጅና የፐብሊክ ፖሊሲ ተንታኝ የሆኑት አቶ ዳዲ ደስታ እንደገለጹት፣ ‹‹አሰብ ሁሌም በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ዘንድ መነሳት ያለበት ነገር ነው፡፡ ይህን ሰፋ አድርገን ብናየውና የቀይ ባህር ቀጣና በሚለው ብንወስደው ትኩረት የሚስብ ጂኦ ፖለቲካል ዞን ነው፡፡ ብዙ ንግድና እንቅስቃሴ የሚካሄድበት አካባቢ ነው፡፡ ይህ አካባቢ ኃያላን የሚባሉ አገሮችን ትኩረት የሚስብና በዚህ አካባቢ የፖለቲካ ተዋናይ የሚባሉት ተፅዕኖአቸውን እያሰፉ መጥተዋል፡፡ ኤርትራ በፈጠረቻቸው ስህተቶችና ጥፋቶች ምክንያት ከዓለም፣ ከጎረቤት አገሮችና አካባቢያዊ ትስስሮች ራሷን እያገለለች የመጣች ነች፡፡ በዚህም የተነሳ ከዓረቡ ዓለም ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ጥረት ስታደርግ ትታያለች፡፡ የቀይ ባህርንና የአሰብ ወደብ አካባቢን ‘ዓረባይዝ’ ወደ ማድረግ እየሄደች ያለችና ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ አካባቢ የነበራትን ታሪካዊ ጥቅም እንድታጣ ወደ ማድረግና መግፋት ዓይነት ዝንባሌ ነው እያካሄደች ያለችው፡፡ በዚህ አካባቢ ግን በዲፕሎማሲና በትብብርም ሆነ በሌላ ዘዴ ትኩረት ልናደርግበት የሚገባ ነው፡፡ እንደ አገር ግን ይህን የሚያስችል እንቅስቃሴ ሲደረግ አይታይም፡፡ ኢጋድም ቢሆን ይህንን አካባቢ በተለይ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከየመንም ሆነ ከሌሎች አገሮች ጋር የጉርብትና መስመር በመዘርጋት ሲሠራ አይታይም፡፡ በዚህም በጨዋታውና እንቅስቃሴው ውስጥ ገብቶ ክትትልና የራሳችንን ጥቅም ለማስከበር የሚደረግ ጥረት የለም፡፡ እዚህ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ እንዝላልነት ይታያል፡፡ ከዚህ ከፍተኛ ዋጋ ካለው አካባቢ የመውጣት ዝንባሌ በኢትዮጵያ ይታያል፡፡ ይህንን ለማንም አሳልፈን የምንሰጠው ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የንግድ መርከቦችን ማንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን የባህር ኃይሏንም በማንቀሳቀስ ራሷን የምትከላከልበት ሁኔታ መፈጠር ነበረበት፡፡ የዓረቦች ወደዚህ አካባቢ መምጣት ደግሞ ጉዳዩን የተወሳሰበ ያደርገዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ከፍተኛ ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ምን የተወሳሰበ የወደፊት ሁኔታና ችግር ይፈጥራል? የሚለውን ነገር በትክክልና ሌት ከቀን ማሰብ ያለበት የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ተንታኝ የሆኑት አቶ ጌታቸው መኮንን ይህንን ጉዳይ በተመለከተ፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ጦርነት የለሽ፣ ሰላም የለሽ ግንኙነት ሆኖ ለዓመታት የዘለቀው የኤርትራ መንግሥት የቀረቡትን የሰላም አማራጮች ባለመቀበሉ ምክንያት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በቀይ ባህርና በአሰብ ወደብ አካባቢ የዓረቦች መምጣት ለኤርትራ መንግሥት የኢኮኖሚ ማንሰራራት የራሱ የሆነ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ከአሰብ ወደብ በሚገኝ ኪራይ ሥርዓቱ ለእኩይ ተግባር ሊጠቀምበት የሚችልበት ሁኔታና የኢትዮጵያን ሰላም፣ የአጎራባች አገሮችንም ሰላም ሊያውክ የሚችልበት መደላድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪና የጂኦ ፖለቲካል ጉዳዮች ዲፓርትመንት ኃላፊ አቶ አበበ ዓይነቴ ይህንን ጉዳይ ሲያብራሩ፣ ‹‹አሁን ባለው ሁኔታ ብዙም የከፋ ነገር ውስጥ አልተገባም፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከአውሮፓና ከዓረብ አገሮች ጋር ጥሩ ግንኙነት ነው ያላት፡፡ ወደ ኋላ ሄደን በ14ኛውና በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረውን ሁኔታ ስንመለከት ግን፣ የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ በላላበትና ይህንን የቀይ ባህርና የህንድ ውቅያኖስ አካባቢ ለመቆጣጠር ያለን ተፅዕኖ ባነሰ ጊዜ የአውሮፓና የመካከለኛው አገሮች ጎልተው የሚወጡበት የታሪክ አጋጣሚ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ጠንካራ አገርና ጠንካራ መንግሥት ስትሆን በህንድ ውቅያኖስም ሆነ በቀይ ባህር አካባቢ ያሉ ሁኔታዎችን የመቆጣጠር አቅም ይኖራታል፡፡ የኢትዮጵያ ጠንካራ መሆን ደግሞ በዚህ አካባቢ የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ ጤናማ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2009 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ በጣለው ማዕቀብ፣ የኤርትራ መንግሥት የውስጥ አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል፡፡ ዜጎችም ለስደትና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡ በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግጭት ቶሎ አለመፈታቱ በዚህ የባህርና የህንድ ውቅያኖስ አካባቢ እያቆጠቆጠ ያለው ከፍተኛ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ብዙውን ጊዜ ወደ ቀይ ባህር አካባቢ የሚሳቡት በኤርትራ በኩል ያለውን ክፍተት እንደ በጎ አጋጣሚ በመጠቀም ነው፤›› ብለዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር አቶ አበበ ዓለሙ በበኩላቸው፣ ‹‹የዓረብ አገሮች ግብፅን ጨምሮ ለኢትዮጵያ ጥሩ አመለካከት የላቸውም፡፡ እነ ቻይና፣ ሩሲያና ሌሎች አገሮች በአሁኑ ወቅት በዚህ ቀጣና የበላይ ሆኖ ለመገኘት በጂቡቲ ወታደራዊ የጦር ሠፈር በማቋቋም ላይ ነው የሚገኙት፡፡ ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ የፀጥታ ሥጋት ከመሆኑ ባሻገር ፖለቲካዊ ኃይልነቷን የሚያሳጣ ጉዳይ ይሆናል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እነዚህንና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ሲባል ደግሞ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት አዲስ ፖሊሲ ለመከተል እያሰበ እንደሆነ በቅርብ ጊዜ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ለረጅም ጊዜ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የሠሩትና በቅርቡም ‹‹የሰላም ፍኖት ለኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦች አንድነት›› የሚሰኝ መጽሐፍ ያሳተሙት አቶ ተሾመ ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ‹‹የአሰብ ወደብ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ወደ ተለያዩ የዓለም አገሮች ያደርገው በነበረው የንግድ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው ነው፡፡ ይህ አካባቢ የአውሮፓና የመካከለኛው ምሥራቅ የዓለም አገሮችን ትኩረት መሳብ የጀመረው ከጥንት ጀምሮ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያና ሌሎች የዓረብ አገሮች ትኩረታቸውን ወደዚህ አካባቢ ያደረጉ ነው የሚመስለው፡፡ ይህ ወደብ አሰብ ይሁን እንጂ ተፅዕኖው የኢትዮጵያን ጉዳይም የሚነካ ነው፡፡ ለምሳሌ በየመን በተፈጠረው ሁኔታ ብዙ የመናውያን ወደዚህ አካባቢ ከመጡ ተፅዕኖው ለኢትዮጵያም የሚተርፍ ነው የሚሆነው፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ስለሚኖረው አዲስ የፖሊሲ አማራጭ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ሊከተል የሚችለው የኃይል ዕርምጃ መውሰድ ነው ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል የኃይል ዕርምጃን የፖሊሲ አማራጭ አድርጎ መውሰድ አገሪቱን ከፍተኛ መስዋትነት ሊያስከፍላት ስለሚችል፣ ጠንከር ያለ አዲስ የዲፕሎማሲ አማራጭ ነው ልትከተል የሚገባት የሚሉ ወገኖች ደግሞ በሌላ በኩል ይደመጣሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም አቶ ዳዲ ደስታ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ዳዲ፣ ‹‹ከዚህ በፊት እንደምናውቀው ሰላምና ድርድር የሚለው ነገር ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ በኩል የተቀመጠ ነገር ነው፡፡ የኤርትራ መንግሥት ግን ለዚህ ጉዳይ ጆሮ አልሰጠም፡፡ ወደፊትም የሚሰጥ አይመስልም፡፡ ዞሮ ዞሮ አሁን አዲሱ ፖሊሲ ምን ሊሆን ይችላል ነው ጥያቄው፡፡ እኔ አጠቃላይ የፖሊሲ ለውጥ ከመጣ ትክክልና እሰየው ብዬ ነው የምወስደው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በፊት የነበረው ፖሊሲ እየሠራ አይደለም፡፡ ኤርትራንም እየጠቀማት አልነበረም፡፡ እየሠራ ያልነበረ፣ ያውም ትናንት መቀየር የነበረበት ፖሊሲ ነው፡፡ ለረጅም