በቅኝ ግዛት ዘመን እአአ 1959 የግብፅ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጋማል አብዱልናስር ከሱዳኑ አቻቸው ጋር የአባይን ወንዝ በኢ-ፍትሀዊነት መጠቀም የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ። ይህ ስምምነት ዓላማው ግብፅና ሱዳን የወንዙን ውሃ በብቸኝነት ለመጠቀም የሚያስችላቸው ነበር። በመሆኑም በስምምነቱ ግብፅ የአባይን ውሃ ሶስት አራተኛውን እንድትጠቀም ሲያደርግ ቀሪውን ደግሞ ለሱዳን የለገሰ ሆነ።
አባይን በብቸኝነት የመጠቀም ሁኔታው ግብፃውያኑ ወንዙን በሚመለከት የአይደፈሬ/ ማንአለብኝነት ስሜት እንዲኖራቸው በማድረጉ ወንዙ በሌላ አካል ተነካ ማለት ግብፅን መዳፈር ነው ሲሉ ለዜጎቻቸው ነግረዋቸዋል። ከልጅነት ጀምሮ በትምህርት ስርዓታቸው ውስጥ በማስረፅ ዛሬም ድረስ «የአባይ ወንዝ ከሌለ ምግብ የለም፤ ታሪክ እና ቅርስም አይኖርም፤ ግብፅ የምትባል አገር አትኖራችሁም» በማለት ከህይወታቸው ጋር አስተሳስረው አሳምነ ዋቸዋል።
የጋማል አብዱል ናስር ተከታይ ፕሬዝዳ ንት አኑዋር ሳዳትም «የአባይን ውሃ በሚመለከት ለሚፈፀሙ ማናቸውም ተግባራት የግብፅ ምላሽ/አፀፋ የከፋ ነው። አፀፋውም እስከ ጦርነት ሊደርስ ይችላል።» ሲሉ ግብፃውያንን እየሰበኩ፣ የተፋሰሱ አገራት ላይ ጫና በመፍጠር የፕሬዝዳንትነት እድሜ ያቸውን ለማራዘም ተጠቅመውበታል ሲሉ የታሪክ ምሁራን ያስታውሳሉ።
በግብፃውያኑ ተግባር ደስተኛ ያልሆኑት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በተለይ ፕሬዝዳንት ጋማል አብዱል ናስር የፈፀሙት የ1959 ኢትዮጵያን ያገለለ ስምምነት 1ሺ 600 ዓመታት ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና የእስክንድርያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ጋብቻ እንዲያፈርሱ አስገድ ዷል።
የናስር አግላይ ስምምነት ለግብፃውያን የመስኖ፣ የኃይል አቅርቦትና ለዘመናት ሲያስቸግራቸው የኖረውን የጎርፍ አደጋ የታደገ ሁሉን አቀፍ ግድብ የአስዋን ግድብን ለመገንባት መልካም አጋጣሚን ፈጠረላቸው። በመሆኑም ግብፅ የአባይን ውሃ በሚመለከት ለተፋሰሱ አገራት የነበራት ኢ-ፍትሀዊ አስተሳሰብ በገሀድ እንዲታወቅ አደረገ።
«ግብፅ የሰሀራ በረሀን አረንጓዴ ለማድረግ የአባይን ውሃ ስትጠቀም ለአባይ ወንዝ 85 በመቶ የምንገብረው እኛ ኢትዮጵያውያን ግን አባይን ተጠቅመን ራሳችንን መመገብ ለምን አልቻልንም?» ሲሉ ታላቁ መሪ አቶ መለስ በቁጭት ተናግረዋል። የግብፅ ፍትሀዊነት የጎደለው ተግባር ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የተፋሰሱ አገራትን ክፉኛ ያስቆጣ ነበር።
ይህን ተከትሎም በወቅቱ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ እንዲህ ብለው ነበር፥ «ግብፅ በዚህ ኢ-ፍትሀዊ ተግባሯ ጥቁር አፍሪካውያንን በተለይ ደግሞ የተፋሰሱ አገራትን እየጎዳች መጓዝ አትችልም።» ሲሉ ወቅሰዋል። «ከዚህ ኢ- ፍትሀዊ አጠቃቀም በመውጣት ሁሉንም የአባይ ተፋሰስ አገራትን ያካተተ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ስርዓት መፍጠር አለብን» በሚል ፅኑ እምነት በተለይ ኢትዮጵያ የጀመረችው እልህ አስጨራሽ ትግል ፍትሃዊ የሀብት አጠቃቀም እንዲሰፍን አገራቱ የጋራ መስማማት ላይ ደረሱ። በዚህም መሰረት አገራቱ አንዱ በአንዱ ላይ የከፋ ተፅእኖ ሳይፈጥር የተፈጥሮ ሀብቱን መጠቀም የሚያስችል አህጉር እና ዓለም አቀፍ ህግ ሆኖ ድጋፍ አገኘ።
በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ፍትሀዊ እና የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል በማድረግ በ2003 ዓ.ም ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታን መጀመሯን ይፋ አደረገች። ይህን ተከትሎም የተለያዩ አካላት በተለይ ደግሞ ግብፅ ከግንባታው መጀመር አንስቶ አሁን እስካለን በት የግንባታ ደረጃ ድረስ ተቃውሞዋን እያቀረበች ትገኛለች። ምንም እንኳ በግብፅና በኢትዮጵያ በኩል ግድቡን በሚመለከት ድርድሮችና ውይይቶች እየተካሄዱ ቢሆንም በተጨባጭ የግድቡን ግንባታ በሚመለከት በተለይ በግብፃውያን ምሁራን እና ባለስልጣናት ዘንድ እየተነሱ ያሉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? በኢትዮጵያውያን ምሁራን እና ባለስልጣናትስ በኩል ጉዳዮቹ እንዴት ይታያሉ? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ከግብፅም ሆነ ከኢትዮጵያ በኩል ያሉ ሀሳቦችን በግልፅ ለመዳሰስ ይሞከራል።
የአዞ እንባ
በካይሮ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ የኮንስት ራክሽን እና የአርክቴክቸር ኢንጂነሪንግ ረዳት ፕሮፌሰር ሼሪን ኤልባራዳይ እንደሚገልፁት የህዳሴ ግድቡን በሚመለከት ግብፅ ማግኘት የሚገባትን ከፍተኛውን የውሃ መጠን ሳትነጠቅ፤ ኢትዮጵያም ተጠቃሚ መሆን የምትችልበትን የጋራ መግባባት ላይ መድረስ አለባቸው፤ ይገባልም ብለዋል።
«ሁለቱ አገራት ግብፅና ኢትዮጵያ ሊነጋገሩበት የሚገባው ዋናው ጉዳይ ግብፅ በዓመቱ ውስጥ የአባይን ውሃ በከፍተኛ መጠን በምትጠቀምበት የእርሻ ወቅት ማግኘት የሚገባትን የውሃ መጠን ሊቀነስባት አይገባም። በእነዚህ የእርሻ ወራት የውሃውን መጠን አስመልክተው ግልፅ መግባባትና ስምምነት ላይ መድረስ ይገባቸዋል።» ሲሉ ሼሪን ይናገራሉ።
አቶ ብርሀኑ በላቸው በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታንት ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ ትምህርት መምህርና የትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ናቸው። በእርሻ ወቅት ውሃ እንዳይቸግረን የሚለውን የሼሪንን ሀሳብ መሰረተ ቢስ ነው ሲሉ ምላሽ ይሰጣሉ። «አባይ ወንዝ የግብፅ እርሻ ላይ ተመስርቶ ኑሯቸውን የሚያደናቅፍበት ሁኔታ የለም። ግብፃውያን እስከ ዛሬ ድረስ ቢመከሩም ሊማሩበት ያልቻሉበት ጉዳይ ቢኖር በሰፋፊ የሩዝ እርሻዎቻቸው ሳቢያ እያባከኑት ያለው ውሃ ነው» ይላሉ አቶ ብርሀኑ።
ግብፃዊያን ከሩዝ ይልቅ ስንዴ ቢዘሩ የውሃ ብክነትን ይቀንሳሉ የሚሉት አቶ ብርሀኑ፤ «የሩዝ እርሻ በተፈጥሮው ውሃ ተኝቶበት ነው የሚበቅለው። በመሆኑም ውሃ ያባክናል። ግብፆች አንድ ማሳ ላይ ሩዝ ለማምረት የሚጠቀሙበት ውሃ አምስት ማሳ ላይ ስንዴ ለማምረት በቂ ነው።» ሲሉ ብክነቱን በንፅፅር ያቀርባሉ። በዚህ ሁኔታ ግብፃውያኑ ውሃውን እያባከኑ እንደሆነ አቶ ብርሀኑ አፅንኦት ይሰጣሉ። ከዚህ አንጻር የውሃ እጥረት እንደሌለባቸው ያስገነዝባሉ።
