Ethiopiaprosperous
Ethiopian News Ethiopian Daily news, Regarding political and social Issues.

የሀገራችን ፌዴራሊዝም እውነታዎች

0 400

Get real time updates directly on you device, subscribe now.

የሀገራችን ፌዴራሊዝም እውነታዎች

ታዬ ከበደ

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው አምነው እና ተስማምተው ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የኢፌዴሪ ህገ መንግስት ያፀደቁትና ፌዴራላዊ ስርዓቱን የመሰረቱት ከሽግግር መንግስቱ በፊት የድህነት ዘበኛ የነበረውን የደርግ ስርዓትን አስወግደው ነው። ሽግግር መንግስቱ ካበቃም በኋላ የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፈዋል፡፡ ያም ሆኖ ህገ መንግስቱን ካፀደቁት በኋላ በመሰረቱት ፌዴራላዊ ስርዓት በርካታ ድሎችን ተጎናፅፈዋል፡፡

ቀዳሚው ድህነት ከተሰኘው ጠላት ጋር የከፈቱት ግልጽ ውጊያ ነው፡፡ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ከድህነት በላይ ጠላት እንደሌላቸውም አወቁ፡፡ ይህን ለመዋጋትም የሀገራችን ህዘቦች ከሊቅ እስከ ደቂቅ በመንግስት ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች እየተመሩ በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ዕድገት ማስመዝገብ ጀመሩ።

ታዲያ ህገ -መንግስቱ ጸደቆ በሀገሪቱ የፌዴራል ሥርዓት ዕውን ከሆነ በኋላ በህገ – መንግስቱ የተቀመጡት መሰረታዊ የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዳዮች በሚገባ ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር፣ የሚፈልጉትን ሃይማኖት በሰላማዊ መንገድ የማራመድ፣ በቋንቋቸው  የመናገር እና የመጻፍ፣ ባህላቸውን እና እሴቶቻቸውን በነጻነት የመግለፅ መብቶቻቸን ህገ – መንግስቱ በማያሻማ መልኩ አረጋግጦላቸዋል፡፡ እርግጥም የዘመናት የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግልም ይህ ነበር፡፡

ሆኖም ‘የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ተግባራዊ ከሆነ ሀገሪቱ ወደ አይሆኑ አዘቅት ውስጥ ትገባለች፣ የመበታተን አደጋ ይገጥማታል፣ ህዝቦቿ በየጎራው ተከፋፍለው እርስ በርሳቸው ይበላላሉ ወዘተርፈ’ በማለት በወቅቱ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን የፖለቲካ ተንታኝ ሟርተኞች በተደጋጋሚ ፌዴራላዊ ስርዓታችን የማይጠቅመን አስመስለው ማራገባቸው አይዘነጋም፡፡

እርግጥ እነዚህ የመገናኛ ብዙሃንና ሟርተኞች በሀገሪቱ የተዘረጋው ፌዴራላዊ ሥርዓት ህዝቦቸችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ዘንግተውት አልነበረም— የቀድሞው ሥርዓት ናፋቂ ከሆኑት ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር በመሰለፍ ማቀንቀኑን መርጠውት እንጂ፡፡ ዳሩ ግን እነርሱ የፈለጉትን ቢሉም መንግስትና ህዝብ በውዠንብራቸው ሳይዘናጉ ብዝሃነታቸውን ውበታቸው በማድረግ አንድነታቸውን አጠናክረው፣ ለጋራ ዕድገት መረባረቡን ነው የመረጡት፡፡

ይህን ሃቅም ዶ/ር ሀሺም ቶውፊቅ የተባሉ ምሁር በ1999 ዓ.ም “ስለ ኢፌዴሪ ህገ – መንግስት አንዳንድ ማብራሪያዎች” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ላሪያ ዳይመንድ የተባለ የውጭ ፀሐፊን ጠቅሰው እንደገለፁት፤ “ፌዴራሊዝም በማህበራዊ ምንነት ምክንያት የሚፈጠር ልዩነቶችን ለማቻቻል (አብሮ ለማራመድ) እና በማህበራዊ ምንነት ወይም በሌላ የማንነት ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን ለማስተንፈስ አግባብነት ያለው የፖለቲካ መሣሪያ ነው” ብለዋል። ይህ አብሮነትም የጋራ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ ሥርዓቱ የጎላ ሚና እንደሚጫወትም አብራርተዋል፡፡

አዎ! ይህን ዕውነታ የተገነዘበው መንግስትም ህገ – መንግስቱን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በገዛ ፈቃዳቸው ተስማምተው እና ተማምነው እንዲያጸድቁት የተጫውተው ሚና በእጅጉ የላቀ ነው፡፡ ይህችን ሀገር ከአምባገነኑ የደርግ ሥርዓት አገዛዝ ያላቀቀው ኢህአዴግ መራሹ የህዝብ ትግል፤ ስልጣን በህዝብ እና በህዝብ ብቻ የሚረጋገጥ እንደሆነም የሚያምን በመሆኑ፤ በዚህ የሀገሪቱ የበላይ ህግ ህዝቦች የትግላቸው ባለቤት እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡

ታዲያ እዚህ ላይ ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በህይወት እያሉ ስለ የፌዴራሊዝም ሥርዓት አስመልክተው ያሉን መጥቀስ ያስፈልጋል። ታላቁ መሪያችን “ህገ -መንግስቱ የህዝቦቻችን የዘመናት ትግል ውጤት ነው፤ ይህን የህዝቦቻችንን የዘመናት ትግል ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ህገ – መንግስቱ የተረቀቀው፡፡ የኢትዮጵያ ባህል ማለት የኢትዮጵያ ህዝቦች ባህሎች ተደምረው የሚፈጥሩት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋ ማለት የኢትዮጵያ ቋንቋዎች በሙሉ ተደምረው የሚፈጥሩት ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ማለት የህዝቦች ታሪክ ተደምሮ የሚፈጥረው ነገር ነው፡፡ ይህ ታሪክም በልዩነት የሚስተናገደው በፌዴራሊዝም ሥርዓት ነው” ብለው ነበር፡፡ እናም ለሀገሪቱ ብቸኛው አማራጭ የፌዴራል ሥርዓት መከተል እንደሆነም አስምረውበታል፡፡

ይህ ዕውነታም የሀገራችን ህዝቦች በፌዴራላዊ ስርዓቱ ተጠቃሚነታቸው መጎልበቱን ያሳየናል፡፡ በቅድሚያ ስርዓቱን ለመቀበል አስፈላጊ የተባሉ ጉዳዩችን አነሳለሁ፡፡ ፌዴራላዊ ሥርዓተ መንግሥትን ለመከተል ከሚያስገድዱ ምከንያቶች አንዱ የማንነት ጥያቄዎችን መልስ ለመስጠት ነው፡፡ ይህም የራስ አስተዳደርና የጋራ አስተዳደርን ያጣመረ ሥርዓት በመሆኑ በርካታ ማንነቶች ባሏቸው ሀገራት ለማንነቶች ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያለው ሥልጣን ያጐናጽፋል፡፡

እንዲሁም በፌዴራል መንግሥት ተቋማት ፍትሃዊ ውክልና እንዲኖራቸው በማድረግ ድምፃቸው ከፍ ብሎ እንዲሰማ ሰፊ ቦታ ይሰጣል፡፡ ሆኖም ሁሉም ፌዴሬሽኖች ተመሣሣይ አወቃቀር ስለማይከተሉ በማንነቶች ላይ የተመሠረተ አወቃቀር የሌላቸው ፌዴሬሽኖች ተጨማሪ የቋንቋና ሌሎች የፖሊሲ እርምጃዎች ይወስዳሉ፡፡ ኢትዮጵያ በቅድመ ፌዴራል ሥርዓት ዘመን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እሥር ቤት የነበረች ሀገር ናት፡፡

በዘውድ ዘመን የገዥዎች ወሣኝ እምነት “አንድ ቋንቋ፣ ኃይማኖት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ አስተዳደር (አኃዳዊ)፣ ባንዲራ” በሚል የሚገለጽ ማንነትን ማሳጣት ስለነበር ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የትክክለኛ ኢትዮጵያዊነት ማንነት ካርድ የሚያገኙት ይህንን ፍልስፍና ከተከተሉ ብቻ ነበር፡፡

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ተገደው ማንነታቸውን እንዲያጡ፣ የእኛ የሚሉትና የኖሩበት አካባቢ መሬት እንዲነጠቁ፣ የሰውና የአካባቢ ስሞችን እንዲለውጡ፣ በመነጩበት ዘር ሐረግ ምክንያት እንዲዋረዱ እንዲሁም በሚከተሉት የተለየ ኃይማኖት ምክንያት እንዲናቁ ያደረገ ሥርዓት ነበር፡፡

በአምባገነናዊ የደርግ አስተዳደር ወቅትም ከማንነቶች ጋር የተያያዘ መሠረታዊ የፖሊሲ ለውጥ አልነበረም፡፡ ማንነትን የማሳጣት የዘውድ ፖሊሲ አጠናክሮ ስለቀጠለበት የማንነት ጥያቄ ያነሱትን ማኅበረሰቦች በማሳደድ ጨፍጭፏል፡፡ ደርግ መሣፍንታዊ የመሬት ይዞታን የለወጠ ቢሆንም ይህን ያደረገው ግን ከማንነት ጋር የተያያዙ የመብት ጥያቄዎችን መፍትሄ ለመስጠት አልነበረም፡፡ ደርግ በአገዛዝ ዘመኑ ማብቅያ ያወጀው የራስ ገዝ አስተዳደርም ቢሆን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የተቀጣጠሉ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ትግሎችን ለማቀዛቀዝ የታቀደ ነበር፡፡

