Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ከሁሉም ዜጋ የነቃና የተደራጀ ተሳትፎ የሚጠይቅ አገራዊ አደራ!

0 357

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ከሁሉም ዜጋ የነቃና የተደራጀ ተሳትፎ የሚጠይቅ አገራዊ አደራ!
ጌታቸው ዶዓ
አንድን አገር በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ መስክ ወደተሻለ የእድገት ደረጃና አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ዜጎቿ በሚያደርጉት ርብርብና ጥረት እንደሚወሰን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በኢኮኖሚ አለምን እየመሩ የሚገኙ አገሮችን ታሪክ ብንመለከት እንኳን ለመጣው ለውጥ ዋና ምስጢሩ ዜጎች በቁጭት መንፈስና በተባበረ ክንድ መስራት በመቻላቸው ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን እነዚህ አገሮች የሰው ሀብታቸውን በአግባቡ የመጠቀም ብቃታቸውና ጠንክሮ መስራትን የሥራ ባህላቸው በማድረጋቸውም ጭምር ነው፡፡ በደረጃ እድገት ሳይሆን በብልፅግና እርከን ላይ የደረሱ አገሮች ያመጡት ማህበራዊ ለውጥ በዜጎች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት በማድረግ በኑሮአቸው ላይ መሠረታዊና ዘላቂ የሆነ ለውጥ እንዲመጣ በማድረጋቸው ነው፡፡
ሥራ የሚባለው የተቀደሰና ክቡር ጉዳይ ከሰው ውጪ ስለማይታሰብ፣ ሥራን ለውጥ በሚያመጣ አቅጣጫና መስመር መምራትና ሰውን አብቅቶ ማሰማራት ከድህነት በሽታ / ነቀርሳ / ለመላቀቅ ያስችላል፡፡ መንግስታትም ለዚህ መሳካት ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ጀምሮ ለተግባራዊነቱ እንቅልፍ አጥተው መጨነቅና መስራት አለባቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በእያንዳንዱ አገር የዜጎች ተሳትፎና ተጠቃሚነት አገራት በሚከተሉት ርዕዮተ አለምና ፖሊሲ መሠረት ሊለያይ ይችላል፡፡ ይህ ሲባል አንዳንዶቹ ጥቂት ሀብታሞችን ብቻ የበለጠ ሀብታም (ቱጃር) እያደረጉ የአገሮቹ ኢኮኖሚ በእነዚህ ጥቂቶች እጅ እንዲገባ በማድረግ ደሀውን (ብዙሃኑን) የዳር ተመልካች እንዲሆን በማድረግ የበለጠ ደሀ እንዲሆኑ የሚያደርግ የመንግስት ሥርዓት ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን ነው የሚባለው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በተቃራኒው የሚመጣው ለውጥ ዜጎችን ተሳታፊና ተጠቃሚ ካላደረገ የመኖራቸው ህልውና በአደጋ ላይ እንደወደቀ አድርገው የሚቆጥሩና ለዜጎች መለወጥ ይጠቅማሉ የሚባሉትን የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ፕሮግራሞች እንዲሁም እቅዶች በማውጣት ደፋ ቀና የሚሉ መንግስታት ናቸው፡፡
የትኛውም እድገት ሲመዘገብ በቅድሚያ ያ እድገት የሰውን ልጅ ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ ማድረግና መለወጥ መቻል አለበት፡፡ ዜጎች ካልተጠቀሙና ካልተለወጡ ድህነት አይጠፋም፣ ድህነት ካልጠፋ ሰላም አይኖርም፣ ሰላም ከሌለ ደግሞ እድገትም አይታሰብም፤ የአገር ህልውናም አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም አለም በእያንዳንዱ አገራዊ ጉዳይ ላይ ዜጎች አምነውበት የነቃና የተደራጀ ተሳትፎ ካላደረጉ በስተቀር ምንም ያህል ወርቅ የሆኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ቢቀረጹም ትርጉም የለውም፡፡ ምክንያቱም እያንዳንዱ ዜጋ ከዝግጅቱ ጀምሮ እስከ አፈጻጸሙ ወይም ትግበራው