ዓመታት ያለ ግንኙነትና በዙሪያው ብዙ ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮች ያሉበት ነገር ክፍተት እየፈጠረ ያለው የእኛው ክፍተት ነውና መቀየር ከነበረበት እንዲያውም ቆይቷል፡፡ ፖሊሲው ምን ሊሆን ይችላል? በሚለው ጉዳይ ላይ እንደዚህ ነው ብሎ መናገር ያስቸግራል፡፡ ምን ቢሆን ይሻላል? ከተባለ ግን መናገር እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ይህ አካባቢ ምን መምሰል አለበት? ብላ ማሰብ አለባት፡፡ ይህን አካባቢ ወደ ሰላማዊና አገሮች የሚበለፅጉበት ሁኔታ የሚፈጠርበት እንዲሆን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥራ ማከናወን ይጠበቅባታል፡፡ አጠቃላይ የአካባቢውን ሁኔታ ሊቀይር የሚችልበትን ሁኔታ ማረጋገጥ አለባት፡፡ ሁለተኛ የኤርትራ መንግሥት ከረጅም የጦርነትና የተጋድሎ ዘመን በኋላ ትንሽ እፎይ ሳይል ወደ ተወሳሰበና ፋታ የማይሰጥ ሥርዓት ውስጥ ነው የገባው፡፡ ወጣቶች በየጊዜው እየተሰደዱ ነው ያለው፡፡ አካባቢው ተስፋ አለው የምንለው አይደለም፡፡ ስለዚህ አዲሱ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ለዚህ ችግር እፎይታ የሚሰጥና ወደ ሰላም የሚያመራ ዓይነት መሆን አለበት፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተስተካከለ ቁመናና መስመር ውስጥ የሚያስገባ መሆን አለበት፡፡ ይህ ሁሉ ግን ከጦርነትና ደም መፋሰስ ውጪ በሆነ ሁኔታ ነው መሆን ያለበት፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ጌታቸው መኮንን በበኩላቸው፣ ‹‹ኤርትራን በተመለከተ አዲሱ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ሁለቱን አገሮች ወደ ግጭት የሚከት ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ነገር ግን ሻዕቢያ እያስታጠቀና እያሠለጠነ የሚልካቸውን ምንደኞች የተመጣጠነ አፀፋዊ መልስ በመስጠት የመከላከል ፖሊሲና ተግባር ሊኖር ይችላል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ባለመግባት በገለልተኝነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ በኤርትራ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚያስገባ ፖሊሲ ትከተላለች ብዬ አላምንም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያ የኃይል ዕርምጃ ትወስዳለች የሚል ሐሳብ ሲያንፀባርቁ ይሰማል፡፡ እኔ ግን የሻዕቢያን ሥርዓት የማስወገድ ጉዳይ የኤርትራ ሕዝብ ብቻ ነው መሆን ያለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ያለው ጉዳይ ለእኔ አላማረኝም፣ ለአገሩ ሕዝብም አይጠቅምም፣ ስለዚህ መወገድ አለበት ብሎ ሥርዓቱን ለማስወገድ መፈለግ የአንድን ሉዓላዊ አገር የውስጥ ጉዳይ መዳፈር ሊሆን ይችላል፡፡ ሻዕቢያን ዝም ብለን ቆመን መጠበቅ ሳይሆን አቅሙን በዲፕሎማሲያዊ፣ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ ጉዳዮች እንዲዳከምና ዳግም ወደ ወረራ እንዳይገባ በስፋት ይሠራበታል የሚል እምነት ግን አለኝ፡፡ በተጨማሪም የሻዕቢያን መንግሥት ከኤርትራ ሕዝብ የመነጠል ሥራ ይከናወናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የኤርትራ ሕዝብን በተመለከተ ሕዝባዊ ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ካለ ያለምንም ማወላዳት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ፣ ለእነዚህ ትግሉን የሚያንቀሳቅሱ ድርጅቶች ድጋፍ አድርጎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፀር የሆነውን የሻዕቢያ መንግሥት መገርሰስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ የሚፈጠርበት ፖሊሲ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

አቶ አበበ ዓይነቴ ከዚህ ጋር በተያያዘ፣ ‹‹አዲሱ የኢትዮጽያ ፖሊሲ ከጦርነት ባሻገር ያሉ አማራጮችን በሙሉ አሟጦ መጠቀም የሚያስችል ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝቦች አቀራርቦ የማነጋገር ስትራቴጂ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡ በዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት የተመዘገቡ ከ180,000 በላይ የሚሆኑ ኤርትራውያን ስደተኞች በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፡፡ እነዚህንና በሌላው ዓለም የሚኖሩ ኤርትራውያንን በቅርብ ማግኘትና ማወያየት ተገቢ ነው፡፡ ከእነሱ ጋር መወያየት ማለት ደግሞ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር በቀጥታ መነጋገር ማለት ነው፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ ትልቅ አገር እንደ መሆኗ አጀንዳዎችን በራሷ ተነሳሽነት ጥያቄ ከማቅረብ ባሻገር ገፍታ በመሄድ ከኤርትራ መንግሥት ጋር ውይይትና ምክክር ማድረግ አለባት፡፡ ሁሌ የተሻልክ ስትሆን ማድረግ ያለብህ ይህንን ነው፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ አበበ ዓለሙ ደግሞ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ልትከተል የምትችለው አዲስ ፖሊሲ ሊሆን የሚችለው ታዋቂና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎችን (ለምሳሌ የቀድሞዎቹን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ኃላፊዎች ሊሆን ይችላል) በመጠቀም፣ ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመወያየትና በመደራደር ሊፈታ የሚችል ሊሆን ይችላል፡፡ ጦርነትን ሁለቱም አገሮች የሚፈልጉት አይመስለኝም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የእንነጋገር ሐሳብ ‘በፍጹም አልቀበለውም፣ መሬቱ ይሰጠኝና ከዚያ በኋላ እንነጋገራለን’ የሚለው አቋሙ ፀንቶ የቀጠለ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ‘ቁጭ ብለን ካልተነጋገርን አሳልፌ የምሰጠው መሬት የለኝም’ የሚለውን አቋሙን አጠናክሮ እንደያዘ ይወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ የኤርትራ መንግሥት ባለፉት አሥራ አምስትና አሥራ ስድስት ዓመታት የኦነግ፣ የግንቦት ሰባት፣ የአርበኞች ግንባርና ሌሎች ቡድኖችን በማሠልጠንና በማስታጠቅ ወደ ኢትዮጵያ ሠርጎ ገቦችን በማስገባት አገሪቱን የማተራመስ ሥራ ሲሠራ እንደቆየ ኢትዮጵያ ትከሳለች፡፡ ይህንን ድርጊቱንም በአሁኑ ወቅት አጠናክሮ እንደቀጠለበት ይሰማል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ትልቅ አገር በመሆኗና በዓለም ተሰሚነቷ እየተጠናከረ በመምጣቱ ምክንያት፣ በተመድ ለፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ከ190 ተሳታፊ አገሮች የ185 ድጋፍ አግኝታ እ.ኤ.አ. ከጥር 1 ቀን 2017 ጀምሮ ወንበሯን ለመያዝ ችላለች፡፡ ድጋፍ ከነፈጓት አምስት አገሮች መካከል ኤርትራ እንደምትገኝበት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በትንሹም በትልቁም ጉዳይ እንካ ሰላንትያ በመግጠም መዝለቅ የለባትም የሚሉ ወገኖች ከየአቅጣጫው ይሰማሉ፡፡ ይህንን የኤርትራ ትንኮሳና የቀጣናው አሸባሪ መሆን በአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት መስጠት ተገቢ እንደሆነ በመጠቆም፣ ኢትዮጵያ የኤርትራ መንግሥት በአንድ ወቅት ይወድቃል የሚል እሳቤውን በመተው ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችል አማራጭ መንገድ መከተል እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም አዲሱ የኢትዮጵያ ፖሊሲ እነዚህን ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት ያክላሉ፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ጀምራ ኤርትራ ወደ ክፍለ አኅጉሩ ድርጅት እንድትመለስ የራሷንና የአባላቱን ተሳትፎ ተጠቅማ እንቅስቃሴ ብታደርግ፣ በኤርትራ መንግሥት ዘንድ ጥሩ የዲፕሎማሲ ዕይታ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል የሚሉ አሉ፡፡ በኢጋድ ደረጃ የሚወሰድ ዕርምጃ ደግሞ የኤርትራን መንግሥት ባህሪ ሊለውጥ የሚችል፣ ብሎም ደረጃ በደረጃ በተመድ የተጣለበትን ማዕቀብ ለማንሳትና ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር ስለሚረዳ ጠቀሜታው ላቅ የለ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ በቅርቡ ልትከተለው ትችላለች ተብሎ የሚታሰበው አዲሱ ፖሊሲ እነዚህን ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡  reporter

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy