እውነቱን መነጋገር የህልውና ጉዳይ ሲሆን!
ሶፊዝም፤ በአንዳንድ የምስራቃዊው ክፍለ ዓለም አካል በሆኑ ሀገራት ውስጥ የሚመለክ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይሔንኑ መንፈሳዊ እሳቤ የሚያመልኩ ህዝቦችም “ሶፊዎች” በመባል ይታወቃሉ፡፡ እናም ሶፊዎቹን ከሌላ ከማንኛውም ሃይማኖት ተከታይ ምእመናን የተለዩ ተደርገው እንዲወሰዱ የሚያደርጋቸው መሰረታዊ ምክንያት፤ የእውነትን ዱካ በማነፍነፍ መጠመድን የሚያዘወትሩ መሆናቸው ነው ማለት ይቻላል፡፡
ለዚህ የሶፊዝም ሃይማኖት ተከታይ ማህበረሰባችን ከሌላው ዓለም ምእመናን ይልቅ ለአፍቅሮተ እውነት የተለየ ግምት ይሰጣሉ ለሚያሰኛቸው መከራከሪያ ፤ እንደ አብነት ከሚጠቀሱት ጉዳዮችም የሚከተለው ይገኝበታል፡፡ በሶፊ ማህበረሰቦች ዘንድ “ኖር ክበር” የተባለላቸው የእምነቱን መንፈሳዊ አስተምህሮ የሚሰጡ ሊቃውንቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እናም ከነዚሁ የሶፊዝምን ሃይማኖታዊ ሕግጋት የማስተማር ተልዕኮ ወስደው፤ በስብከት ተግባር ላይ ከሚሰማሩ ሊቃውንት መካከል አንዱ የእውነትን አስፈላጊነት ለደቀ መዛሙርቱ ያስረዳበት መንገድ ብዙ ጊዜ ተደጋግሞ ይነሳል፡፡
መምህሩ በሶፊዝም እምነት ተከታዮች ዘንድ አድናቆትን ያተረፈና የእርሱን ጥበብ ተምረው ፈለጉን ለመከተል የሚሹ ወጣቶች የበረከቱለት ዝነኛ ሰው ከመሆኑ የተነሳ በርካታ ደቀመዛሙርትን ለማፍራት ችሏል፡፡ እናም በዚህ መሰረት ከዕለታት አንድ ቀን፤ የእርሱን ጥበብ ለመቅሰም ሽተው ወደሚያስተምርበት ገዳም ከመጡት ደቀመዛሙርት የመሆን ጥያቄ አቅራቢዎች መካከል፤ ለአንዷ ልጃገረድ “አንቺ እንኳን የፊትሽ ውበት ወንዶችን የሚያማልል ስለሆነ የኔ ተማሪ ላደርግሽ አልፈቅድም” የሚል ምላሽ ይሰጣታል መምህሩ፡፡ ፊቷ ላይ የተመለከተው ቆንጆ ገፅታ ወንዶችን ለማማለል የምትጠቀምበት ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ገልፆ አቋሙን ለማስቀየር ብትጥርም ወይ ፍንክች የአባቢላዋ ልጅ!
እንዲያም ሆኖ ወጣቷ በዋዛ የምትበገር አልነበረችምና “ይሄን ውብ የፊቴን ገፅታ በሰው ሰራሽ ዘዴ አበላሽቼ አስቀያሚ ባደርገውስ ትቀበለኛለህን?” የሚል ጥያቄ አቀረበችለት ለመምህሩ፡፡ እርሱም ትንሽ እንኳን የማመንታት ስሜት ሳይስተዋልበት “ያን ማድረግ አለማድረግ ያንቺው የግል ምርጫ ነው እንጂ እኔን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም” ሲል እርምጃውን እንድትወስድ በገደምዳሜ ነገራት፡፡
ቆንጆዋ የሶፊ ልጃገረድ፤ ከጥቂት ሳምታት በኋላ ወደ ታዋቂው መምህር ገዳም ስትመለስም ታዲያ፤ እርሱ ራሱም ጭምር እርሷ መሆኗን እንኳን ለመለየት እስኪቸግረው ውቡ ፊቷ ተቦዳድሶ ነበር፡፡ ወጣም ወረደ ግን፤ ማንነቷን ስትገልፅለት ጊዜ “አሁን ፈቅጄልሻለሁ” ሲል መምህሩ ጥያቄዋ ተቀባይነት ማግኘቱን ያረጋግጥላታል፡፡ እንዲህ የተጀመረው የሁለቱ ባለታሪኮች ግንኙነት፤ ጥበብ በመስጠትና በመቀበል ሂደት እየዳበረ ቀጥሎ ተቀራርበው የሆድ የሆዳቸውን መጨዋወት ሲችሉም “የወጋ ቢረሳ፤ የተወጋ አይረሳም” እንደሚባለው ሆኖ፤ እርሷው ጉዳዩን ታነሳበትና ለምን ያን ያህል ጭካኔ እንዳሳያት ትጠይቀዋለች ለመምህሯ፡፡