ምን ይህ ብቻ! ጥያቄውን ያነሱ ሕዝቦች ፍላጐት መሠረት ያላደረገ፣ ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና ያልነበረውና ከደርግ የተመረጡ ባለሥልጣናት በአስተዳዳሪነት የተሾሙበት ነበር፡፡ የራስ ገዙ አከላለል አንዱን ማንነት ከሌለው ማንነት በማቀላቀል የተፈፀመ በመሆኑ ማንነትን ለማሳጣት የተቀረፀ እንደነበር ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራል ሥርዓት ለማንነቶች የሰጠው መብት ከብዙ ፌዴሬሽኖች ጋር ሲነጻጸር የላቀና ብዙ ማንነቶች ላሏቸው ሀገራት ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡ የሥርዓቱ የማንነቶች አያያዝ ብዝኃነት ዕድል ነው ከሚል መሠረታዊ አስተሳሰብ ይመነጫል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አጠቃላይ መንፈስና በተለያዩ አንቀጾች ውስጥ ተደንግጐ ይገኛል፡፡

የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች ያሏቸውን ልዩ ልዩ የማንነት መገለጫዎች አምነውና አክብረው ለመኖር፣ ካሳለፉት ታሪክ የወረሱትን መልካም ትስስር ተጠቅመው ለወደፊት የላቀ ትስስር ማለትም አንድ የጋራ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ቃል መግባታቸውን ያረጋግጣል፡፡ ብዙህነታቸው ለአብሮነታቸውና ለጋራ ተጠቃሚነታቸው ዕድል መሆኑን ተስማምተው ቃል ኪዳንም አስረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ  ሕገ መንግሥት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች እና ኃይማኖቶች እኩል መሆናቸውንና አብሮ ለመኖር ያላቸውን ተስፋ በፌዴሬሽኑ ሰንደቅ ዓላማ መሃል በተቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የሚንፀባረቅ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቋንቋዎች እኩል እውቅና የተሰጣቸው ነው፡፡ እያንዳንዱ ክልልም የሥራ ቋንቋ የመምረጥ መብት አለው፡፡

ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶችና የመንግሥት ሥልጣን ምንጮች መሆናቸው በሕገ መንግሥቱ ተደንግጐ ይገኛል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የኃይማኖትና መንግሥትን መለያየት መርህ በማስቀመጥ መንግሥት ለሁሉም እምነቶች እኩል የማገልገል ግዴታን ጥሎበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም ሰው የመረጠውን ኃይማኖት የመከተል መብቱ የተረጋገጠ መሆኑም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን እስከ መገንጠለ መብታቸው መጠበቁን፣ እያንዳንዱ ማንነት በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ ታሪኩን የመንከባከብ መበት አለው፡፡ እንዲሁም እያንዳንድ ማንነት ራሱን የማስተዳደር ሙሉ መብት የተረጋገጠለት መሆኑ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡

ከዚህም ጋር ሴቶች በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ መስኮች ከወንዶች ጋር እኩል መሆናቸውንና ከዚህ በፊት በነበረው ልዩነት ምክንያት የተፈጠረባቸውን ጫና ለመቅረፍ ልዩ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተደንግጓል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት መሬት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ሀብት መሆኑን ደንግጓል፡፡

እነዚህ ማንነቶች ራሳቸውን የማልማትና በማያቋርጥ ሁኔታ ኑሯቸውን የማሻሻል መብት እንዳላቸው እንዲሁም አባል የሆኑበትን ማኅበረሰብ በሚመለከቱ የመንግሥት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ሃሳብ የመስጠት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አናሣ ብሔረሰቦች ያለምርጫ በልዩ ሁኔታ የሚወከሉበት ከሃያ የማያንስ መቀመጫዎች በተወካዮች ምክር ቤት እንዲኖራቸው መደንገጉ ድምፃቸው ከፍ ብሎ እንዲሰማ ያስችላል፡፡ እነዚህ መብቶች ላለፉት 26 ዓመታት ጥቅም ላይ ውለው መላውን ህዝቦች ተጠቃሚ ያደረጉ ብቻ አይደሉም። ይልቁንም የሀገራቸውን አንድነት በማፅናት አንድ የጋራ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ስርዓት እንዲገነቡም በር የከፈቱ ናቸው፡፡ በመሆኑም የሀገራችን ፌዴራሊዝም እውነታዎች የሚያሳየው ልዩነትን የሚያከብርና አንድነትን የሚያጠናክር በመሆኑ የዚህች ሀገር የህዝቦች ችግር መፍቻ መፍትሔ ሆኗል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.

This website uses cookies to improve your experience. We'll assume you're ok with this, but you can opt-out if you wish. Accept Read More

Privacy & Cookies Policy