የአስዋን ግድብ በረሀ ላይ ነው የተሠራው። ግድቦቹ እኛ ጋር ቢሠሩ በተለይ ከፍተኛ ሙቀት በሌለባቸው ደጋ ቦታዎች በረሀ ላይ የሚተነው ውሃ ይቀንሳል። አቶ ብርሀኑ እንደሚገልጹት ግብጾች ውሃ አባካኝ የሆኑ ፕሮጀክቶች አሏቸው። እንደ አቶ ብርሀኑ ምላሽ አስዋን ግድብ ብቻ ሳይሆን «ቶሽካ» የሚባል ግድብ ላይ ውሃ ጠልፈው ሲያበቁ በረሀ ላይ ያስተኙታል፤ በዚያ ሙቀትና በረሀ የተኛው ውሃ በመትነን ከአገልግሎት ውጪ ይሆናል። እርሻቸውም ሆነ ግድቦቻቸው ውሃ ቆጣቢ አይደሉም። ይህን የሚያባክኑትን ውሃ የት ትተው ነው የውሃ እጥረት ይገጥመናል የሚሉት ሲሉ አቶ ብርሀኑ ይመልሳሉ።
«ይህም ሆኖ ከአባይ ወንዝ ባለፈም ለብዙ ዘመናት የተከማቸ የከርሰ ምድር ውሃ አላቸው። ይህን ሀብት ለክፉ ቀን አስቀምጠው ነው አሁን ከእኛ ጋር የሚደራደሩት። ይህ በራሱ ኢ-ፍትሀዊ ነው። ነገር ግን የውሃ ችግር ኖሮባቸው አይደለም። ዋናው ግን “ከእኛ በላይ የበላይና ተደማጭ የለም” በሚል ነው። ነገር ግን በተግባር ሲታይ በዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ በአፍሪካ ውስጥ ተደማጭ ከሆኑ አገራት ውስጥ ኢትዮጵያ፥ ደቡብ አፍሪካን ተከትላ ሁለተኛዋ አገር ናት። ይህን ወደ ኋላ መመለሰ አይቻልም።» ሲሉ አቶ ብርሀኑ ያስረዳሉ።
የውሃ ሙሌት ስትራቴጂ
ሼሪን አፅንኦት ሰጥተው የሚገልፁት ጉዳይ አለ። ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ እያገባደደች ባለችበት በአሁኑ ወቅት ውሃ የምትሞላበት ጊዜ ግብፅን ያሳስባታል ብለዋል። በመሆኑም ግድቡ ውሃ ሲሞላ ግብፅ ላይ የሚኖረው ተፅእኖ ከፍተኛ ነው ብለው ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ የምትሞላበት ጊዜ ከአስራ ሁለት ዓመታት ያነሰ ሊሆን አይገባም ሲሉ፤ ይህን በሚመለከትም የግብፅ መንግሥት ቁልፍ የመደራደሪያ አጀንዳ ሆኖ ሊያነሱት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ግድቡ ውሃ የሚሞላበት ወቅት ይራዘም በሚል የሚነሳው ሀሳብ ከሳይንሱ የራቀና የተምታታ ነው የሚሉት የኢፌዴሪ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዲህ ብሎ ነገር ጭራሽ አለመኖሩን ያነሳሉ። ግድቡ የሚሞላበት የራሱ የሆነ የሙሌት ስትራቴጂ አለ። በዚህ ስትራቴጂ መሰረት ይሞላል እንጂ እነሱ በሚሉት መንገድ አይደለም።
“ሙሌቱ 12 ዓመት በላይ የወሰደ ጊዜ ሊመደብለት ይገባል” ይላሉ። የሚገርመው ግን በተከታታይ 12 ዓመታት ድርቅ ከሆነ ግድቡ ውሃ አይሞላም። ወቅቱ ዝናባማ እና ለሙሌት ምቹ ወቅት ከሆነ ደግሞ በአጭር ጊዜ ሊሞላ ይችላል። ስለዚህ እነሱ እንደሚሉት ውሃውን ለመሙላት ይህን ያህል ዓመት ይበቃል ብሎ በመወሰን ችግሩ ላይፈታ ይችላል። በመሆኑም የግድቡን ውሃ በሚመለከት ራሱን የቻለ ስትራቴጂ አለው ብለዋል ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ። እስከ አሁን ባለን ግምገማ ጉልህ ተፅእኖ በማያሳድር መልኩ ግድቡን ውሃ ለመሙላት እየሠራን ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።
የተበላሸውን ግንኙነት ማከሚያ
ተባባሪ ፕሮፌሰር ሀሚድ አሊ በካይሮ ዪኒቨርሲቲ የህዝብ ፖሊሲና አስተዳደር ትምህርት ክፍል አስተባባሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ግብፅ እአአ በ1959 ከሱዳን ጋር የፈፀመችው የብቻ ስምምነት ከተፋሰሱ አገራት ጋር የነበራትን የተበላሸ ግንኙነት ዳግም በመልካም ገፅታው ለመገንባት የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ በመጠቀም የትብብር አስተሳሰብን የምትጀምርበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ይመክራሉ። ይህን ገፅታዋን ለመገንባት ለህዳሴ ግድቡ በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር ሊኖራት የሚገባው የትብብር ፍላጎትም በቅድመ ሁኔታ ላይ ሊመሰረት አይገባም ባይ ናቸው። ግብፅ በዚህ መነሻነት በቅኝ ግዛት ዘመን ይዛው የመጣችውን ኢ- ፍትሀዊነት በትብብር ልትቀይር ይገባል ሲሉ አስታውቀ ዋል።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ሀሚድ አክለውም ግብፅና ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ልዩነትን አስወግደው ግንኙነታቸውን ወደ ጋራ ተጠቃሚነት በመለወጥ በኢኮኖሚ ዕድገትና ኢንቨትመንት ሥራዎች ማትረፍ የሚችሉባ ቸው እና ህዝቦቻቸውንም ተጠቃሚ የሚያደርጉባቸው መንገዶችን መፈተሽ ወቅቱ ያስገድዳል፤ ለህዝብ ጥቅም ሲሉም ይህን ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
እንደ አቶ ብርሀኑ ገለጻ እአአ በ1959 ዓ.ም ግብጽ የፈጸመችው ስምምነት የዓለም አቀፍ ህግን ያልተቀበለ ነው። የኢንቴቤውን የጋራ ስምምነት ማዕቀፍንም አልተቀበሉም። በመርህ ደረጃ ግን ኢትዮጵያ፤ ሱዳን እና ግብፅ የተፈራረሙት ስምምነት ዓለም አቀፍ ህጎች ላይ ያሉትን ቁምነገሮች በአቋራጭ ተቀብለው ፈርመውታል ብለዋል። ይህ የሚያሳየው ግብፆች ወደ አእምሮ ሥራ መመለስ መጀመራቸውን ነው ይላሉ። ከዚህ በኋላ በግጭት፤ በጡጫ አልያም በጦርነት የሚፈታ ነገር አለመኖሩን አስረድተዋል።
«ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት ከፍቶ የአባይን ወንዝ ጠቅልሎ ከነምንጩ ወደ ግብጽ እንወስዳለን የሚለው ሀሳብ የሚያዋጣ አይደለም። እርዳታ እና ብድር ማስከልከል ነበር የሚችሉት፤ ይህም ቢሆን የሚያዋጣ አልሆነም። ምክንያቱም ያለ ብድር እና እርዳታ በራስ አቅም የምንሠራ አገር ለመሆን በቅተናል።
«ስለዚህ ያላቸውን አማራጭ በሙሉ አሟጠው ተጠቅመውበታል፤ እንደማያዋጣም አይተውታል። የሚሻለው ተቀራርቦ ሁለቱን አገራት የሚጠቅም ሥራ ለመሥራት ማሰብ ነው። ይህን በሚገባ የተገነዘቡት የግብፅ ባለስልጣናት ሳይቀሩ ግድቡ ህዝባቸውን እንደማይጎዳ ማስተማር አለባቸው። ይህን ባለማድረጋቸው ግን በመጨረሻ የሚጎዱት እነሱ ራሳቸው ናቸው። እኛ የጀመርነው ግንባታ ከእንግዲህ ወደ ኋላ አይመለስም።» የአቶ ብርሀኑ አቋም ነው።
የጥናቱ ፋይዳና ግንባታው አልተገናኝቶም
በጀርመን አቸን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የውሃ አስተዳደርና የኃይል ማመንጫ ግድቦች ጉዳዮች ዳይሬክተር ግብፃዊው ሀኒ ስዊላም እንደገለፁት፥ የህዳሴ ግድቡ ሊኖረው ይችላል ተብሎ የተገመተው ተፅእኖን የሚያጠኑት ፈረንሳያዊያኑ ኩባንያዎች ቢአርኤል እና አርቴሊያ በግብፅ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ መንግሥታት በኩል እውቅና ተሰጥቷቸው የጥናት ሥራውን እያከናወኑ ይገኛሉ።
እንደ ሀኒ ስዊላም አስተያየት ከሆነ ኩባንያዎቹ የጀመሩት ጥናት ከአንድ ወር ያልዘለለ እድሜን አስቆጥሯል። ይሁን እንጂ በውላቸው መሰረት ጥናቱን የሚያጠናቅቁት በ11 ወራት በመሆኑ እስከዚያ ድረስ ደግሞ የግድቡ ግንባታ ይጠናቀቃል የሚል ስጋት አላቸው። በዚህም ሁኔታ ውስጥ እያለ የህዳሴ ግድቡ ከተጠናቀቀ በኋላ ግድቡ በግብፅ ላይ የሚኖረውን ተፅእኖ የማጥናት ሥራው ትርጉም አይኖረውም፤ የጥናቱ አስፈላጊነት ላይም እንደማይስማሙ ይገልጻሉ።
