ውይይቱና ድርድሩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቱን ለማስፋት ነው!
ታዬ ከበደ
ዴሞክራሲ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የሚመጣ የሂደት ውጤት ነው። የመራጩ ህዝብ አስተሳሰብ፣ በጊዜ ሂደት ለምርጫ የሚሰጠው ትርጉም የሚያድግና የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሁም እየሰፋ የሚመጣ ብሎም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በምርጫ የሚኖራቸው ተሳትፎ እየጎለበተ የሚሄድበት አውድ ነው። ይህ ተጨባጭ ሁኔታም በጅምር ላይ ያለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እና ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በምንም መልኩ አንድ ሊሆን እንደማይችሉ የሚያመላክት ነው። ለዚህም ነው— ዴሞክራሲ በአንዴ የሚገነባ ሳይሆን በጊዜ ዑደት ውስጥ ከህዝቡ አስተሳሰብ ደረጃ ጋር እያደር አብሮ የሚራመድ ሂደት ነው የሚባለው።
ከዚህ አኳያ የሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ስንመለከተው ሂደቱ 25 ዓመታትን ብቻ ያስቆጠረ ጅምር በመሆኑ ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች የሉበትም ለማለት የሚያስደፍር አይመስለኝም። አሁን የምንገኝበት ደረጃ የህዝብ አስተሳሰብ አድጓል፣ የሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳርም በሚፈለገው መጠን ሰፍቷል ለማለት አይቻልም። እናም ሀገሪቱን በመምራት ላይ የሚገኘው መንግስት የህዝቦች የዘመናት ጥያቄ የሆነውን ዴሞክራሲ በጥልቀት ማስፋትና ማጎልበት ይጠበቅበታል።
ከመሰንበቻው በገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ በሚንቀሳቀሱ 21 ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ክርክርና ድርድር ለማካሄድ በቅድመ ሁኔታዎች ላይ ለመወያየት መስማማታቸው ተዘግቧል። ዴሞክራሲን ከማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ከማድረግ አኳያ ይህ በገዥው ፓርቲ አማካኝነት የተጠራው የውይይት መድረክ ሊመሰገን የሚገባው ተግባር ነው።
እንዲህ ዓይነት መድረኮች በበዙና በተበራከቱ ቁጥር የሀገራችን ዴሞክራሲ ይበልጥ አሳታፊ፣ ግልፅነት የተሞላበትና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በበቂ ሁኔታ ሊያሳትፍ የሚችል ይሆናል። እናም በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካከል የሚካሄደው ክርክርና ድርድር ከዚህ ዴሞክራሲያዊ አውድ ብቻ መታየት ያለበት ይመስለኛል።
እንደሚታወቀው ገዥው ፓርቲ ከአምባገነኑ የደርግ ስርዓት ጋር ያደረገው መራርና እልህ አስጨራሽ ትግል የነበረው አንዱ ጉዳይ የዴሞክራሲ እጦት ነው። ደርግን አስወግዶ ስልጣን ከያዘም በኋላ ቢሆን፣ ይህን የህዝቦችን ጥያቄ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን ጥረት አድርጓል። ገዥው ፓርቲ ገና ከስልጣን መባቻው ወቅት ጀምሮ የታጠቁና ወደ 17 የሚጠጉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማወያየትና በማከራከር ባህሉ የሚታወቅ ነው። ይህም ዴሞክራሲን ለማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው ለማስቻል ክርክርና ድርድር ማድረግ ለገዥው ፓርቲ አዲስ ጉዳይ አለመሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።
እዚህ ሀገር ውስጥ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ለማሳለጥ የሚከናወኑ ማናቸውም ሁነቶች ማንንም ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሳይሆን የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የታገሉላቸውን መብቶች በፅኑ መሰረት ላይ ለማቆመ ታስቦ የሚከናወን ተግባር መሆኑን መገንዘብ የሚገባ ይመስለኛል። ስለሆነም በገዥው ፓርቲም ይሁን በመንግስት በኩል የሚከናወኑ ጉዳዩች ሁሉ ለሀገርና ለህዝብ ጠቀሜታ ሲባል እንጂ፣ ለታይታ አሊያም ለሌላ ጉዳይ የሚከናወኑ አይደሉም፤ ሊሆኑም የማይቸሉ መሆናቸውን በሰከነ አዕምሮ ግንዛቤ መያዝ ይገባል ባይ ነኝ።
