ወደሃገር ቤት/ብ. ነጋሽ
የሳኡዲ አራቢያ መንግስት በሃገሩ በህገወጥ መንገድ የሚኖሩ የሌሎች ሃገራት ዜጎች ከመጋቢት 20፣ 2009 ዓ/ም ጀምሮ በ90 ቀናት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ አውጇል። በሳኡዲ አረቢያ በብዙ ሚሊየን ሚሊየን የሚቆጠሩ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች ይኖራሉ። 33 ሚሊየን ከሚሆነው ያሀገሪቱ ህዝብ ከ32 በመቶ በላይ የሚሆኑት ስደተኞች ናቸው። በስራ ላይ ከተሰማራውን የሃገሪቱ የሰው ሃይል 56 በመቶ በውጭ ሃገራት ዜጎች የተያዘ ነው። የግሉ ዘርፍ የሰው ሃይል ደግሞ 89 በመቶ በውጭ ሃገራት ዜጎች የተያዘ ነው።
ሳኡዲ አራቢያ በሌሎች ሃገራት ዜጎች የሰው ሃይል መጥለቅለቅ የጀመረችው እነደአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1930ዎቹ ጀምሮ ነው። ይህ ዘመን በሳኡዲ አረቢያ የነዳጅ ፍለጋ የተጀመረበት ነው። ይህ ሁኔታ በተለይ ከአካባቢው የአረብ ሃገራትና ከደቡብ ኢሲያ የሳበው ከፍተኛ የሰው ሃይለ በተለይ የሃገሪቱን ያልሰለጠነ የሰው ሃይል የስራ እድል ስለተሻማ በ1950ዎቹ በባእዳን ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር። ይሁን እንጂ ከ1970ዎቹ መጀመሪያ በኋላ የሳኡዲ አራቢያ ነዳጅ በገፍ መመረት ሲጀምር በተለይ የህንጻና የመሰረተ ልማት ግንባታ በከፍተኛ መጠን በማደጉ የውጭ ሃገር የሰው ሃይል ፍላጎቱ ጨምሮ በባእዳን ሰራተኞች ላይ የበረውን ተቃውሞ አበረደው። ከዚህ በኋላ ሳኡዲ አራቢያ በሰለጠነና ባልሰለጠነ የውጭ ሃገር ዜጎች ተጥለቅልቃለች። ኢትዮጵያውያንም በተለይ በቤት ሰራተኝነትና መሰል ስራዎች ላይ ለመሰማራት ከ1980ዎቹ ጀምረው ወደሳኡዲ አረቢያ መጓዝ መጀመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ሳኡዲ አረቢያ በህጋዊ መንገድ ገብተው ከሚሰሩት ያልተናነሰ ህገወጥ ስደተኞች መናኸሪያም በመሆኗ ትታወቃለች።
ይሁን እንጂ ከ2000 ዓ/ም በኋላ በሃምሳ ዓመታት ውስጥ ከአስር እጥፍ በላይ ያደገው የሳኡዲ አረቢያ ዜጎች የህዝብ ቁጥር የስራ እድል ጠያቂ ዜጎችን ፈጠረ። የውጭ ሃገር ዜጎችን በስራ እድል ተሻሚነት መመልከትም ተጀመረ። ይሄኔ የሳኡዲ አራቢያ መንግስት ኒትቃት የተሰኘ በስራ ላይ የተሰማራውን የሰው ሃይል በዜጎች የመሙላት ፖሊሲ አወጣ። ይህ ሁኔታ በተለይ በ2011 በተለያዩ የአረብ ሃገራት ከተቀሰቀሰው የአረብ ጸደይ ወይም የአረብ አብዮት ጋር ተያይዞ የሳኡዲ አራቢያ መንግስት የውጭ ሃገር ዜጎችን በተለይ በህገወጥ መንገድ የገቡትን ለማባረር እንዲወስን አደረገ። በዚህ እርምጃ ከአራት ዓመት በፊት ማለትም እ ኤ አ በ2013/14 ከግማሽ ሚሊየን በላይ የተለያየ ሃገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ከሳኡዲ አራቢያ እነዲወጡ ተደርጓል። ታዲያ በዚህ ወቅት አስር ሺህ ገደማ በሳኡዲ አረቢያ በህገወጥ መንገድ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያንም መባረራቸው ይታወሳል።