እንግዲያውስ የሶፊዝም ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ሊቁ ለዚያቺ እንስት ደቀመዝሙሩ የመጨረሻ ጥያቄ የሰጠውን ምላሽ ነው እኔም ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ህዝቦች የሚጠቅም መልዕክት ያዘለ ሆኖ ያኘሁት፡፡ ስለዚህም ሶፊው መምህር አንድ ወቅት የወጣቷን ቆንጆ የፊት ገፅታ ወደ አስቀያሚነት እንዲቀየር ያደረገ አቋም ይዞ የተገኘበት ምክንያት ምን እንደነበር ሲያብራራ ከተናገረው ላይ ጥቂት ለኛ አገሩ አጠቃላይ እውነታ ጠቃሚ ሆነው ያገኘሁዋቸውን ነጥቦች እንደሚከተለው ለማስታወስ ሞክሩያለሁና አብረን እንመልከት…
“በሰው ልጆች መካከል የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት መስተጋብር (ግንኙነት) የተሻለና ዘላቂነት ያለው ሊሆን እንዲችል ሲባል ብዙውን ጊዜ እርስ በዕርስ ስንነጋር ከምንወሻሽ ይልቅ እውነቱን ማስቀደም ይሻላል ብዬ አምናለሁ” ሲል የእንስቷን ተማሪውን ቅሬታ አዘል ጥያቄ በምክንያት አስደግፎ ለመመለስ ያለመ ንግግሩን የጀመረው የሶፊዝሙ ሃይማት አባት “በተለይም አንዳንዴ እውነቱን እና እውነቱን ብቻ የመነጋገር አስፈላጊነት የህልውና ጉዳይ ሆኖ የሚገኝበት አጋጣሚ አለ” የሚል ምክሩን እንዳከለ ነው ያነበብኩት፡፡
ይህን ስለ የሶፊዝም እምነት ተከታይ ማህበረሰቦች አፍቅሮተ እውነት የሚያወሳ ተረክ ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ፤ የተጠቃሿ ልጃገረድ ውብ የፊት ገፅታ እንኳንስ ጥበብ ለመማር ሲሉ እርሱ ዘንድ በሚታደሙት ወጣት ወንዶች ላይ፤ እርሱን ራሱንም ሳይቀር ስጋዊ ፍላጎት እንዲፈታተነው የሚያደርግ አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ገብቶታል፡፡ እናም ይህን ጥሬ ሃቅ ልቦናው እያወቀ፤ ጉዳዩን በዋዛ ፈዛዛ ሊያልፈው ቢፈቅድ ኖሮ፤ ብዙሃኑን ሰዎች ላሰባሰባቸው መሰረታዊ ዓላማ ተገቢ ዋጋ እንዳለመስጠት ይቆጠርበት ስለነበረ እንጂ እርሷን መጉዳት ፈልጎ አይደለም ብለን ልናጠቃልለው የምንችል ይመስለኛል፡፡
ስለዚህ፤ በተለይም “እውነቱን አንስተን በድፍረት የመነጋገር አስፈላጊነት የህልውና ጉዳይ ሆኖ የሚገኝበት አንዳንድ ወሳኝ አጋጣሚ አለ” የምትለዋን ቁልፍ ነጥብ ወስደን ብንመለከት እንኳን፤ ከኛው ሀገር ወቅታዊ እውነታዎች አኳያ ሲቃኝ ሊሰጠን የሚችለው ትርጉም ፈርጀ ብዙ እንደሚሆን ነው ለኔ የሚሰማኝ፡፡ ይህን ስልም ደግሞ፤ መላው የሀገራችን ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚያካሔዱትን ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ጉዞ፤ ለማስቀጠልና ላለማስቀጠል በሚፈልጉ የፖለቲካ ሃይሎች መካከል፤ የሚስተዋለውን ፍጥጫ ከማርገብ ጀምሮ፤ ሌሎችም በርካታ ጉዳዮቻችን፤ እውነቱን መነጋገር የህልውና ጥያቄ እየሆነ መምጣቱን የሚያመለክቱ ናቸው ብዬ እንደማምን መጠቆሜ ነው፡፡
ስለሆነም ፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፈርጀ ብዙ መስዋዕትነትን በጠየቀ የዘመናት ትግል የተቀዳጀነውን ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ከቅልበሳ አደጋ ለመታደግና የጀመርነውን የስር ነቀል ለውጥ ጉዞ ይበልጥ አጠናክረን ለማስቀጠል እንችል ዘንድ፤ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ እውነቱን ልንነጋገርባቸው የሚገባን የጋራ ርዕሰ ጉዳዮች ስለመኖራቸው አምነን መቀበል ይጠበቅብናል የሚለው ነጥብ ላይ ይሰመርበት፡፡ ይህን መሰረተ ሀሳብ አንስተን መወያየት ካለብንም ደግሞ፤ እውነቱን መነጋገር የጋራ ህልውናችንን የሚወስን ጉዳይ ተደርጎ እንዲወሰድ የሚጋብዝ ገፅታ ያላቸው ሀገራዊ ችግሮች ምንምን ናቸው? በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ተገቢውን የጋራ ግንዛቤ መጨበጥ እንደሚጠበቅብን የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡
እናም እንደኔ አረዳድ፤ የፌዴራሊዝም ስርዓቱን ለትግራይ ተወላጆች የበላይነት የቆመና ሌላውን ኢትዮጵያዊ የብሔር ብሔረሰብ ህዝብ እንብዛም የማይመለከተው እንደሆነ ተደርጎ እንዲወሰድ የሚሞክርበትን አግባብ የማጥራት ጉዳይ ቀዳሚ ስፍራ ሊሰጠው የሚገባ ሆኖ ይሰማኛል፡፡ እውን በዚህ መልኩ ሲነሳ የሚደመጠው ቅሬታ እውነትነት ያለው ነውን? ከሆነስ ተጨባጭ መገለጫው ምንድነው?ነገሩ መሰረተ ቢስ ነው ከተባለስ ታዲያ ለምን ዓላማ በዚህን ያህል ጩኸት ሲደጋገም ይሰማል? ወዘተ የሚሉትን ነጥቦች ህዝቡ በውል እንዲያውቃቸው ማድረግ ግድ ይላል የሚል እምነት አለኝ፡፡
ከዚህ አኳያ የሚነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ እየተፈጠረ ያለውን ብዥታና እንዲሁም ደግሞ ትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ላይ አልፎ አልፎ የሚስተዋለውን የጥላቻ አዝማሚያ በመታገል ረገድ ከህወሐት ውጭ ያሉት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ምን ያህል ጥረት አድርገዋል? ብሎ መጠየቅ እንደሚገባም ነው እኔ በግሌ የማምነው፡፡ በተለይም ደግሞ የፌዴራል ስርዓቱ ለሁሉም የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዕኩል መጠን የሚጠቅምና የሚያስፈልጋቸው እንጂ ለተወሰኑ ወገኖች ብቻ የቆመ ያለመሆኑን ጥሬ ሀቅ ከማስረገጥ አኳያ ሲታይ ምን ያህል ርቀት መጓዝ እንደተቻለ መተማመን ያሻል ባይ ነኝ፡፡ ለነገሩ በሀገራችን የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ተጨባጭ እውነታ ዙሪያ እቅጩን መነጋገር የህልውና ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን የሚያሳዩ ሌሎች በርካታ የጋራ ችግሮች እንዳሉን የሚያከራክር አይደለም፡፡ ከነዚሁ ከመቸውም ጊዜ በላይ እውነቱን ተነጋግረን ትርጉም ያለው መፍትሔ እንፈልግላቸው ዘንድ ግድ የሚሉ የጋራ ችግሮቻችን መካከል ፤ በተለይም ወቅታዊ ምላሽ ካልተሰጣቸው ሀገራዊ ህልውናችንን ለአሳሳቢ የብተና አደጋ ሊያጋልጡ የሚችሉ ሆኖ የሚሰማኝም ደግሞ፤ የኪታይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መገለጫ ተግባርና አስተሳሰብን የሚያራምዱ ሃይሎችን አምርሮ ከመታገል አኳያ ማሳየት የሚጠበቅን ቁርጠኝት ነው ማለት እችላለሁ ፡፡
በግልፅ አነጋገር፤ የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝት አስተሳሰብ መገለጫ የሆነውን ፅንፈኛ የፖለቲካ አቋም ላይ የሚመሰረት የአመለካከት ወገንተኝነትን እንደዋነኛ መመዘኛ በመውሰድ የሚቧደኑ ሃይሎች፤ ስርዓቱን ለእርሱ ጠባብ ፍላጎት ማስፈፀሚያ ሊያደርጉት ሲሞክሩ የሚስተዋሉበትን አደገኛ አዝማሚያ፤ የምር ታግለን መቀልበስ እንደሚጠበቅብን ትርጉም ያለው የጋራ መግባባት የመፍጠር ጉዳይ ለነገ የማይባል አንገብጋቢ ጥያቄ ስለመሆኑ አምኖ መቀበል ያሻል ማለቴ ነው፡፡ አለበለዚያ ግን፤ ሁሉንም