«በአሁኑ ወቅት ኩባንያዎቹ የግንባታውን ተፅእኖ እያጠኑ ነው። ጥናቱ ሳያልቅ ግንባታው ይጠናቀቃል። በመሆኑም በጥናቱ መጨረሻ ተፅእኖ አለው ቢባል እኛ ግብፃውያን ምን ልናደርግ ነው? ግድቡን ልናፈርስ ወይስ ምን እናደርጋለን? ይህን በመገንዘብ ኢትዮጵያም ጊዜውን እየተጠቀመችበት ነው። በመሆኑም ጥናቱ እስኪጠናቀቅ የግድቡ ግንባታ መቆም አለበት» ሲሉ ሀኒ ስዊላም ይጠይቃሉ።
ህጋዊውን ሁኔታ አስመልክተው ዓለም አቀፍ የህግ ፕሮፌሰርና የግብፅ የውጭ ጉዳዮች ካውንስል አባል አይማን ሰላማ በሀኒ ሰዊላም ሀሳብ አይስማሙም። እርሳቸው እንደሚሉት ግብፅ፥ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ አንድታቆም የመጠየቅ መብት የላትም። «ባለፈው ዓመት የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በጋራ የተፈራረሙት የሶስትዮሽ ስምምነት መዘንጋት የለበትም። በመሆኑም ሱዳንም ሆነች ግብፅ፥ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን ግንባታ እንድታቆም የሚያደርግ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታም ሆነ የህግ ማዕቀፍ የላቸውም።» ሲሉ ፕሮፌሰር አይማን ለግብፁ አህራም ኦንላየን አስታ ውቀዋል።
ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ የአይማን ሰላማን ሀሳብ ደግፈው እንደገለፁት የፈረንሳይ ኩባንያዎች ጥናት የሚያጠ ኑበት ምክንያት የግድቡን ማለቅ እና አለማለቅ ተከ ትሎ አይደለም። ይልቁንም የጥናቱ ቁልፍ ዓላማ ግድቡ በተፋሰሱ አገራት ሊኖር ይችላል የተባለውን ስጋት ለመቅረፍ የሚያስችል ሆኖ ያሉ ነገሮችን ለማመላከት ነው።
ጥናቱ የመጀመሪያ ደረጃ መረጃዎችን ተጠቅሞ አሊያም ተፅእኖ መገምገሚያ መስፈር ቶችን ያስቀመጠ ነው። በተለ ይም ከዓለም አቀፍ ሙያተኞች የተሰነዘሩ ምክረ-ሀሳቦች መሰረት ግድቡ ተፅእኖ ካለው በጥናቱ መመልከትና የሚወሰዱ ችግሮችን የማቅለያ እርምጃ ዎችን ለመተግበር እንጂ የተጀመረውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማቋረጥ አለ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አመልክተዋል።
«የጥናቱ አላማ ይህ አይደለም። ከጥናቱ ጋር የማይተሳሰሩና የሌሉ ነገሮችን በማራገብ አሁንም ህዝቦቻቸውን ግራ ለማጋባት እንጂ ከጥናቱ ጋር የሚያያይዘው ምንም ጉዳይ የለም። ግድቡ ይሠራል፤ አይቋረጥም። የጥናቱ ፋይዳ ግድቡ ተፅእኖ ካለው ለማየት፤ ጉልህ ተፅእኖ የሚያመጣ ከሆነም የማቅለያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ነው።» ብለዋል ኢንጂነር ስለሺ፡፡
እንደ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ምላሽ በኢትዮጵያ በኩል ያለው መረጃ የግድቡ ግንባታ በተፋሰሱ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት አያስከትልም። ምክንያቱም ግድቡ እየተገነባ ያለው ለኃይል ማመንጫነት ብቻ በመሆኑ ምንም የሚባክን ውሃ አይኖርም ብለዋል። ነገር ግን በኢትዮጵያ በኩል በግብፅ ላይ የሚፈጥረው ተፅእኖ እንደሌለ ስለሚታ ወቅ ጥናት ቢደረግም ባይደረግም በኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣው ምንም ችግር የለም ነው ያሉት።
ግብጾች “ይህ ችግር ይፈጠራል፤ ያኛውም ችግር እንዲሁ ነው” እያሉ የሚያነሷቸው ሀሳቦች ውሃ የሚቋጥሩ አይደ ሉም፤ ይህንንም ሀቅ በሚገባ እንደሚያውቁት ኢንጅነር ስለሺ አረጋግጠዋል። ምክንያቱም የግድቡ ዓላማ ለኃይል ማመንጫ እንጂ ለመስኖ ልማት የሚውል አይደለም ነው የሚሉት ሚኒስትሩ። ግብፃውያኑ የህዳሴ ግድቡ ለመስኖ ልማት የታሰበ አድርገው የሚስሉት ስዕል እንጂ ሌላ አይደለም ይላሉ። ይህ ደግሞ ህዝብን ማሳሳት እንጂ የሚጠቅም ሥራ አለመሆኑን ይገልጻሉ።
ቁመቱ ምን አደረገ?
ኑር አል-ዲን በካይሮ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ሀብት ፕሮፌሰር ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር በምታደርገው ድርድር የግድቡን ቁመት እንዲቀነስ የሚያስችል ፅኑ አቋም ልትይዝ ይገባል ይላሉ። በመሆኑም 145 ሜትር ቁመት ያለው የህዳሴ ግድብ ከ120 እስከ 122 ሜትር ዝቅ ማለት አለበት ብለዋል። ይህም የሚሆነው የግድቡን ውሃ የመያዝ መጠን እንዲቀንስ በማሰብ ነው።
«የግድቡን ቁመት የመቀነስ ጥያቄው በመሰረቱ ምላሽ የሚያስፈልገው አልነበረም። ግድቡ በራሱ ዲዛይን ተሠርቶለት ስምንት ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ የሚታደስ የውሃ መጠን እንዲኖረው ተደርጎ አጠቃላይ የግድቡ የመያዝ መጠን 78 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ነው። ይህንን የሚለውጥም ሆነ የሚያሻሽል ምንም ዓይነት የቁመትም ሆነ የስፋት ለውጥ አይኖርም። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ በኩል ምንም ሊኖር የሚችል አማራጭ መንገድ እንኳ አይኖርም።» ሲሉ ምላሽ የሰጡት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ናቸው።
ይህ ቢሆንስ
በአጠቃላይ የህዳሴው ግድብን በሚመለ ከት በኢትዮጵያም ሆነ በግብፃውያኑ በተለይ በምሁራኑ ዘንድ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰባቸው ሁለት ቁም ነገሮች ወይም ምክረ-ሀሳቦች አሏቸው። አንደኛው ግድቡን በሚመለከት ተከታታይና ግልፅነት ያለው የተጠናከረ የመረጃ ልውውጥ ሊኖር ይገባል የሚል ነው። ይህ ደግሞ በቀጣይ የሚደረጉ ጥናቶችን ያለ ምንም እንከን፥ ግልፅነትና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን የሚያረጋግጥ ይሆናል የሚል እምነት አላቸው።
ምሁራኑ ሁለተኛው ያስቀመጡት ቁም ነገር ወይም መክረ-ሀሳብ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ መንግሥታት የሚያደርጉት ያልተቋረጠ ድርድርና ስምምነት አሁን የሚነሱ ብዥታዎችን በሚቀርፍ መልኩ በትብብርና በመግባባት መርህ ሊሰሩ ይገባል የሚል ነው። በተለይ አገራቱ ከእነሱም ባለፈ ለቀሩት የተፋሰሱ አገራት ህዝቦች ጭምር ሊያስቡና ፍትሀዊነትን ማዕከል ያደረጉ ስምምነቶችን ማከናወን ይኖርባቸዋል ሲሉ ሀሳብ አቅርበዋል።
ሀብታሙ ስጦታው
– See more at: http://ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/business-market/item/11993-2017-04-01-18-34-17#sthash.7pThl6PX.dpuf