በዚህ ወቅት የኢፌዴሪ መንግስት የሳኡዲ አራቢያ መንግስት ህገወጥ ኢትዮጵያውን ከሃገሩ እንዲወጡ ያስቀመጠው የግዜ ገደብ ከመጠናቀቁና ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ከመጀመሩ በፊት ዜጎቹን በሰላም ለማስወጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጓል። ይሁን እንጂ የግዜ ገደቡ ከማለቁ በፊት ማስወጣት የቻለው በጥቂት መቶዎች የሚቆጠሩትን ብቻ ነበር። የኢፌዴሪ መንግስት የሳኡዲ አራቢያ መንግስት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ዜጎቹን በሙሉ ለማሰወጣት ያደረገው ጥረት በተፈለገው መልኩ ሳይሳካ ቀነ ገደቡ አልፎ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት ህግን የማስከበር እርምጃ ሲወስድ በግርግር በኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ እንግልት መደረሱማ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ የኢፌዴሪ መንግስት የልኡካን ቡድን ወደሳኡዲ አረቢያ በመላክ በዚያ የሚኖሩ ዜጎቹን ወደሃገሩ የመላክ የዘመቻ ስራ ማከናወኑም የታወሳል። የኢፌዴሪ መንግስት ከዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ጋር በመቀናጀት በአጭር ግዜ ውስጥ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቹን ወደሃገሩ አጓጉዟል። በአጭር ግዜ ውስጥ በተካሄደ ዘመቻ ወደሃገራቸው የተመለሱ ዜጎችን ተቀብሎ የማስተናገድ ስራ ከፍተኛ ወጪና የሰው ሃይል የሚጠይቅ ነበር። ወደሃገራቸው የተመለሱትን ዜጎች ተቀብሎ ወደየመኖሪያቸው የማጓጋዙ ስራ በበጎ ፍቃደኛ ኢትዮጵያውያንና ለጋሾች ትብብር ነበር የተከናወነው። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የነበረውን ሁኔታ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሚያውቀው በዝርዝር ማስታወስ አልፈልግም።
እንግዲህ የሳኡዲ አራቢያ መንግስት በጽሁፉ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው ከመጋቢት 20፣ 2009 ዓ/ም ጀምሮ በዘጠና ቀናት ውስጥ በሃገሩ የሚኖሩ ዜጎች እንዲወጡ አውጇል። ይህ በህገወጥነት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንንም ይመለከታል። የኢፌዴሪ መንግስት በህገወጥ መንገድ በሳኡዲ አራቢያ የሚኖሩ ዜጎቹን በሰላም ወደሃገራቸው ለመመለስ እንቅስቃሴ ጀምሯል። በዚያ በህገወጥ መንገድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከአራት ዓመት በፊት ያጋጠመውን በማስታወስ በሰላም ወደሃገራቸው መመለሳቸው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ምኞት ነው።
የሳኡዲ አራቢያ መንግስት ያወጣው አዋጅ፣ በህገ ወጥ መንገድ ድንበር አቋርጠው የገቡ ስደተኞችን፣ ቋሚ ቦታ ሳይኖራቸው በመዘዋወር በህገ ወጥ መንገድ የሚሰሩ ስደተኞችን፣ የስራና የመኖሪያ ፍቃድ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ የውጭ ሃገራት ነዋሪዎችን፣ የስራ ፍቃድ ኖሯቸው ነገር ግን የመኖሪያ ፍቃድ መታወቂያ የሌላቸውን፣ ለዑምራና ሃጂ ተጉዘው በዚያው የቀሩ ወይም የቆይታ ጊዜያቸው ያለፈባቸውንና ያለ ሃጂ ፍቃድ የተጓዙ አማኞን የሚመለከት ነው። በአዋጁ የተቀመጠውን ሃገሪቱን ለቆ የመወጫ የግዜ ገደብ በማያከብሩት ላይ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ በአዋጁ ተደንግጓል። በጸጥታ ሃይሎች የቤት ለቤት አሰሳ ተካሂዶ፣ ህገ ወጥ ነዋሪዎቹ በህግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግ ነው ድንጋጌው የሚገልጸው።
