NEWS

ወደ ህዳሴ ግድበ የሚያመሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ በማሰብ በቦምብ የሰው ህይዎት እንዲያልፍ ያደረጉ ተከሳሾች በእስራት ተቀጡ

By Admin

April 13, 2017

ከሱዳን በመግባት በቤንሻንጉል ጉሙዘ ክልል ወደ ህዳሴው ግድበ የሚያመሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ በማቀድ በህዝብ ትራንስፖርት ላይ ቦምብ በመወርወር የዘጠኝ ሰወች ህይዎት እንዲያልፍ ብሎም በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ 10 የቤህነን የፓለቲካ ቡድን አባላት ከዘጠኝ አመት እስከ እድሜ ልክ በሚደርስ ጽኑ እስራት ተቀጡ።

የቅጣት ውሳኔ የተፈረደባቸው ተከሳሾች በኤርትራ ሃረና አካባቢ በሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ የሚኖሩት 1ኛ አብዱልዋሃብ መሃዲ ኢሳ፣ 2ኛ አብዱራሃማን ናስርን ጨምሮ 10 ግለሰቦች ናቸው።

የጠቅላይ አቃቢ ህግ ክስ እንደሚያመለክተው ተከሳሾቹ እራሱን ቤህነን ብሎ የሚጠራው የጸረሰላም ቡድን አባል በመሆን በኤርትራ ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ በ2006 ዓ.ም ወደ ህዳሴው ግድብ የሚያመራ ማንኛውም ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት ለማድረስ አቅደው 12 ሆነው ሙሉ የጦር መሳሪያ ትጥቅ በመታጠቅ በሱዳን አድርገው ቤንሻንጉል ገብተዋል።

ጥቅምት 26 ቀን 2006 ዓ.ም በሸርቆሌ ወረዳ ሼዲ አሸሸል ቀበሌ በህዝብ ትራንስፖርት በሚሰጥ ሚኒባስ ላይ ቦምብ በመወርወር የዘጠኝ ሰው ህይዎት እንዲያልፍና በአራት ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በሚየዚያ አራት ቀን 2006 ዓ.ም ደግሞ በአካባቢው እጣን ማውጣት ስራ ላይ የነበሩ ሶስት ወጣቶችን በመግደል፥ ነዋሪዎቹ የሚጠቀሙበትን አምቡላንስ ማቃጠላቸውን አቃቢ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

በፈጸሙት የሽብር ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ጥፋተኛ ተብለዋል።

በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል በዋለው ችሎትም፥ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ድረስ ያሉ ተከሳሾች በእድሜልክ እስራት ተቀጥተዋል።

ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያሉት ደግሞ በ21 አመት ጽኑ እስራት፣ ከ7ኛ እስከ 9ኛ ያሉት በ16 አመት ጽኑ እስራት እንዲሁም 10 ተከሳሽን በዘጠኝ አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።