ክቡር አምባሳደር ግርማ ብሩ በዩኤስ ኮንግረስ የኒውጀርሲ 4ኛ ዲስትሪክት ተወካይ ከሆኑት ሚ/ር ክሪስ ስሚዝ ጋር እ.ኤ.አ. ኤፕሪል 25/2017 ዓ.ም በጽ/ቤታቸው ውይይት አካሂደዋል። በውይይታቸውም ኮንግረስማን ክሪስ ስሚዝ በአገራችን ይስተዋላሉ የሚሏቸውን የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮች ዙሪያ ስለሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት፣ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ለማሻሻል ስለሚከናወኑ ተግባራት፣ በመንግስትና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተወሰዱ ስለሚገኙ አበረታች ተግባራት በሰፊው ምክክር አድርገዋል። በዚህ ወቅት ክቡር አምባሳደር ግርማ ኮንግረስማኑ በኢትዮጵያ ይስተዋላሉ የሚሏቸውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ጉድለቶች በሚመለከት በመረጃ ምንጭነት የሚጠቀሙት የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ነን ባይ ድርጅቶች የራሳቸው የሆነ የፖለቲካ ዓላማ (Motives) ያሏቸው በመሆኑ በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ ትክክለኛ ገጽታ ማግኘት የማይችሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ እውነተኛውን መረጃ ለማግኘት እንዲችሉና በቀጣይም ከመንግስትና ከሚመለከታቸው አካላት በጋራ ለመስራት እንዲችሉ ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ጉብኝት እንዲያደርጉ ጋብዘዋል። ኮንግረስማን ክሪስ ስሚዝ Kአምባሳደር ግርማ ብሩ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው፤ በተለያዩ አገራት በተለይም በአፍሪካ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ተያያዥ የሰብዓዊ መብቶች ችግሮች ለመፍታት በጋራ ለመስራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን፣ የአገራችን አየር መንገድ በተለያዩ የዓለም አገራት ካለው ሰፊ ተደራሽነት አንጻር በአሜሪካ ከተቋቋመው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ለመግታት ከሚሰራ ድርጅት በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸትና የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለመመካከር እንዲችሉ የድረጅቱን የሥራ ኃላፊ ወደ ኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት አብረው እንደሚያካትቱ ኮንግረስማኑ ገልጸዋል። በመጨረሻም ኮንሬስማን ክሪስ ስሚዝ ከክቡር አምባሳደር ግርማና ጋር በቅርብ ለመሥራት ያላቸውን ፍላጎት የገለፁ ሲሆን፣ አምባሳደር ግርማ የተደረገው ውይይት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን ከአስረዱ በኋላ ምክከሩን በመደበኛነት ለማድረግ መግባባት ላይ ተደርሷል።