የኢፌዴሪ መንግስት ህግ ተላልፈው በሳኡዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሳይጉላሉ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ መጋቢት 21፣ 2009 ዓ/ም ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር የሚመክርና አቅጠጫ የሚያስቀምጥ የልኡካን ቡድን ወደሳኡዲ አራቢያ ልኳል። የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ወደሳኡዲ አራቢያ የተጓዘው የውጭ ሃገር ዜጎች እንዲወጡ የተቀመጠው የ90 ቀናት ቀነ ገደበ በተጀመረበት ዕለት ነበር።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ መንግስት ዜጎቹ ሳይጉላሉ ወደ ሃገራቸው በሰላም እንዲመለሱ ለማድረግ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አስታውቋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ኢትዮጵያውያኑን ወደሃገራቸው የሚመልስ አስተባባሪ ኮማንድ ፖስት ተቋቁማል። በሀገር አቀፍ ደረጃም እንዲሁ ስራውን የሚመራ ኮማንድ ፖስት ተደራጀቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ በዚህ አኳኋን በሪያድ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲና ጅዳ ባለው ቆንጽላ ጽህፈት ቤት አማካኘነት ለዜጎች አስፈላጊውን መረጃ በማቅረብ ድጋፍ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል። የሳኡዲ አራቢያ መንግስት ባስቀመጠው የ90 ቀናት የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሃገራቸው ለሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ከአራት ዓመት በፊት እንደተደረገው ወደ የመጡበት አካባቢ የሚመለሱበትና ቀጣይ ህይወታቸውን የሚመሩበት ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት አስፈላጊውን ሁኔታ ለማመቻቸት መዘጋጀቱንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በቅርቡም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል የተመራ የልዑካን ቡድን ወደ ሳኡዲ አራቢያ አምርቶ በጉዳዩ ዙሪያ ከሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ተወያይቷል። የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል ከሳኡዲ አረቢያ የቆንስላ ጉዳዮች አቻቸው አምባሳደር ታሚሚ አልደውሰሪ ጋር ነበር የተወያዩት። በውይይቱ ኢትዮጵያውያኑን ወደሃገራቸው የማስመለሱን ሂደት በተረጋጋ መንፈስ ለማከናወንና የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሏቸው መንገዶች ላይ መክረዋል። ዶክተር አክሊሉ በሪያድና አካባቢው ከሚገኙ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ተወካዮች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችም ጋር ውይይት አድርገዋል።
በሪያድና በጂዳ የሚገኙ ሚሲዮኖች የጉዞ ሰነድ አሰጣጥ ሁኔታ የተቀላጠፈ እንዲሆንና በጉዳዩ ዙሪያ ሊያጋጥሙ በሚችሉ መሰናክሎች ላይ ውይይት ተካሂዷል። ከውይይቱ በኋላ ወደሃገራቸው የሚመለሱ ኢተዮጵያውያን በቀላሉ መውጫ ቪዛ እንዲያገኙ በሳኡዲ አራቢያ መንግስት በኩል ተንቀሳቃሽ ጽህፈት ቤቶች እንዲከፈቱ ተደርጓል። ይህን ተከትሎ 4 ሺህ ህገ ወጥ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን የጉዞ ሰነድ መውሰዳቸውንና ከእነዚህ ውስጥ 2 መቶ ወደ ሃገራቸው መግባታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። ወደሃገራቸው የተመለሱት መመለስ ከሚገባቸው አንጻር ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመልክቷል።
እንግዲህ ኢትዮጵያውያን በተለይ ባለፉ አራት አስርት ዓመታት በብዛት ወደሳኡዲ አራቢያ ሲጓዙ መቆየታቸው ይታወቃል። የጉዟቸው ምክንያት ኢኮኖሚያዊ ነው። ኢትዮጵያውያን ወደሳኡዲ አራቢያም ሆነ ወደሌሎች ሃገራት የሚጓዙት ስራ ፍለጋ እንዲሁም የተሻለ ገቢን ተስፋ በማድረግ ነው። ኢትዮጵያ የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት በህገመንግስት የተረጋገጠባት ሃገር በመሆኗ ዜጎች ስራ እናገኛለን ወይም የተሻለ ገቢ የሚያስገኝ ስራ ይገጥመናል ብለው ወዳሰቡበት ሃገር ያለአንዳች ክልከላ በነጻነት የመጓዝ መብታቸው ተረጋግጧል። እናም ኢትዮጵያውያን ለስራና የተሻለ ገቢ ፍለጋ ወደሳኡዲ አራቢያም ሆነ ወደሌሎች ሃገራት መጓዛቸው በራሱ ችግር የለውም። ለዚህ ዓላማ ጉዞ ማደረግ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የበለጸጉትን የአውሮፓ ሃገራት ጨምሮ በየትኛውም ሃገር ዝንተ ዓለም ሲከናወን የኖረ ነው።
በተለይ በኢተዮጵያውያኑ የስራና የተሻለ ገቢ ፍለጋ ወደውጭ ሃገራት ከሚያከናውኑት ጎዞ ጋር በተገናኘ ያለው ችግር የህጋዊነት ችግር ነው። ይህን ችግር ሌሎች በማደግ ላይ ያሉ ሃገራት ዜጎችም የጋሩታል። በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት የሚካሄድ የውጭ ሃገር ጉዞ፣ ጎዞው ራሱ ለከፍተኛ የህይወት መጥፋት ስጋት የሚያጋልጥ አደገኛ ከመሆኑ በተጨማሪ በመድረሻ ሃገራትም የመኖሪያና የስራ ፍቃድ በማግኘት በህጋዊነት የመኖር እድል ሰለሚያሳጣ ለአስከፊ እንግልትና ለሰብአዊ መብት ጥሰት ያጋልጣል። ሰዎች ከፍተኛ ወጪ አውጥተው በህገወጥ አዘዋዋሪዎች አማካኝነት በሚደርሱባቸው ሃገራት ከሚያጋጥማቸው አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት በተጨማሪ የመሰራት እድል ሳያገኙ ኪሳራና እንግልት ብቻ አትርፈው ባረፉበት ሃገር መንግስት ወደሃገራቸው የሚባረሩበት አጋጣሚም የተለመደ ነው። አሁን በሳኡዲ አራቢያ እየተደረገ ያለው ይህ ነው።
እናም ኢትዮጵያውያን ወደውጭ ሃገራት ለመጓዝ ከመወሰናቸው አስቀድመው በሃገራቸው ያለውን የስራ እድል አሟጠው ለመጠቀም ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ጥረታቸው አልሳካ ካላቸው ወይም በውጭ ሃገራት የተሻለ ገቢ እናገኛለን በለው ሲያምኑ ደግሞ ጉዞቸውን በህጋዊ መንገድ ብቻ አከናውነው፣ በሚኖሩበት ሃገር ህጋዊ የኑሮና የስራ ፍቃድ ሊኖራቸው የግድ ነው። ይህ ካልሆነ ለከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይጋለጣሉ፣ የስራ እድልም ሆነ ያሰቡትን የተሻለ ገቢ ማግኘት የሚችሉበት እድልም አይኖራቸውም።
አሁን በሳኡዲ አረቢያ ህገወጥ ሆነው የሚኖሩ ዜጎች የሃገሪቱ መንግስት ያወጣውን በሰላም ወደሃገራቸው የመመለስ አስገዳኝ አዋጅ አክብረው፣ የኢፌዴሪ መንግስት ያመቻቻውን የመመለሻ እድሎች ተጠቅመው ወደሃገራቸው መመለስ ይኖርባቸዋል። ይህ ካልሆነ ከአራት ዓመት በፊት አጋጠሞ የነበረው እንግልትና የሰብአዊ መብት ጥሰት ሊገጥማቸው የሚችል መሆኑ አያጠያይቅም። ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያውያኑን ከመጉዳት ባሻገር የሃገርንም መልካም ገጽታ ሰለሚያበላሽ፣ በሰላም እንዲመለሱ የማድረጉ ተግባር በሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ ሊደረግበት ይገባል። በዚህ ሂደት ዋነኞቹ ግን ህገወጥ ስደተኞቹ ኢትዮጵያውያኑ ናቸው። ወደሃገር ቤት ተመለሱ!