አሳሳቢ የዚች አገር ችግሮች ለመፍታት ሲባል የሚደረግ ጥረት፤ ለህወሐት (ኢህአዴግና ለትግራይ ተወላጆች ብቻ የሚጠቅም ተደርጎ እንዲወሰድና ሌላው ኢትዮጵያዊ የህብረተሰብ ክፍል የመፍትሔ ፍለጋው አካል የመሆንን ተነሳሽነት እንዳያሳይም ጭምር በማድረግ ረገድ፤ አፍራሽ ሚና መጫወት የያዙት ፅንፈኛ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደግሱልንን ፈርጀ ብዙ የጥፋት ድግስ አምክኖ የማስቀረቱን ጉዳይ አዳጋች እንዲሆን የሚያደርጉ ውስብስብ መሰናክሎች መኖራቸው ሳይታለም የተፈታ ጥሬ ሀቅ ነው፡፡
ስለዚህም፤ በእርግጥ እንደሀገር የጋራ ህልውናችን የተመሰረተባቸውን የኢትዮጵያውያን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጠቃሚ የጋራ ዕሴቶች ይበልጥ እያዳበርን በመቀጠል አንድ ጠንካራ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ የመፍጠር ግባችንን ማሳካት ካለብን፤ ኢህአዴግና አጋሮቹ የጀመሩትን የጥልቅ ተሃድሶ መድረክ እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅመን ከመቸውም ጊዜ ይልቅ እውነቱን ልንነጋገርባቸው የሚገባን እጅጉን አንገብጋቢ መፍሔ የሚሹ ተጨባጭ የጋራ ችግሮች ስለመኖራቸው ለመረዳት እንብዛም ዕውቀት የሚጠይቅ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ደግሞ፤ የፌዴራሊዝም ስርዓታችንን አጠቃላይ ይዘት፤ ለትግርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን የበላይት እንደቆመ አድርገው የሚያቀርቡት፤ የትምክህትና ጠባብ ብሔርተኝነት ፖለቲካዊ አመለካት አቀንቃኝ ተቃዋሚ ኃይሎች፤ ከሀገር ቤት እስከ ባህር ማዶ ድረስ በተዘረጋ የፕሮፖጋንዳ መረባቸው አማካኝነት የሚያዛምቱት መርዘኛ ቅስቀሳ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመቋቋም የሚያስችል አስተማማኝ አቅም ይኖረን ዘንድ፤ እኛ ስርነቀል የለውጥ ሂደቱን ለማስቀጠል የምንታገል ወገኖች ከመቸውም ጊዜ በላይ እውነቱን እያነሳን ልንነጋገርባቸው የሚገባን ወሳኝ የጋራ ርዕሰ ጉዳዮች ያሉን ስለመሆናቸው የሚያከራክር አይደለምና ነው፡፡
ስለሆነም፤ እቺን ሀገር የምትመራበትን ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት አክብሮ ማስከበርን ጨምሮ፤ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በህዳሴ ጉዞ ላይ የምትገኝ ሀገር ናት ብለን እንድናምን ባደረገን ፈርጄ ብዙ የልማት ንቅናቄ አስፈላጊነት ዙሪያም ሆነ፤ ሌሎች የጋራ ህልውናችን ፅኑ መሰረት የተጣለበትን ወሳኝ ርዕሰ ጉዳይ የሚመለከቱ የመነጋገሪያ ነጥቦችን እያነሳን የምር መወያየት እንደሚጠበቅብን ነው እኔ በአፅንኦት ለማሳሰብ የምሻው፡፡ ያን ሳናደርግ ቀርተን ከመጋረጃው በስተጀርባ የሚዶለት የጥላቻ ፖለቲከኞች እኩይ ሴራ በሚያሳድረው አሉታዊ ተፅእኖ ምክንያት ሲፈታተነን የሚስተዋለው፤ ህዝቦችን በብሔርና በኃይማኖት ልዩነታቸው ሰበብ ተቃቅረው ዕርስ በርስ ወደሚናቆሩበት አደገኛ አዝማሚያ የመውሰድ ሙከራ የሚሳካበት ሁኔታ ሊፈጠር ቢችል፤ ድምር ውጤቱ ሀገራዊ ህልውናችንን ለከፋ ጥፋት የሚዳርግ አይሆንም ብሎ ማሰብ ተራ የዋህነት ነው ብለን ከወዲሁ መደምደማችን ሟርተኝነት ተደርጎ ሊቆጠር አይገባምና እንግዲህ እኔ ተመራጩን መፍትሔ እነሆ እንዲህ ጠቁሜያለሁ፡፡
መዓሰላማት!