Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

ካልበረቱ አይታይም ምርቱ! አለች…

0 319

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

ካልበረቱ አይታይም ምርቱ!   አለች…

አባ መላኩ

“ወገብ  የሚያጎብጡ  ዕቅዶቻችንን በመተግበር አንገታችንን ቀና እናደርጋለን” ታላቁ መሪ  በአንድ ወቅት ካደረጉት ንግግር የተወሰደች ናት። ለእኔ ድንቅ አባባል ነች። የዛሬው አነሳሴ አገራችን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዙሪያ ትኩረት የተደረገባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አንዳንድ ነገሮች ለማንሳት ያክል ነው።

 

አገራችን ከድህነትና ኋላቀርነት ለመላቀቅ  ዘርፈ ብዙ ዕቅዶችን  በማዘጋጀት ለተግባራዊነታቸው በመረባረብ ላይ ነች። ህዝብና መንግስት ተቀራርቦ መስራት ከቻለ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችል ኢትዮጵያ ጥሩ ማሳያ ናት። ይህን ያልኩት አገራችን እዚህ ግባ የሚባል የተፈጥሮ ሃብት ሳይኖራት በዓለም ፋጣን ዕድገት ማስመዝገብ የቻለችው መንግስት ህብረተሰቡን በየመስኩ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ሁኔታዎችን በማመቻቸቱ ነው። ለዚህ ነው በርከታ ምሁራን የኢትዮጵያ ዕድገት የፖሊሲና ስትራቴጂ ውጤት ነው የሚሉት።    

 

በመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይፋ በተደረገበት ወቅት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ የልማት አጋር መንግስታትና ድርጅቶች እንዲሁም   በርካታ ምሁራን ኢትዮጵያ እንዲህ ያለውን ዕቅድ መተገባር አትችልም የሚል አስተሳሰብ ሲያራምዱ ነበር። በእርግጥ እንዲህ ያለ አቋም ቢፈጠርባቸው የሚገርም አልነበረም። ምክንያቱም ዕቅዱ እጅግ የተለጠጠ ከመሆኑ ባሻገር አገራችን እንዲህ ያለ ዕቅድ የመፈጸም ልምድም አልነበራትም። በዕቅዱ ውስጥ የተካተቱት አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ  ልምድ የሚጠይቁና ዳጎስ ያለ  የፋይናንስ ወጪ ያውም በውጭ ምንዛሬ የሚፈልጉ ነበሩ።  

 

ይሁንና ለዕቅዱ አፈጻጸም መንግስት ህብረተሰቡን አስተባብሮ መስራት በመቻሉ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አጠቃላይ አፈጻጸም ስኬታማ መሆን ተችሏል። የአገሪቱ  ኢኮኖሚው በየዓመቱ በአማካይ በ10.1 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡

 

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በተለያዩ መንግስታት ዓለም አቀፍ ተቋማት እውቅና የተቸረው ነው።  ይህ የአገራችን ዕድገት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ከመሆኑ ባሻገር በሁሉም ዘርፎች ዕድገት የተመዘገበ በመሆኑ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል በየደረጃው ተጠቃሚ ያደረገ ሆኗል። በዚህም የአርሶና የአርብቶ አደሩና የከተማው ህዝብ የኑሮ ደረጃ እጅጉን መቀየር ተችሏል።  የአገራችን የድህነት መጠንም ከግማሽ በላይ መቀነስ ተችሏል። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በተከታታይ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት የዓለም አገራት  መካከል በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀስ  አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ በመሆኑም  የአገራችን  ገፅታ  በመሠረቱ እየተቀየረ  እንደመጣ መረዳት ይቻላል። የአገራችን ፈጣን ዕድገት በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን የፖሊሲዎቻችንና የስትራቴጂዎቻችን ውጤት ነው።

 

መንግስት የመጀመሪያውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም በአግባብ ከገመገመ ብኋላ  ቀጣዩን ማለትም የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አዘጋጅቶ በመተግበር ላይ ይገኛል።  በዚህ ዕቅድ ልዩ የትኩረት  መስኮች ተደርገው ከተለዩት ውስጥ  የመጀመሪያው የግብርናው ዘርፍ ማሳደግ የሚል ነው። የግብርናውን  ዘርፍ  ማዘመን ለአገራችን ፈጣን ዕድገት የማይተካ ሚና እንዳለው መንግስት በመገንዘቡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።

 

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎረሜሽን እቅድ መጀመሪያ ማለትም በ2003 ዓ.ም  ላይ ግብርናው ከአጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከ41 በመቶ በላይ  የነበረው ድርሻ በዕቅዱ ዘመን ማብቂያ ማለትም በ2007 ማብቂያ ላይ  ወደ 38 በመቶ ገደማ እየወረደ መምጣቱ የመንግስት ፖሊሲ ስኬታማ መሆኑን ያሳያል። ይሁንና መንግስት በአምስት ዓመት ውስጥ ሶስት በመቶ ብቻ ነው የቀነሰው በማለት የመንግስት ፖሊሲ ውጤታማነት ላይ ክርክር ለማንሳት ይዳዳቸዋል።

ይሁንና ግብርናው በአገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ  ሰፊ መሰረት ያለው እጅግ በርካታውን የሰራተኛ ሃይል የያዘ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ላይ የሚከሰት ትንሽ  ለውጥ በአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ ላይ ትልቅ ልዩነት የሚያመጣ መሆኑን ካለመገንዘብ የሚከሰት ነው።  አሁንም ይህ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ እጅግ ወሳኝ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ዕድገት ለማምጣት መንግስት ጠንክሮ በመስራቱ በዘንድሮው የመኸር ምርት ብቻ በዋና ዋና ሰብሎች  ከ50 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ተጭማሪ ምርት በማስመዝገብ ከ320 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰብ ተችሏል።

 

መንግስት የአገሪቱ በምግብ ሰብል ራሷን እንድትችል እያደረገ ያለው ጥረት ተሳክቷል። ይህን ስኬት በቤተሰብ ደረጃ  ማውረድ ላይ ግን አሁንም መከናወን ያለባቸው ስራዎች አሉ። በአገራችን በቤተሰብ ደረጃ  በምግብ ሰብል ማረጋገጥ እንዲቻል መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል። በዚህም በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ ምርት ማግኘት ተችሏል። በቀጣይም መንግስትና ህዝብ ተቀራርበው መስራት የሚችሉ ከሆነ የአገራችን  የግብርና አቅም ከፍተኛ በመሆኑ ውጤቱ ከዚህም በላይ ማሳደግ ይቻላል። ግብርናን ተከታታይ ዕድገት በማስመዝገቡ  ከምግብ ሰብሎች ምርት መጨመር  ባሻገር አርሶ አደሩ የገበያ ምርቶች (ካሽ ክሮፕ) በማምረት የበለጠ ተጣቃሚ መሆን ችሏል።  

 

ሌላው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ትኩረት የተሰጠው ዘርፍ  የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ነው።  የዚህ ዘርፍ መስፋፋት አገራችን ከግብርና ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር እንድትሸጋገር  የሚያግዛት መሆኑ መንግስት በመረዳት ግብርናውንና ኢንዱስትሪውን ለማስተሳሰር በርካታ ተግባራትን በማከናውን ላይ ይገኛል። አርሶና አርብቶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና ስርዓትን እንዲከተሉ በመደረጉ ገበያ ተኮር ምርቶችን በማምረት እንዲሁም የግብርና ምርቶች ላይ እሴት ጨምረው ለገበያ ማቅረብ የሚችሉ ውስብስብ ቴክኖሎጂንና ከፍተኛ ፋይናንስ የማይጠይቁ ቀላል ኢንዱስትሪዎች  እንዲስፋፉ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ነው።

 

ከዚህ ባሻገር መንግስት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ በራሱ ወጪ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ላይ ይገኛል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት በአገሪቱ  ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ አዎንታዊ ለውጦችን የሚያመጡ ይገኛሉ። የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባት ባለሃብቱን የለምንም ውጣ ውረድ ወደ ምርት እንዲሸጋገር አግዘዋል፤ ለዜጎች ከፍተኛ የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፣ የአገሪቱን የወጪ ምርቶች በዓይነት፣ ብዛትና ጥራት በማሳደጋቸው የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ለመሆን በቅተዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ግንባታ የወቅቱን ቴክኖሎጂ የተከተሉ በመሆናቸው ከአካባቢ ብክለት ነጻ ናቸው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ መንግስት ትልቅ ትኩረት የሰጠው አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን  ከኢንዱስትሪው ጋር እንዲተሳሰሩ  በያዘው እቅድ መሰረት  በርካታ ዜጎች  የስራ እድል እየተፈጠረላቸው ይገኛል።    

 

ሌላው በዕቅዱ ትኩረት የተደረገበት መስክ ቁጠባን  ማሳደግና   ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ነው። የኢንቨስትመንትን በተለይ የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ሊስፋፋ የሚችለው ዜጎች አገራዊ ቁጠበን ማጠናከር ሲችሉ ብቻ ነው። በመሆኑም መንግስት አገራዊ ቁጠባን ለማሳደግ የተለያዩ ማበረታቻዎችን  በማድረግ ላይ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዕቅዱ ላይ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ በወጪና በገቢ ንግድ መካከል ያለው ክፍተት ማጥበብ ነው። መንግስት  የገቢና የወጪ  የንግድ ሚዛኑን ለመጠበቅ በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። ለአብነት የወጪ ምርቶችን በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት ማሳደግ  እንዲሁም የገቢ  ምርቶችን የሚተኩ ምርቶች በአገር ውስጥ ማምረት ላይ የመንግስት ዋንኛ የትኩረት መስክ ሆኗል።

 

ሌላው በዕቅዱ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን  ልማትና ፕሮጀክቶች ማኔጅመንት አቅምን ማጎልበት  ነው።  በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በተለይ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን /የግድቦች ግንባታ፣ የመንገድ ግንባታ፣ የመስኖ ግንባታ ወዘተ/ ማስፋፋት እንዲሁም የማስተዳደርና የመምራት አቅምን ለማሳደግ መንግስት በዘርፉ ለተሰማሩ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ነው። የከተሞች መስፋፋትን ከኢንዱስትራላይዜሽን እንቅስቃሴ ጋር ለማጣጣም  የተሰጠው ትኩረትም ውጤታማ ሆነዋል። የተቀናጀ የከተማ ልማት በሁሉም የአገሪቱ ክፍል እንዲኖር መንግስት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል።    

 

ሌላው በዕቅዱ ላይ ልዩ  ትኩረት የተሰጠው  የሰው ኃብት ልማቱን በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ እንዲደገፍ ማድረግ ነው። በዚህ ረገድ ዋናው ጉዳይ የትምህርትና ጤና አገልግሎትን ተደራሽነት እና ጥራትን ከማሳደግ አኳያ ትልቅ ስኬት በመመዝገብ ላይ ነው። በአገሪቱ የትምህርትና የጤና መሰረተ ልማት በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋታቸው ለቴክኖሎጂ አጠቃቀም ቅርብ የሆነ ማህበረሰብ በመፈጠር ላይ ነው።  የትምህርትና የጤና አሰጣጥ ጥራትን ለማሳደግ  መንግስት ጠንክሮ በመስራት ላይ ነው። በዚህም ተጨባጭ ለውጦች በመመዝገብ ላይ ናቸው።

 

በዕቅዱ ሌላው ትኩረት የተደረገው የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ናቸው።  በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂን በማዘጋጀትና በመተግበር ግንባር ቀደም አገር ለመሆን በቅታለች፡፡  ከዚህ አንፃር የአካባቢ ሙቀት ሳቢ ጋዞችን ልቀት መቀነስ የሚያስችሉ የደን  ማልማት ማስፋፋትና የተፋሰስ ልማት እንዲሁም  ከታዳሽ ኃይል ምንጭ የኤሌክትሪክ ኃይል በሰፊው ማመንጨትና ዘመናዊና ኃይል ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት የዕቅዱ  አካል ናቸው። በዚህ ረገድ አገራችን ውጤት ማስመዝገብ  የተቻለበት ዘርፍ ነው። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ትክረት የተደረገባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለማንሳት ሞክሬለሁ። በቀጣይ በዕቅዱ ላይ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን  በተመለከተ የተጠቀሱትን ጉዳዮች  ለማንሳት ሞክራለሁ። ቸር እንሰንብት!

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy