NEWS

ክልሎቹ በጋራ ለተስማሙት የወሰን ማካለል ስራ ተግባራዊነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ገለጹ

By Admin

April 21, 2017

የኢትዮጵያ ሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች በጋራ ለተስማሙት  የወሰን ማካለል ስራ ተግባራዊነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት እነዚህ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ስምምነቱን እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡

ገራድ ኮልሚዬ ገራድ መሀመድ የተባሉት የሀገር ሽማግሌ እንደገለጹት ስምምነቱ በሁለቱ ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች፣ ቀበሌዎችና መንደሮች የነበረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትያስችላል፡፡

በተጨማሪም  ስምምነቱ የሁለቱ አጎራባች አካባቢዎች ወንድማማች  ህዝቦችን በጋራ የመኖርና የማልማት የቆየ ባህላቸውን በጋራ እንዲጠበቅ የሚስችል በመሆኑ እንደሚደግፉትም አመልክተዋል፡፡

እንደ ሀገር ሽማግሌ ከሁለቱም መንግስታት ጋራ በመተባበር ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን  ገልጸዋል፡፡

“በሁለቱ መንግስታት የተደረሰው ስምምነት በወሰን አካባቢዎች የነበረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መሰረት ይሆናል “ያሉት ደግሞ ሼክ አብዲራህማን አሊ ናቸው፡፡

ከአስተዳደር ወሰን ጋር ተያይዞ በአካባቢዎቹ የተከሰተውን ግጭት ለመፍታትና ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት ለእምነቱ ተከታዮች ስለ ሰላም ጠቀሜታ ለማስተማር እንደሚሰሩም ጠቅሰዋል፡፡

ሱልጣን አብዲ አደን በበኩላቸው አጎረባች የሆኑ የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች የጋራ ባህል፣ ቋንቋና እምነት የሚጋሩ በመሆናቸው ስምምነቱን ለመተግበር የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ክልሎች ባደረጉት ስምምነት መሰረት በሰባት ዞኖች 33 ወረዳዎች ሥር በሚገኙ 147 ቀበሌዎችና መንደሮች መካከል አስተዳደራዊ ወሰን እንደሚካለል ቀደም ብሎ ተገልጿል፡፡