እርግጥም በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚዎች መካካል ይደረጋል ተብሎ የታሰበው ዛሬ አይደለም። ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ትናንት የነበረና ነገም የሚኖር ነው። በዓመቱ መጀመሪያ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የህዝብ ተወካዩችንና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን የጋራ ስብሰባ በከፈቱበት ወቅት “…የሀገራችንን ዴሞክራሲ ለማጐልበት የተለየ እንቅስቃሴ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ አንዱ ቀዳሚ ስራ በገዥው ፓርቲና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚደረግ ድርድር የምርጫ ህጋችንን የማሻሻል ጉዳይ ይሆናል። ሀገራችን የምትመራበት የምርጫ ህግ በብዙ አገሮች እንዳለ የሚሰራበት ቢሆንም፣ ከእኛ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ድምፅ ሊሰማ የሚችልበትን አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ ሆኖ ከመገኘቱ ጋር የህግ ማሻሻያ ይደረጋል።…” ማለታቸው ይህንኑ የክርክርና የድርድር መንፈስ ለማመላከት ይመስለኛል። ይህ ሁኔታም መንግስትና ገዥው ፓርቲ ሁሉንም ነገር አስበውበትና በመርህ ደረጃ አምነውበት እንጂ ተግባራቸው ከታይታ አሊያም ከፍራቻ ጋር የተያያዘ ስለሆነ አይደለም።
ዴሞክራሲን ለማስፋትና ለማጠለቅ ተብሎ ገና በጅምር ላይ የሚገኝ፣ ክርክርና ድርድር መሆኑ እየታወቀ፤ በአንዳንድ ፅንፈኛና ህገ ወጥ ቡድኖች “ወጡ ሳይወጠወጥ ወስከንቢያው ቂጢጥ” እንደሚባለው ሂደቱን ለማጣጣል አስቀድመው የሚያነሷቸው ነጥቦችም ትርጉም አልባ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። በተለይም ‘ከክርክሩና ከድርድሩ በፊት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይነሳ፣ የታሰሩ ወገኖች ይፈቱ፣ ሁሉም ተቃዋሚዎች (በሀገራችን የህዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁትን ጭምር ማለታቸው ነው) ይሳተፉ…ወዘተ. የሚሉ አጀንዳዎችን በማንሳት የሚነዛው አሉባልታዊ አስተሳሰቦች መታረም መታረም የሚኖርባቸው ይመስለኛል።
እርግጥ እነዚህ አስተሳሰቦች ፅንፈኞቹና ተላላኪዎቻቸው በክርክርና በድርድር ሽፋን የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ለማወክ የሚያግዛቸውን አጀንዳ ለማራገብ የተሰነዘሩ መሆናቸውን ለማወቅ ነብይ መሆንን የሚጠይቅ አይመስለኝም። አንድን ጉዳይ ህጋዊ ለማድረግ በሚደረግ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ ህገ ወጥነትን በማቀንቀን ወንጀለኞችንና አሸባሪዎችን ዕውቅና ለመስጠት የሚደረግ አላስፈላጊ እንካ ሰላንቲያዎችም ናቸው።
ክርክሩና ድርድሩን ያዘጋጀው አካል ገና ከመነሻው ያስቀመጠው ነገር ቢኖር፤ እዚህ ሀገር ውስጥ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንጂ ህገ ወጦችንና አሸባሪዎችን አይደለም። ይህ ባልሆነበት ሁኔታም ፅንፈኞቹና ተላላኪዎቻቸው ባልተጠሩበትና በማይመለከታቸው ጉዳይ በለመደ አፋቸው እጃቸውን ለመዶል መሞከራቸው ባልተጋበዙበት ቤት የመቀላወጥ ያህል የሚቆጠር ነው። እናም በእኔ እምነት ይህን እጅግ የተዛባ፣ ህገ ወጥነትን የሚያገዝፍና የህግ የበላይነትን የሚደፈጥጥ አካሄድ ገዥውም ፓርቲ ይሁን ከእርሱ ጋር ለመደራደር ቀነ-ቀጠሮ የያዙት ህጋዊና ሰላዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ ሊኮንኑት የሚገባ ይመስለኛል።
የሀገራችንን ዴሞክራሲ ለማጎልበትና ለማጠለቅ ገዥው ፓርቲ፣ ህጋዊና ሰላማዊ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ውጤት ሊያመጡ አይችሉም። የሀገራችንን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ለፓርቲዎች ተሳትፎ የሚሰጠውን ትኩረት ባልተናነሰ ሁኔታ፤ በከፍተኛ ትምህርትና በልዩ ልዩ የስራ ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ምሁራን፣ የተለያዩ የሲቪክ ማህበረሰብ አደረጃጀቶችና በእነርሱ ውስጥ የታቀፉ ዜጎችን በቀጥታ በማሳተፍ ጠቃሚ ሃሳቦቻቸውንም ማካተት ይገባል።
በመሆኑም በክርክሩና በድርድሩ ወቅት እነዚህ ጉዳዩችም ታሳቢ መሆን ይኖርባቸዋል። ክርክርና ድርድር ሲባል በውጤቱ የሚገኘውን ግብዓት ለሀገር ግንባታና ዕድገት ለማዋል እንጂ፣ ፓርቲዎች ለራሳቸው ጥቅም ማስገኛ አድርገው እንዲጠቀሙበት አይደለም። እናም ፓርቲዎች ገና ድርድሩን ሳይጀምሩ ለመለያየት ከመሞከር ችግራቸውን በጋራ ፈትተው ለዴሞክራሲው መዳበር ራሳቸውንም ጭምር ሆን መስዕዋት ማድረግ ይገባቸዋል።