ባለው ደረጃ ወይም ሂደት በሚቀረጸው ፖሊሲና ስትራቴጂ ወይም ፕሮግራም ላይ ተሳትፎ ካላደረገ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣትና ዓላማውንም ለማሳካት በፍፁም አይቻልም፡፡ እነዚህን የተቀረጹ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮግራሞች ውጤታማነት በየጊዜው መገምገምና መፈተሽ የሚሰመርበት ሆኖ ዋናው የመገምገሚያ መለኪያ በሰብአዊ ልማት ወይም በዜጎች ኑሮ ላይ ያመጣው መሠረታዊ ለውጥና ስኬት መሆን አለበት፡፡ የአንድ አገር ዜጎች የሚኮሩባት አገር ሆና የህዝቦቿ አንድነት በጽኑ መሠረት ላይ ሊገነባ የሚችለው ከአገሪቱ እድገትና ከሚመነጨው ኢኮኖሚ ዜጎች በፍትሐዊነት ተጠቃሚ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡
ከዚህ አንጻር በአገራችንም ያለው የመንግስት ሥርዓት እንደሚታወቀው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ነው፡፡ መንግስታችንም ከላይ በስፋት በገለጽኩት አግባብ ከጥሩ መንግስት ወይም ለዜጎች ከሚጨነቅ መንግስት የሚፈለገውን መስፈርት በማሟላት ሁሉንም ዜጋ በየደረጃው ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ መቻል አለበት ባይ ነኝ፡፡ መንግስት የጀመራቸውን ጥሩ ሥራዎች ማስቀጠልና ከህዝቡ የተነሱና የሚነሱ ጥያቄዎችን በአፋጣኝ በመመለስና ክፍተቶችን በመድፈን የህዝቡን ፍላጎት ማርካት ይኖርበታል፡፡ ለዚህም በህዳሴው ግድብ የታየውን አይነት የህዝብ ተሳትፎና የባለቤነት ስሜት እንዲሁም ትልቅ አገራዊ መግባባት እንደተሞክሮ በመውሰድ በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲደረግ ከፍተኛ የሆነ ሥራ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ በተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራም አርሶ አደሩ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እንደ መልካም ተግባር ሊታይ የሚችል በመሆኑ እዚህ አካባቢ ያለውም ተሳትፎና ተጠቃሚነት ወደ ሌሎችም ጉዳዮች መስፋት ያለበት ነው ማለት ይቻላል፡፡
ለዚህም ሁላችንም በሕብረ-ብሔራዊነታችን ደምቀንና በእኩልነት፣ በፍቅር እንዲሁም በአንድነት ተባብረን ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማጥፋት ወይም ለማሸነፍ በእልህና ወኔ ቆርጠን መነሳት ይኖርብናል፡፡ አገራችንን ድሮ ወደነበረችበት ስልጣኔና የእድገት ማማ ወይም ከፍታ ለማሸጋገር አራሹ ገበሬ፣ የመንግስት ሠራተኛው ፣ የፋብሪካ ሠራተኛው ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን አስተባብሮ ክንዱን አጠንክሮ ማምረትና መስራት ይኖርበታል፡፡ አገርንና ራስን ለመለወጥ ልግመኛ መሆን አያስፈልግም፡፡ ይህንን ከልብ ቆርጠን መፈፀም ከቻልን ሁሉም ዜጋ በቀጥታ ወደፊት መራመዱ አይቀርም፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን የቀደምት ታሪካችን እንደሚያሳየው ለሥራ በሥራ የኖርን ሕዝቦች ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን ዋናው ትኩረታችን ያንን የቀድሞውን ታላቅነታችንን ለመመለስ እንደአባቶቻችን ሥራ ወዳዶችና ወኔያሞች በመሆን ዳር እስከ ዳር በጋራ ከተረባረብን ረሃብና ችግር ድንቁርና ከአገራችን ምድር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚወገዱ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያስረዳው ህዝቡ በሥራ የማይደክም ነው፤ ስለዚህ እንዴት መለወጥ ያቅተናል?!
የአገራችን የኢንዱስትሪ ግንኙነት ሰላማዊ ሆኖ የሠራተኛው ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ፣ በሥራ ቦታ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በማህበራዊ ምክክርና ትብብር በመፍታት ኢንቨስትመንትና የሥራ ባህልን ለማሳደግ የሚያስችል ብሔራዊ የሥራ ሥምሪት ፖሊሲ በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ወጥቷል፡፡ ይህ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ለማርካትና ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድልን ለመፍጠር ከፍተኛ ትኩረት የሰጠው ብሔራዊ የሥራ ሥምሪት አገልግሎት የፅሑፌን ዓላማ ለማሳካት /ለማጠናከር/ ወሳኝ ድርሻ ያለው ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ፖሊሲው ከአገራችን ሥራ አጥነትንና ድህነትን አሳድዶ ለማጥፋት የተቀረጸ መሆኑን በጥር 16/2009 ዓ.ም ከታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ መረዳት ችያለሁ፡፡ የወጣቱን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሲባል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶበት በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድም ሌላኛው የፅሑፌ ዓላማ ማጠናከሪያ እቅድ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
የእቅዱና የፖሊሲው መውጣት በራሱ አንድ እርምጃ ወደፊት የተሄደበት ቢሆንም መውጣቱ ብቻ ግን የሚፈይደው አንዳችም ትርጉም የለውም፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ እቅዱን በሙሉ ወደ መሬት ማውረድ መቻሉ ነው፡፡ ለዚህ ተግባራዊነትም ወሳኙና ቁልፉ ጉዳይ ሁሉም አስፈጻሚና ፈጻሚ ወገብን ጠበቅ፣ አንገትን ዝቅ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ለእቅዶቹ ተግባራዊነት በተለይም የሥራ ኃላፊዎች ወይም አስፈጻሚዎች የሚጫወቱት ሚና እጅግ በጣም የላቀ ነው፤ መሪው ጠንካራ ሆኖ በአግባቡ ከመራና ሠራተኛውን ማሰራት ከቻለ በየተቋሙ ለውጥ የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለም፤ ተቋሙ መሪውን ይመስላል ብል ምንም አልተሳሳትኩም፡፡ የእቅዱና የፖሊሲው ውጤት የሚለካው እቅዱና ፖሊሲው በተግባር ተተርጉመው ወደሚፈለገው የህብረተሰብ ክፍል (Target Group) ተደራሽ በማድረግ በኑሮው ላይ የሚታይና መሠረታዊ ለውጥ ሲያመጣ ብቻ ነው፡፡
ከሥራ ባህልና ከጥንካሬ በተቃራኒው ደግሞ አሁን አሁን ልመናን እንደ መደበኛ ሥራ አድርገው የያዙ ዜጎች ቁጥር እያሻቀበ ስለሆነ መኮነንና መወገዝ ያለበት አስነዋሪ ድርጊት ነው፡፡ የማይሰራ አይብላ የተባለው ቁምነገር በአግባቡ መሬት ላይ እንዲወርድ እንደዜጋ ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡ መስራት እየቻለ ለማይሰራው ገንዘብ መስጠት ራሱ ልመናን ማበረታታት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይልቅስ ሥራን እንዲለምድና እንዲሰራ ለማድረግ መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል አለብን፡፡ አሳውን እዲበላ ሁሌ እያዘጋጀን ከመስጠት ይልቅ እንዴት ማጥመጥ ወይም ማዘጋጀት እንዳለበት አሠራሩን ወይም ዘዴውን ማስተማር ይኖርብናል፡፡
ሁላችንም የምንኮራባትና በኢኮኖሚም የበለፀገች አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ በዋናነት መከናወን ያለባቸውን ወሳኝ ጉዳዮች ትንሽ ሰፋ አድርገን ማየቱ በጣም አስፈላጊ ነው ብዬ ስላሰብኩ እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ፡፡
ነጻነቷን ከመጠበቅና ከማስጠበቅ አንጻር
በመጀመሪያ ደረጃ አገር ማለት በሰፊው ሲታይ በውስጡ ያሉ ዜጎች ማለት ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ የሚመጣው ደግሞ ምድሪቷ እንደሆነች ለሁላችንም ግልፅ ነው፡፡ ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንገባ ነጻነት የሚለውን ወሳኝ ቃል ዘርዘር አድርጎ ማየት ጠቃሚ ነው፡፡ ነጻነትን በብዙ መንገድ መተንተን ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከቃሉ ትርጉም ከብዙ በጥቂቱ የጀግና ህዝብ ውጤትና መገለጫ ከሆኑ ጉዳዮች አንጻር ትንሽ ቀንጭበን እንደሚከተለው እናያለን፡፡
ሀ/ የአገርን ሉዓላዊነት የመጠበቅና የማስጠበቅ ጉዳይ፡- የነጻነት ጉዳይ ሲነሳ መጀመሪያ በሁላችን አዕምሮ ውስጥ የሚመጣው የአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የአገር ሉዓላዊነት ስንል የአገሪቷን ዳር ድንበር ከተለያዩ ከውጭም ሆነ ከውስጥ ጠላት የመጠቃት አደጋን በብቃት የመጠበቅና የማስጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው አገራችን ኢትዮጵያ በታሪኳ በየትኛውም ዓይነት በውጭ ወረራ ወይም በቀኝ ግዛት ያልተገዛችና ያልተደፈረች ብሎም ሉዓላዊነቷን ያስጠበቀች ብቸኛ አፍሪካዊት አገር ናት፡፡
ይህ ሉዓላዊነት የተጠበቀው እንዲሁ ሳይሆን ከአብራኳ በወጡ በጠንካራና ጀግና ልጆችዋ አማካኝነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ዓለም በላይ ወኔ ያላቸውና ለሰላም ዘብ የሚቆሙ ዜጎችን ያፈራች አስደናቂ አገር በመሆኗ ለየትኛውም ወራሪ ጠላት እጅ አልሰጠችም፤ ወደፊትም አትሰጥም፡፡ ረጅም እድሜ፣ ሙሉ ጤና፣ ብርታትና ኃይል ለውድ ልጆችዋ ይሰጣቸው፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ የዛሬ 25 ዓመት ኢትዮጵያ በፀረ-ልማት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ተተብትባ ሕዝቦችዋ በፀረ-ዲሞክራሲ አገዛዝ ተሸብሽበው በሰላ ብሔራዊ ቅራኔና በማያባራ ጦርነት እየተናጠች በጠቅላላ ውድቀትና በመበታተን አፋፍ ላይ የደረሰች አገር ነበረች፡፡ እንኳንስና ጠላት ወዳጅም ቢሆን ይህች አገር አልቆላታል ከዛሬ ነገ ትበታተናለች ብሎ በገመተበት ደረጃ ላይ የደረሰች አገር ነበረች፡፡
ያለፉት መንግስታት ያራምዱት በነበረው የአገራዊ ደህንነትና የመከላከያ ፖሊሲ ምክንያት የአገራችን ውስጣዊ ችግሮች እየጨመሩና የአደጋ ተጋላጭነታችን እያደገ ለአገራዊ ደህንነትና ህልውናችን ያላቸው ትርጉም ተገቢውን ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡
ከደርግ ውድቀት በኋላ የአገራዊ ደህንነት እና የመከላከያ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ብሔራዊ ጥቅማችንን የማስጠበቅና አገራዊ ህልውናችንን የማረጋገጥ ተልዕኮ ያለው ሲሆን፣ መሠረታዊ ይዘቱ ሥር-ነቀል የሆነ የአገራዊ ደህንነት ፖሊሲ ላይ የአመለካከት ለውጥ እንዲኖር የሚያደርግ ነው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በብርቱ ልጆችዋ (ዜጎቿ) በአግባቡ ካልተጠበቀች የደህንነቷ ጉዳይ ዋስትና አይኖረውም ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ዜጎቿ በሙሉ ዘብ ሆነው እንዲጠብቋትና ግልፅነት እንዲፈጠር በደህንነት ፖሊሲዋ ላይ የአመለካከት ለውጥ እንዲኖር የሚደረገው፡፡
ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ፖሊሲውም ሆነ ስትራቴጂው በዋነኝነት የሚያጠነጥኑት ህዝቡ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትንና፣ ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን እውን በማድረግና ለዚሁ የተመቻቸ ሁኔታን በመፍጠር ዙሪያ የተመሠረተ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ለኛ ለዜጎቿ ህልውና ቁልፍ የሆኑት ጉዳዮችን ከምንም በላይ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ህገ-መንግስቱ ያስገድዳል፡፡ መሥራትም ይገባዋል፤ አለበትም፡፡
ስለሆነም መንግስት በብሔራዊ ጥቅማችንና በደህንነታችን ላይ የሚቃጡ ማናቸውንም አደጋዎች መቀነስ ብሎም መግታትና መመከት የሚያስችል የመከላከያ ኃይል አደራጅቷል፡፡ ምክንያቱም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተለያዩ ዓላማዎችና ፍላጎቶች ማሳኪያ የውጭ ኃይል ይቅርና ከኛው የወጡም ጭምር የኢትዮጵያን ሰላምና እድገት ለማወክና ለመበጥበጥ የተለያዩ እኩይ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ስለሆነ ህብረተሠቡን ባሳተፈና ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ መንግስት ኃይሉንና አቅሙን ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር አለበት፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ እንዳሉት #ጫፍ የረገጡ አክራሪዎች እንቅስቃሴ በእንጭጩ መቀጨት አለበት፡፡;
ለ/ የኢኮኖሚ ነጻነት ጉዳይ፡- የአንድ አገር የነጻነት ጉዳይ ሲነሳ የኢኮኖሚ ጉዳይ አብሮ መነሳቱ የማይቀር ነው፡፡ የአንድ አገር የኢኮኖሚ አቅም ከሌለ ወይም ካልዳበረ ሉዓላዊነቷ በቀላሉ እንደሚደፈርና ለውጭም ሆነ ለውስጥ ኃይሎች በቀላሉ እጅ እንደሚሰጥና በእነሱ እንደሚጠቃም ጥርጥር የለውም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የአንድ አገር የኢኮኖሚ አቅም በየጊዜው ካልዳበረና ካላደገ የተለያዩ ለጋሽና አበዳሪ ድርጅቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የራሳቸውን ድብቅ ዓላማና ፍላጎት ለማሳካት እንደሚሰሩና ከፍተኛ የሆነ ጫናና ተፅእኖ እንደሚያሳድሩ እሙን ነው፡፡
ስለዚህ የኢኮኖሚ ነጻነታችንን ለማስጠበቅና ለማስከበር ሁላችንም ለልማትና ለሥራ በቁጭትና በእልህ በመነሳሳትና በተባበረ ክንድ ኢኮኖሚያችንን በበለጠና በላቀ ሁኔታ ማሳደግ እንችላለን፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ አገራችን ያላት ውድና ትልቁ ሀብት የሰው ጉልበትና መሬት (ያልተነካና አገራችንን ሊያሳድጋት የሚችል የተፈጥሮ ሀብት ክምችት የያዙ) ናቸው፡፡
ከዚህም አንጻር አንድ አገር አደገ ማለት የሚቻለው የእያንዳንዱ ዜጋ ኑሮና የገቢ ደረጃ ሲያድግ ሲሆን፣ ይህም እድገት የሚመጣው አገሪቷ ያላት ሀብት ማለትም የሰው ኃይል በሙሉ አቅሙ በልማቱና በሥራው ላይ ሲዘምቱና ሲረባረቡ ብቻና ብቻ ነው ፤ እንጂ በሌላ ታዓምር አይደለም፡፡ ከሰው ጉልበት አንዱ እኔ ነኝ ፤ስለዚህ እኔ በተሰማራሁበት የሥራ መስክ ወይም ሌላ ሥራ ፈጥሬ በርትቼ ካልሰራሁ እንዴት እለወጣለሁ? በመርህ ደረጃ የእኔን ሕይወት ለመለወጥ የሚሰራ ሰው ወይም አካል ሊኖር ይችላል ብለው ያስባሉ? በፍጹም ሊኖርም ሊሆንም አይችልም፡፡ እኔ ነኝ በሥራዬ ተለውጬ አገሬንም መለወጥ ያለብኝ፡፡ ሁሉም ሰው እንደዚህ ብሎ ካልተነሳ የሚመጣ ለውጥም ሆነ እድገት አይኖርም፡፡
ቻይናን እንደ ምሳሌ ወስደን ብናይ የዓለምን ግማሽ ያህል ህዝብ ነው ያላት፡፡ ነገር ግን ያ ሁሉ ህዝብ የማይሰራ ቢሆንና ምርታማ ባይሆን ኖሮ ቻይና ዛሬ በደረሰችበት የእድገት ደረጃ ላይ አትደርስም ነበር፡፡ ዓለምንም በኢኮኖሚዋ መቆጣጠር አትችልም ነበር፡፡ ስለዚህ ሁላችንም የሥራ ባህላችንን ከቀየርንና ሁሉም ሰው ሥራን ሳይመርጥና ሳይንቅ ከሰራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ቻይና የማንሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡
ሁላችንም እንደምናውቀው ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በደርግ ዘመን የነበሩት ፀረ-ልማት ፖሊሲዎች ተሽረው በነፃ ገበያ የኢኮኖሚ መርህ ላይ የተመሰረቱ የተስተካከሉ የልማት ፖሊሲዎች ተቀርፀው ተግባራዊ በመሆን ላይ ናቸው፡፡ ከእዝ ኢኮኖሚ ወደ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሽግግር ከተካሄደባቸው ከብዙ አገሮች በተለየ አኳኋን በአገራችን የተደረገው ሽግግር በጊዚያዊነትም ቢሆን ኢኮኖሚውን ይበልጥ በሚያዳክምና ቀውሱን በሚያባብስ አኳኋን የተፈጸመ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ለውጡ አገራችን ከዚህ ጊዜ በፊት ባልታየ ደረጃ የኢኮኖሚ እድገት በምታስመዘግብበት አኳኋን የተፈጸመ ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ከተገኘው አጥጋቢ እድገት ባሻገርም የአገራችንን ፈጣን እድገት ከማረጋገጥ አኳያ ሰፊ ልምድ ተካብቷል፡፡ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ሀሳብ አመንጭነት፣ አፍላቂነት ብሎም ቀያሽነትና መሃንዲስነት ከዚያም በላይ በእሳቸው መስዋዕትነት ለቀጣዩ እድገታችን ምቹ መደላድል ተፈጥሯል፡፡ በመሆኑም በኢኮኖሚው መስክ አበይት ድሎችን ተቀዳጅተናል፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ አገራቸውን ኢትዮጵያን የሚያኮሩ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውነውና ኢኮኖሚያዊ ነጻነቷንም አስጠብቀው አልፈዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያም ህዝቦችዋም ከልብ አልቅሰዋል፤አዝነዋል፡፡ እኛስ ለአገራችን ምን አደረግንላት? ዛሬም ሆነ ነገ ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡ ካልሰራን ሕሊናችንም ይወቅሰናል፤ ታሪክም ይወቅሰናል፡፡ ለወደፊትስ ከዛሬ ጀምሮ የሚሰራ ሆኖ ከታላቁ መሪያችን ትምህርትና ተሞክሮ ወስደን ምን ለመሥራት አቅደናል?! ካቀድነው ውስጥስ ምን ያህሉን አከናውነናል? ምክንያቱም የአገራችን የኢኮኖሚ ልማት ዓላማ የዓላማዎች ሁሉ መሠረትና ምሰሶ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ዜጋ በተሰማራበት የስራ መስክ በአንድነት በርትቶና ጠንክሮ ካልሰራ ይህ የተቀደሰና የጋራ የሆነው አላማችን ሊሳካ አይችልም፡፡
ሐ/ የሐይማኖት ነጻነት ጉዳይ፡- በአንድ አገር ላይ የሐይማኖት ነጻነት ከሌለ እንደ አገር ጸንቶ በሰላም የመኖር ጉዳይ በአደጋ ላይ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት በተደነገገው መሠረት መንግስትና ሃይማኖት ተለያይተው በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሃይማኖቶች ሁሉ ካለአንዳች ልዩነት የእምነት ነፃነትና እኩልነት እንዲረጋገጥ ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን የበለጠ ለማጠናከርና ሰላማችንንም ዘላቂ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ማንኛውም ዜጋ የራሱን ሃይማኖት እንደጠበቀ ሁሉ የሌላውንም አክብሮ አብሮ የመኖር አስደናቂ እሴታችንን ጠብቀን ማስቀጠል መቻል አለብን፡፡ እንደ አገር ጥንካሬ የሚኖረንም አብረን ተባብረንና ተቻችለን መኖር ስንችል ብቻ ነው፡፡ ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ነው መልእክቱ፡፡ የየራሳችንን ሃይማኖት ጠብቀን ከያዝን በኋላ የሌላውን ማክበር የስልጣኔ ምልክትም ጭምር ነው፡፡ እንደ ትናንቱ ሁሉ በእኩልነትና በፍቅር መንፈስ አብረን እንድንኖርና በጋራ ሰርተን በጋራ እንድንበለፅግ ሌላውን ሁሉ አክብረንና በልዩነት ውስጥ ባለው ልዩ ውበት ደምቀን ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ትልቅ ማንነታችንና ኩራታችንን ከመቼውም ጊዜ በላቀ ትኩረትና በበለጠ ማጠናከር ይኖርብናል፡፡ አቅም ፈጥረን ያቀድናቸውን እቅዶች ማሳካትና ሁሉንም ነገር ማሸነፍ ምንችለው ያ ሲሆን ብቻ ነው፡፡
የአገሪቱ የልማት እንቅስቃሴ ዋና አላማ የዜጎችን እድገትና መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ነው፤ ለዚህ ደግሞ ሁሉም አቅሙ የሚችለውንና የፈቀደውን ሁሉ በማድረግ አስተዋፅኦ የማበርከት አገራዊና ዜግነታዊ ኃላፊነትና ግዴታ አለበት!!
ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን!!! ሰላም፣ ጤናና ብልፅግና ለእናንተ ይሁን!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy