NEWS

ኢትዮጵያ የራሷ ሳተላይት ለማምጠቅ ፈቃድ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ናት

By Admin

April 08, 2017

ኢትዮጵያ የራሷ ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ በዘርፉ ፈቃድ ሰጪ ከሆኑ አለም አቀፍ ተቋማትና አገራት ፈቃድ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ መሆኗን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የበላይ ጠባቂ አቶ ተፈራ ዋልዋ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ህዋ ሶሳይቲ 11ኛው መደበኛ ጉባኤው አካሂዷል። በጉባኤው አገሪቱ የራሷ ሳተላይት ወደ ህዋ ስታመጥቅ ለሳተላይት ኪራይ የምታወጣው ወጪ እንደሚቀንስላትም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የበላይ ጠባቂ አቶ ተፈራ ዋልዋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት በዘርፉ የእንጦጦ የህዋ ምርምር ማዕከል ከመገንባት ጀምሮ በላሊበላ የመስኩ አለም አቀፍ የምርምር ጣቢያ ለመፍጠር የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ሳተላይት የማምጠቅ አቅሙ እንዳላት የገለጹት የበላይ ጠባቂው ለተግባራዊነቱ በዘርፉ አቅም ካላቸው አገራት ጋር ተባብሮ ለመስራት ስምምነት መፈረሙን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለዘርፉ በሰጠችው ትኩረትና ባከናወነቻቸው ተግባራት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2012 የዘርፉ አለም አቀፍ ህብረት ሙሉ አባል ሆና ተመዝግባለች።

በምስራቅ አፍሪካም የአስራ አራት አገራት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት መቀመጫ እና አስተባባሪ አገር ሆናለች።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ይዞት የተነሳ ሰፊ ራዕይ የአይቻልም መንፈስ የሰበረ መሆኑንም ተመልክቷል። ሶሳይቲው ተተኪ ተመራማሪዎች ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።

ኢትዮጵያ የራሷ ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ ዝግጅቷን አጠናቃ  በዘርፉ ፈቃድ ሰጪ ከሆኑ አለም አቀፍ ተቋማትና አገራት ፈቃድ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ መሆኗንም ተመልክቷል።