የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያጋልጠውን የግዥ ስርዓት እንዲያስተካክል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።
የምክር ቤቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮርፖሬሽኑን የ2009 በጀት ዓመት የስምንት ወራት እቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።
ቋሚ ኮሚቴው በግምገማው የኮርፖሬሽኑ የግዥ ስርዓት ለመልካም አስተዳደር ችግርና ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያጋልጥ እንዲሁም ያልታቀዱና አስቸኳይ ግዥዎች በብዛት የታዩበት እንደነበር አንስቷል።
ተቋሙ በኮንስትራክሽን ዘርፉ አገሪቱን ወደ ለውጥ ጎዳና ለማድረስ እያሳየ ያለው ጅማሮ አበረታች ቢሆንም ያልታቀዱና አስቸኳይ ግዥዎች መብዛት በመልካም አስተዳደር ስራዎችና በኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ ላይ የጎላ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ተነግሯል።
ኮርፖሬሽኑ በህግና ደንብ መሰረት ግልፅ ጨረታ በማውጣት ግዥ እንዲፈፅምና ለኪራይ ሰብሳቢነት የሚያጋልጠውን የቀጥታ ግዥ እንዲቀንስ ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።
በሜጋ ፕሮጀክቶች ግንባታ የሚታዩበትን መጓተቶችና የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች ለይቶ መፍትሄ በመስጠት ረገድ ኮርፖሬሽኑ የሄደበትን ርቀት በሪፖርቱ አለማካተቱንም በድክመት ገምግሟል።
ተቋሙ ወደ ስራ ከገባ አጭር ጊዜ ቢሆነውም የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማሳደግ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴና የተቋሙን ሰራተኞች አቅም ለማጎልበት ያከናወናቸውን ተግባራት ደግሞ በጥንካሬ ገልጿቸዋል።
የኮርፖሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ኃይለመስቀል ተፈራ የተቋሙ አሰራር አገሪቱ ከምትጠቀመው የግዥ ስርዓት ጋር የተናበበ ነው ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ የግዥ ስርዓቱ ፍትሃዊ እንዲሆንና የመንግስትን ንብረት በአግባቡና ለታለመለት ዓላማ ለመጠቀም ደንብና መመሪያ ተዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑንና ክትትልም እንደሚደረግ አብራርተዋል።
ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ አስተያየቶችን በመውሰድ እናስተካክላለን ሲሉም አክለዋል።
ኮርፖሬሽኑ የመንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን፣ የውሃ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅትና የተገጣጣሚ ህንፃ አካላት ማምረቻ ድርጅት ኮርፖሬሽንን በማጣመር በ2009 ዓ.ም መስከረም በአዲስ መልክ የተቋቋመ ነው።